ጫትን መቆጣጠር ወይስ ማገድ?

የጫት ንግድ Image copyright ZACHARIAS ABUBEKER

ጫት የጤናና ማህበራዊ ቀውሶች ይዳርጋል ፣ የዜጎች ምርታማነት ይቀንሳል ፣ ቤተሰባዊ መስተጋብርን ያዛባል በሚል ሃሳብ፤ ከሰሞኑ የአማራ ክልል ምክርቤት በጫት ላይ ህግ ለማውጣት የሚያስችለውን ምክረ ሃሳብ ረቂቅ አዋጅ አፅድቋል።

አማኑዔል ያየህ ከባህርዳር ዙሪያ ቀበሌዎች ወደ ከተማው ጫት በሞተር በማጓጓዝ ይተዳደራል። በዚህ ስራም በወር 1200 ብር ያገኛል። ይሁን እንጂ ከሰሞኑ በክልሉ ይፋ የተደረገው ጫትን የማገድ እቅድ ስራ እንዳያጣ አስግቶታል።

"ምንም ከህዝብ የሚደበቅ ነገር አይኖርም" አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽመልስ አብዲሳ

የሴቶች መብት ታጋይዋ ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ማን ናቸው?

"ሌሎች ሴቶች ላይ የአሲድ ጥቃት ሳይ ይረብሸኛል፤ ህመሜን ያስታውሰኛል" ካሚላት መህዲ

በተለይም ገቢያቸው ዝቅተኛና ከጫት ጋር በተያዘ ብቻ ህይወታቸውን የሚመሩ ግለሰቦችን ኑሮ እንደሚያቃውስም ያምናል።

"ጫት በመቁረጥና እንዲሁም እንደኔ በማመላለስ ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተደድሩ አሉ። የጫት ድርጅት የያዘው ሰራተኛ ከአንድ መስሪያ ቤት የማይተናነስ ነው። ስለዚህ ጫት ቢታገድ ብዙ ስራ አጥ ይኖራል። እኔ ራሱ ጫት ቢያቆም ምን እንደምሰራ አላውቅም" ይላል

የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ፅ/ቤት ከሚያዚያ 17፣ 2010 ዓ.ም ተግባራዊ የሚሆንና በአንድ ኪሎ ግራም 30 በመቶ ወይም 30 ብር ቀረጥ በጫት ላይ ጥሎ ነበር።

በወቅቱ ያነጋገርናቸው የባህርዳር ገቢዎች ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ዘውዱ ክፍሌ ቀረጥ መጣል ያስፈለገበትን ምክንያት ገልፀዋል።

"ጫት እንዳይበረታታ፣እንዳይስፋፋ፤ ተጠቃሚው ደግሞ ገዝቶ የመጠቀም አቅሙን የማዳከም ስራ እንራለን። ቀረጡም አንድ አጋዥ ይሆናል ብለን እናስባለን። ከዚህ በተጨማሪ ገቢ ተቋሙ ገቢውን በመሰብሰብ ለሌላ የልማት አገልግሎት የሚውልበት መንገድ ይኖራል"

የአማራ ክልል ምክር ቤት በጫት ላይ ህግ ለማውጣት በጉባዔው ላይ ምክረ ሃሳቡን ያቀረቡት የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊ አቶ ልዑል ዮሐንስ ወደዚህ መንደርደሪያ ሃሳብ ስትገቡ የቁጥጥር አቅማችሁን አይታችኋል ወይ ብሎ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ

" በማህበረሱ ልምድ የሆነና ወደ ባህልነት የተጠጋ ከመመሆኑ አንፃር፤ በአንድ ጊዜ የሚቀረፍ ችግር አይሆንም። አስበን እየሰራን ነው ያለነው አመታትን እንደሚወስድ እናውቃለን" ብለዋል።

ጫት የአገር ውስጥን ብቻ ሳይሆን የውጭ ምንዛሬ ገቢን ከሚያስገኙ ምርቶች ግንባር ቀደሙ እንደሆነ ይነገራል። የህብረተሰቡን የገቢ ምንጭን ጫትን ከማስቀረት ዕቅዱ ጋር ማስታረቂያው ምንድን ነው?

"የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በተመለከተ አንዱ ምክር ቤቱ ያሳለፈው በልዩ ሁኔታ እዚህ ውስጥ የተሰማሩ የህብረተሰቡ ክፍሎችን ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር መንግሥት ልዩ ማበረታቻና ድጋፍ አድርጎ ተመጣጣኝ የሆነ ስራ የሚሰሩበት ሁኔታ ይመቻቻል። " ያሉት አቶ ልዑል ሊተካው ሊተካው የሚችል ስራ የገቢ ምንጭን በተመለከተ ዝርዝር የማስፈፀሚያ እቅዶች ሲወጡ አብሮ የሚፈፀም እንደሆነም ተናግረዋል።

በክልሉ ያለውን መቆጣጠር ቢቻልም ከሌሎች ክልሎች ጋር ወጥ የሆነ አቋም ከሌለ አስቸጋሪ ነው የሚሉት ኃላፊው ይህንንም ለመፍታት ጅማሮው እንዳለ ያስረዳሉ።

" ብቻችንን ውጤታማ መሆን ስለማንችልና ጉዳዩም በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲታይ፤ የክልሉ ምክር ቤት ለፌደራል ምክር ቤት ጉዳዩን ልኳል። ከድንበር፣ ድንበር፤ ከክልል ክልል የሚንቀሳቀስ ስለሆነም በጋራ ለመስራት ከሌሎች ክልሎች ጋር መነጋገር አለብን።" ብለዋል።

በፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ(ኤፍኤስኤስ) ተመራማሪ የሆኑትና ጫት ላይ የተለያዩ ጥናቶችን ያደረጉት ዶ/ር ዘሪሁን መሃመድ ጫትን በሚመለከት የተሳሳተ ግንዛቤ አለ ይላሉ።

እሳቸው እንደሚሉት ጫትን ከልክ በላይ በመጠቀም ራሳቸውን የሚጎዱ ሰዎች አሉ።ሁሌም ስለጫት ሲታሰብ የሚታየው ይህ ጎን ብቻ ነው።ነገር ግን ኑሯቸው በጫት ላይ የተመሰረተ በርካቶች መሆናቸው እንዲሁም ጫትን በአግባቡ የሚጠቀሙ መኖራቸውም ታሳቢ ሊደረግ ይገባል።

ለቀናት የተዘጋው የአላማጣ- ቆቦ መንገድ ተከፈተ

"መጠጥን ባልተገባ መንገድ የሚጠቀሙ እንዳሉ ሁሉ ጫትንም በተመሳሳይ መንገድ የሚጠቀሙ መኖራቸው ነው ሊሰመርበት የሚገባው" ይላሉ።

ጫት የብዙዎች ኑሮ እንዲሁም ለአገሪቱ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ከመሆኑ አንፃር የሚያዋጣው አካሄድ ጫትን መቆጣጠር እንጂ ማገድ እንዳልሆነ ይናገራሉ።

"ማገድ ግን ጫትን ኮትሮባንድ ከማድረግ የዘለለ የሚያመጣው ነገር አለ ብዬ አላምንም"

በምን መንገድ ጫት ላይ ቁጥጥር ይደረግ የሚለውን በሚመለከትም በጉዳዩ ላይ ምርምር ያደረጉ ሰዎች የተለያየ ሃሳብ ስላላቸው ይህ ጉዳይም ብዙ መነጋገርን እንደሚጠይቅ ዶ/ር ዘሪሁን ይገልፃሉ።