የቱርክ ባለስልጣናት፡ የሳዑዲ ጋዜጠኛው ጀማል ኻሾግጂ አስክሬን 'በአሲድ እንዲሟሟ ተደርጓል'

Khashoggi

የፎቶው ባለመብት, EPA

የቱርክ ፕሬዚዳንት ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ያሲን አከታይ ጀማል ኻሾግጂ ከተገደለ በኋላ አስክሬኑን በመቆራረጥ በአሲድ አንዲቀልጥ ተደርጓል ብለን እናምናለን አሉ።

የሳዑዲው ጋዜጠኛ ኢስታንቡል ውስጥ ከተገደለ በኋላ የተፈጸመበትን ወንጀል ለመሸሸግ አስክሬኑ እንዳይገኝ ስለመደረጉ ከድምዳሜ ላይ ተደርሷል ብለዋል።

ከአንድ ወር በፊት የሳዑዲ መሪዎችን በመተቸት የሚታወቀው ኻሾግጂ ኢስታንቡል በሚገኘው የሳዑዲ ቀንስል ጽ/ቤት ውስጥ መገደሉ ይታወሳል።

የኻሾግጂ አስክሬን በአሲድ እንዲቀልጥ መደረጉን የሚያሳይ ምንም አይነት የምርመራ ውጤት ግን እስካሁን አልተገኘም።

''የኻሾግጂን አስክሬን የቆራረጡት በአሲድ ለማቅለጥ እንዲመች ነው'' ሲሉ የፕሬዚዳንቱ አማካሪ ሁሪያት ለተሰኘ ዕለታዊ ጋዜጣ ተናግረዋል።

''አስክሬኑን መቆራረጥ ብቻ አይደለም፤ እንዲተንም ጭምር አድርገውታል'' ሲሉ ያሲን አከታይ ተናግረዋል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

በቅርቡ ለመጋባት እቅድ እንደነበራቸው የምትናገረው የኻሾግጂ እጮኛ ከባድ ሃዘን ውስጥ ናት።

የኻሾግጂ እጮኛ የዓለም መሪዎች ገዳዮቹን ለፍርድ እንዲቀራቧቸው ጠይቃለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሳዑዲው አልጋ ወራሽ ልዑል ሞሐመድ ቢን ሰልማን «ኻሾግጂ እንደ አደገኛና አክራሪ ኢስላሚስት ነው የማየው» ብለው ለአሜሪካ መናገራቸው ተዘግቧል።

አልጋ ወራሹ ከዋይት ሃውስ ጋር በስልክ ይህን ውይይት ያደረጉት ኻሾግጂ መሞቱ ሳይታወቅ ጠፍቶ ሳለ ነበር ተብሏል።

የአሜሪካ ጋዜጦች ዋሽንግተን ፖስት እና ኒው ዮርክ ታይምስ ያወጡትን ይህን ዘገባ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ክዶታል።

ከሁለት ቀናት በፊት የቱርክ መርማሪዎች ኻሾግጂ ታንቆ መቀደሉን አረጋግጠዋል።

ስለ ጀማል ኻሾጂ አሟሟት እስካሁን የምናውቃቸው እውነታዎች

ሳዑዲ ዜግነት ያለው ዝነኛው ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾጂ ቱርክ ኢስታንቡል ወደ ሚገኘው የሳዑዲ ቆንስላ የገባው ከአንድ ወር በፊት ነበር። የጀማል ኻሾግጂ ወደ ቆንስላው ገብቶ ደብዛው ለሁለት ሳምንታት ጥፍቶ ነበር።

በወቅቱ የቱርክ ባለስልጣናት በሳዑዲ ሰዎች ስለመገደሉ የድምጽ ማስረጃ አለን ብለዋል።

ሳዑዲ ግን በተደጋጋሚ ጀማል ወደ ቆንስላው ከገባ ከደቂቃዎች በኋላ ቆንስላውን ለቅቆ ወጥቷል ብትልም ቆይታ ግን መገደሉን አምናለች።

ሳዑዲ ጀማል ኻሾግጂ መገደሉን ከማመኗ በፊት የሃገሪቱ ጠቅላይ አቃቢ ሕግ በቆንስላው ውስጥ በነበሩ ሰዎች እና ጀማል መካከል በተፈጠረ ጸብ ምክንያት ሊሞት ችሏል ብለው ነበር።

ጀማል ኻሾጂ ማን ነበር?

ጀማል ኻሾግጂ በሳዑዲ ዝነኛ ጋዜጠኛ ነበር፤ የሶቪየት ሕብረት የአፍጋኒስታን ወረራን በዝርዝር ዘግቧል። እንደ ኦሳማ ቢን ላድን ከመሳሰሉ ግለሰቦች ጋር ቃለ መጠይቅ አድርጓል።

ለበርካታ አስርት ዓመታት ለሳዑዲ ንጉሳውያን ቤተሰብ የቅርብ ሰው ነበር፤ የሳዑዲ መንግሥት የመገናኛ ብዙሃን አማካሪ ሆኖም ሰርቷል።

ባለፈው ዓመት ግን ከሳዑዲ መንግሥት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ሃገር ጥሎ ወደ አሜሪካ ተሰደደ። አሜሪካም ሆኖ የዋሽንግተን ፖስት አምደኛ ሆነ። በጽሑፎቹ የሳዑዲ አረቢያውን ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማንን ይተች ነበር።

ይህን ከሳዑዲ መንግሥት ጋር ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ እንዳስገባው በርካቶች ይናገራሉ።

ወደ ሳዑዲ ቆንስላ ለምን አቀና?

ጀማል ኻሾግጂ ወደ ቆንስላው የሄደው ከቀድሞ ሚስቱ ጋር መፋታቱን የሚያረጋገጥ ዶሴ ለማግኘት፣ ከዚያም ቱርካዊት እጮኛውን ለማግባት በዕለተ አርብ መስከረም 18 በቆንስላው ተገኘ።

በቆንስላው ያሉ ሰዎች ግን ለማክሰኞ ጥቅምት 12 ቀጠሩት።

''ቱርክ ውስጥ በሚገኝ የሳዑዲ ቆንስላ ውስጥ ምንም ሊያደርጉኝ አይችሉም ብሎ ገምቶ ነበር'' ስትል እጮኛው ለዋሽንግተን ፖስት ጽፋለች።

''ጀማል ምንም እንደማይገጥመው እርግጠኛ ነበር''

ማክሰኞ ጥቅምት 12 ከቀጠሮ ሰዓት 15 ደቂቃ ቀደም ብሎ ወደ ቆንስላው ሲገባ በተንቀሳቃሽ ምስል ይታያል።

ጀማል ወደ ቆንስላው ከመግባቱ በፊት ለእጮኛው ሁለት ስልክ ቁጥሮች ሰጥቷት ካልተመለስኩ ለቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ታይብ ኤርዶዋን አማካሪዎች ደውለሽ ንገሪያቸው ብሏት ነበር።

እጮኛው ሳትታክት ለ10 ስዓታት በቆንስላው በር ላይ ጠበቀችው። በነጋታውም ወደ ቆንስላው ሄዳ ጠበቀችው ጀማል ግን የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ።

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የጀማል እጮኛ ሳትታክት ለ10 ስዓታት በቆንስላው በር ላይ ጠብቃው ነበር።

በወቅቱ በጉዳዩ ላይ የሳዑዲ አረቢያ ምላሽ ምን ነበር?

ለሁለት ሳምንታት ያክል ሳዑዲ በጀማል እጣ ፈንታ ላይ የማውቀው ነገር የለም ስትል ቆይታ ነበር።

ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን ለብሉምበርግ ሲናገሩ ''ጀማል ላይ ስለሆነው ነገር ለማወቅ ጓጉችያለሁ። ከደቂቃዎች በኋላ ወይም ከአንድ ሰዓት ቆይታ በኋላ ጉዳዩን ጨርሶ ወጥቷል'' ብለው ነበር።

''ምንም የምንደብቀው ነገር የለም'' ሲሉም ተደምጠዋል።

ልዑል አልጋ ወራሹ ይህን ባሉ ከቀናት በኋላ የሳዑዲ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋዜጠኛው በቆንስላው ውስጥ በተፈጠረ ጸብ ምክንያት ለሞት ተዳርጓል ሲል ዘገበ።

ብሔራዊ የቴሌቪዝን ጣቢያውን ጨምሮ እንደዘገበው ከጀማል ግድያ ጋር በተያያዘ 18 የሳዑዲ ዜጎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

በኢስታንቡል የሚገኘው የሳዑዲ ቀንጽላ

ቱርክ ጀማል ላይ ምን ደረሰ አለች?

ከሁለት ሳምንት በፊት የቱርክ ባለስልጣናት ጀማል በሳዑዲ የጸጥታ ኃይሎች በቆንጽላ ውስጥ እንዲሰቃይ ተደርጎ ተገድሏል፤ ከዚያም አስክሬኑ በሰዋራ ስፍራ ተጥሏል ብለው ነበር።

ቱርኮች ይህን የሚያረጋግጥ የቪዲዮ እና የድምጽ ማስረጃ አለን ይላሉ። ይሁን እንጂ የቪዲዮ እና የድምጽ መረጃዎቹ ለህዝብ ይፋ አልሆኑም።

ሳብሃ የተሰኘ የቱርክ ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ በቆንጽላው ውስጥ የሚሰሩ የቱርክ ዜግነት ያላቸው ሰራተኞች በጀማል ቀጠሮ ዕለት በፍጥነት ቆንስላውን ጥለው እንዲወጡ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው ነበር።

ዛሬ ከሰዓት ደግሞ የቱርክ ባለስልጣናት ጀማል ኻሾግጂ ከተገደለ በኋላ አስክሬኑን በመቆራረጥ በአሲድ አንዲቀልጥ ተደርጓል። ከዚያም እንዲተን ሆኗል ብለዋል።

በጀማል ግድያ እጃቸው አለበት የተባሉት የሳዑዲ የጸጥታ ኃይል አባላት እነማን ናቸው?

የቱርክ መገናኛ ብዙሃን 15 አባላት ያሉት የሳዑዲ ቡድን የጀማል ደብዛ የጠፋ ዕለት ከሳዑዲ አረቢያ ወደ ኢስታንቡል ቱርክ በግል አውሮፕላን መጥተዋል።

ከ15ቱ ሰዎች መካከል ማህር ሙትሬብ የተባለው ግለሰብ ለንዶን በሚገኘው የሳዑዲ ኤምባሲ የጸጥታ እና ደህንነት አባል መሆኑን ቢቢሲ አረጋግጧል።

አራት ግለሰቦች ደግሞ ከልዑል አልጋ ወራሹ ሞሐመድ ቢን ሰልማን ጋር ቅርርብ አላቸው።

የቱርክ መገናኛ ብዙሃን እንደሚሉት ከሆነ 15ቱ ግለሰቦች አጥንት መቁረጫ መጋዝ ይዘው ነው የመጡት።

ከግለሰቦቹም መካከል አንዱ የሬሳ ምርመራ ባለሙያ ነው ተብሏል።

የፎቶው ባለመብት, AFP