የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ እና ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አረዳ ፍትህን ለሁሉም ለማድረስ እንደሚሰሩ ገለፁ

አቶ ሰለሞን አረዳ እና ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ

የፎቶው ባለመብት, Solomon Areda FB/Getty Images

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ረቡዕ ዕለት ከተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት ለተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን በፍራንክፈርት ኮሜርዝ አሬና ስታዲያም ባደረጉት ንግግር፤ የፍትሕ፣ የምርጫ ቦርድ እና የደህንነት አካላቱን ተዓማኒ እና ገለልተኛ ለማድረግ የመዋቅር ማሽሻያ እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል።

ለተቋሞቹ በዘረፉ ብቁ የሆኑ መሪዎችን መሾም የዚህ ለውጥ አካል መሆኑን ጭምርም ተናግረው ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትሩ ከአውሮፓ ቆይታቸው ሲመለሱ፤ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት እጩ አድርገው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የወ/ሮ መዓዛን ሹመት በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

ምክር ቤቱ በተጨማሪም አቶ ሰለሞን አረዳን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አድርጎ ሾሟል።

ቢቢሲ ከአዲስ ተሿሚዎቹ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ እና ከምክትላቸው አቶ ሰለሞን አረዳ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

ወ/ሮ መዓዛ ''ሁልጊዜም የማስበው ስለ አገልግሎት እንጂ ስለ ሹመት አይደለም'' ሲሉ ሹመቱን እንዳልጠበቁት ቢገልጹም፤ ሹመቱ ''ትልቅ ክብር ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያን ህዝብ የማገልገል እድል ስለተሰጣቸው ደስተኛ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

''የፍርድ ቤት መሪ ስሆን ፍትሕ ለሁሉም እንዲደርስ ነው የምፈልገው። ጥረቴም፤ ትኩረቴም ፍትሕ ለሁሉም እንዲደርስ ማድረግ ነው'' በማለት ቅድሚያ የሚሰጡትን ጉዳይ ጠቁመዋል።

አቶ ሰለሞን አረዳ በበኩላቸው፤ ወደ ሥራ ሲገቡ ቅድሚያ ስለሚሰጡት ጉዳይ ተጠይቀው፤ ''ከቅልጥፍና፣ ከውጤታማነት እና ፍርድ ቤትን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር ከህብረተሰቡ ከፍተኛ ቅሬታ ይነሳል። ከዚህ በላይ ደግሞ 'ፍርድ ቤቶች ውሳኔ የሚሰጡት ገለልተኛ ሆነው አይደለም' የሚሉ ቅሬታዎች በስፋት ይነሳሉ። በባለሙያዎች የተደረጉ ጥናቶችም ይህነኑ ስሞታ የሚያሳዩ ናቸው።" በማለት ገልጸው፤ የወደፊት የትኩረት አቅጣጫቸውን አስቀምጠዋል።

እሳቸው እንደሚሉት፤ "ከፍርድ ቤቶች ገለልተኛነት እና ነጻነት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮችን ለመቅረፍ ቅድሚያ ሰጥተን የምንሰራው ጉዳይ ነው''።

ፍርድ ቤቶችን እንደ መሳሪያ በመጠቀም፤ የመንግሥት ባለስልጣናት በፍርድ ቤት ሥራዎች ጣልቃ እየገቡ የግል ወይም የፓርቲ ፍላጎቶችን የሚያስፈጽሙባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ በማለት የሚያስታውሱት አቶ ሰለሞን፤ ህብረተሰቡ በፍርድ ቤት ላይ ያለው እምነት ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻልበት ደረጃ ተሸርሽሯል ይላሉ።

ህብረተሰቡ በፍርድ ቤቶች ላይ ያለውን እምነት መመለስ ቅድሚያ ሰጥተው የሚሰሩት ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል። ይህንን ለማሳካትም ህብረተሰቡም ሆነ መንግሥት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነቶች መወጣት አለባቸው ብለዋል።

በተመሳሳይ መልኩ ወ/ሮ መዓዛ፤ ''በፍርድ ቤቶች አሰራር ላይ የህዝቡ እምነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያነሰ የመጣበት ሁኔታ አለ'' ይላሉ።

ወ/ሮ መዓዛ በፍርድ ቤቶች ላይ እምነት የተሸረሸረበትን ምክንያት እናጣራለን ብለው፤ የሕግ እና የአሰራር ለውጦችን በማድረግ የህብረተሰቡን ዕምነት ለመመለስ ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሰሩ አክለዋል።

''ይህንን ሹመት ከመቀበሌ በፊት ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርጊያለሁ። ባደረኩት ውይይት ዳኝነት እንዲከበር እና እንዲጠናከር ያላቸውን ፍላጎት ተረድቻለሁ፤ ከዚህ በኋላ ነው ይህን ሃላፊነት ለመውሰድ የወሰንኩት።'' ይላሉ ወ/ሮ መዓዛ።

አቶ ሰለሞን፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የፍርድ ቤቶች አፈጻጸም መለኪያ መስፈርት የሚያሟላ ቀልጣፋ የሆነ አገልግሎት የሚሰጥ ፍርድ ቤት እንዲኖር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

"ከፍርድ ቤት መዋቅር ውስጥ የሚመነጩም ሆነ ከውጪ የሚመጡ ፈተናዎች ይኖራሉ ብዬ እገምታለሁ" በማለት ወደ ፊት በስራቸው ላይ ተግዳሮት ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን ያነሳሉ።

እሳቸው እንደሚሉት "ከውስጥም የተለመዱ አሰራሮች እና አመለካከቶች ጋር ተያይዞ ብዙ ፈተናዎች አንደሚገጥሙን እገምታለሁ።

ከውጪ ደግሞ ህብረተሰቡን ጨምሮ የፍርድ ቤት ባለድርሻ አካላት አሉ። የተለመደውን አይነት አሰራር ጥሰን ልንወጣ ስንሞክር ፈተናዎች ሊገጥሙን ይችላሉ"።