"የቅማንትን ሕዝብ እንወክላለን የሚሉ ፅንፈኞች ከሌሎች ጋር በቅንጅት እየሰሩ ነው" ጄኔራል አሳምነው

ጄኔራል አሳምነው ፅጌ

ከሰሞኑ በአማራ ክልል ውስጥ በቅማንት ህዝቦች ላይ ጥቃት እየደረሰ ነው፤ ከዚህም በተጨማሪ መተማ ላይ የቅማንትና የትግራይ ተወላጆች ላይ በታጣቂዎች ጥቃት እየደረሰባቸው እንደሆነ መረጃዎች እየተሰሙ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ የአማራ ክልል የፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ብርጋዲየር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ቢቢሲ፦ በቅርቡ በቅማንት ተወላጆች ላይ አማራ ክልል ውስጥ ጥቃት እየደረሰ ነው የሚሉ ዘገባዎች ይደመጣሉ። ስለዚህ ያለዎት መረጃ ምንድነው?

ጄነራል አሳምነው፦ የቅማንትና የአማራ ሕዝብ ለዘመናት አብሮ የዘለቀ ሕዝብ ነው። በብዙ ነገር የተሳሰረ ሕዝብ ነው፤ ሕብረተሰብ በሚያገናኙ እንደ ባህል እና ቋንቋ ባሉ እሴቶች የተሳሰረ ነው። ሰሞኑን የተፈጠረው ሁኔታ ቀደም ብሎ የተለያዩ ኃይሎች በተለያየ መንገድ የአካቢቢውን ሰላም ለመንሳትና አለመረጋጋቱ እንዲቀጥል ለማድረግ በፈጠሩት ሥራ የተፈጠረ ችግር ነው።

እንደ ሕዝብም ሆነ እንደ ተቋም ሲታይ፤ የቅማንት ሕዝብ በተለየ መንገድ ጥቃት የሚደርስበት ተጨባጭ ሁኔታዎች የሉም። ስለዚህ የቅማንትን ሕዝብ እንወክላለን የሚሉ ፅንፈኛ ኃይሎች ከሌሎች ጋር በቅንጅት በመሥራት አካባቢው እንዲቃወስ ለማድረግ ሞከረዋል።

"ምንም ከህዝብ የሚደበቅ ነገር አይኖርም" አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አቶ መላኩና ጄነራል አሳምነው ለማዕከላዊ ኮሚቴ ተመረጡ

ከጄኔራሎቹ ሹመት ጀርባ?

ለምሣሌ በቅርቡ በተነሳው ግጭት ከአማራም፤ ከቅማንትም ሰዎች ሞተዋል። ቁጥሩ መጣራት ቢኖርበትም በአማራ በኩል የሞተው ያይላል። ይህ ጥቃትን ሳይሆን ግጭትን የሚያመለክት ነው። ነገር ግን ይህንን ለመጠቀም የሚፈልጉ ኃይሎች ይኖራሉ። በገበሬ ደረጃ ሊያዙ የማይችሉ ትጥቆች ሁሉ ተገኝተዋል።

ከጎረቤት ሃገር ሊሆን ይችላል፤ ከጎረቤት አካባቢ ወይም ክልል ሊሆን ይችላል፤ ብቻ የቆየ ጥቅማቸውን ለማሳካት 'ስትራቴጂ' ነድፈው እየተንቀሳቀሱ ያሉ አሉ።

ቢቢሲ፦ ብዙ ጊዜ የውጭ ኃይሎች፤ ሰላም የማይፈልጉ እና መሰል አገላለፆች አሉ። ነገር ግን ጣልቃ የሚገባ ኃይል አለ ተብሎ የሚታመን ከሆነ ለምን ስም መጥራት አልተፈለገም?

ጄነራል አሳምነው፦ እሱ ይጣራል። ይጣራል ብቻ ሳይሆን አደጋ እስከሆነ ድረስ ደግሞ ትግል ይካሄድበታል። በመረጃ የበለጠ አጠናክረን ይህንን ኃይል ማጋለጥም፤ መታገልም ይቻላል። ብቅ ብቅ የሚሉት መረጃዎች አንድ ላይ 'ሰመራይዝ' (ተጠቃለው) ፤ ከዚህ በኃል እየሆነ ያለው ነገር እናያለን።

ለምሳሌ ቅማንት 69 ቀበሌዎች እንዲያደራጅ ተፈቅዶለታል። ኃይሉ ይህ እንዲደራጅ አልፈለገም፤ የብጥብጥ ቀጠና እንዲሆን ነው የፈለገው። እነኚህ ኃይሎች ደግሞ ከጎረቤት ክልል የሚድያ ሽፋን ይሰጣቸዋል። ለምሳሌ የዛሬ ሁለትና ሶስት ዓመት የተደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች ከሰሞኑ እንደተደረጉ ተደርገው ይቀርባሉ።

የሞተው ሌላ ሆኖ እያለ የሞተው ይሄ ነው ይባላል። ላሊበላ ላይ የደረሰ ግጭት እንደቅማንት ሆኖ ይቀርባል። እንዲህ ዓይነት ከእውነታ የራቀ መረጃ ይለቀቃል። ፌስቡክ ያለው ጥሩ ገፅታ እንዳለ ሆኖ መጥፎ የሆኑ መረጃዎች ይሰራጩበታል። ይህንን መረጃ ባትቀበሉት ጥሩ፤ ከተቀበላችሁት ደግሞ ብታጣሩት ደስ ይለኛል።

ቢቢሲ፦ ከጎረቤት ክልል ድጋፍ ይደረግላቸዋል የሚል ነገር ነግረውናል፤ የትኛው ክልል ይሆን?

ጄነራል አሳምነው፦ እሱን እነግርሃለሁ፤ በሂደት ብዬ ነው። እነርሱም ያውቁታል፤ እኛም እናውቀዋለን። ከእኔ ይበልጥ ሚድያ ላንተ ይቀርባል። ከኔ ልስማው ብለህ ካልሆነ በስተቀር 'ዩ ኖው ኢት ቬሪ ዌል' (በደንብ ታውቀዋለህ)፤ ይሄ በአደባባይ እየተሰራ ያለ ሥራ ስለሆነ። ነገሮች እየጠሩ ሲሄዱ መረጃዎችን አጠናክረን ለእናንተ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሚድያዎችም መረጃ እንሰጣለን።

ቢቢሲ፦ ተመሳሳይ በሆነ መልኩ መተማ ውስጥ ያጋጠመ ችግር አለ። ለምሳሌ የቅማንት እና የትግራይ ተወላጆች ላይ ጥቃት ተፈፅሟል የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ነው። ስለዚህስ ያለዎት መረጃ አለ?

ጄነራል አሳምነው፦ እውነት ነው። ይሄ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ቦታዎችም ቤቶች ተቃጥለዋል። የመንግሥት ንብረት ተቃጥሏል፤ የግል ድርጅቶችም ተቃጥለዋል። አሁንም ተልዕኮ ያላቸው ግን ደግሞ ሕብረተቡን የማይወክሉ ሰዎች መተማና ሌሎች አካባቢዎች ችግር ፈጥረዋል። ይሄ እውነት ነው።

ሆኖም ግን ሰዉ ከዚህ በፊት አንዳንድ ችግሮች ደርሰውበት ስለነበር እነዚህ ኃይሎች ቢጋጩ የሚደርሰውን በመስጋት እየለቀቀ ካምፕ (ማዕከል) ውስጥ ይገባል፤ ወደውጭም ይሄዳል፤ ሌሎችም አማራጮች ይጠቀማል። ይሄ አጋጣሚውን መጠቀም የፈለጉ ዘራፊዎች የወሰዱት እርምጃ ካልሆነ በቀር ይህ ሕዝብ ውጣልኝ፤ ልቀቅልኝ የሚል ሕዝብም አይደለም።

በማንነታቸው ጉዳት እንዳይደርስባቸው ከለላ እየሰጠ ያለ ሕዝብ ነው። ግጭቱ እውነት ቢሆንም መንስዔውና አካሄዱ ግን አሁን ባልኩት መንገድ ነው። ከሕብረተሰቡ ጋር የመነጋገር ዕድል ገጥሞን ነበር፤ አንድም ሕዝብ እንዲወጣ አይፈልግም። የነሱም ቤተሰቦች ሌላ ቦታ ይገኛሉ። እንዲህ ዓይነት ነገር በሃገራችን እንዲፈጠር አይፈልጉም።

ቢቢሲ፦ ያነጋገርናቸው እና ከዚህ አካባቢ ተፈናቅለናል የሚሉ ሰዎች ሕዝቡን ሳይሆን የሚወቅሱት የአማራ ክልል ታጣቂዎችን ነው።

ጄነራል አሳምነው፦ 'ኔቨር'። ይሄ ከእውነት የራቀ ነው። የአማራ ታጣቂዎች የሉም። ምናልባት በተለያየ ወንጀል ወደበረሃ ወጥተው፤ ወደ ውጭ ወጥተው መጥፎ ድርጊት የሚፈፅሙ ወገኖች አሉ። 'ባይዘወይ' (በነገራችን ላይ) አካባቢው የግብርና ኢንቨስትመንት በስፋት የሚከወንበት በመሆኑ ሰዎች ከየትኛው የሃገሪቱ ክፍሎች መጥተው ይሰራሉ።

ወቅቱ ደግሞ ሰሊጥ የሚታጨድበትና የሚወቃበት ነው። እና እንዲህ ዓይነት ችግር ሲፈጠር አጋጣሚውን ተጠቅመው ለመውረርና ለመዝረፍ ሙከራ ያደርጋሉ። 'ኤክሰፕሽናል' (ያልተለመደ) ሁኔታ አይደለም። እዚያ አካባቢ ያለው ሁኔታ የፈጠረው ነው። እንጂ የአማራ ክልል ታጣቂ የፈጠረው አይደለም። እንዴት ተደርጎ ይታሰባል? እምልህ ጥያቄውም ይከብዳል፤ አይደለም ድርጊቱ።

ቢቢሲ፦ መተማ ውስጥ ግጭት ከሆነ የተፈጠረው፤ ማን ከማን ጋር ነው የተጋጨው? ጥቃትም ከሆነ ማን አጥቂ? ማንስ ነው ተጠቂ?

ጄነራል አሳምነው፦ አሁን እዚያ አካባቢ ልዩ ኃይል አለ፤ መከላከያ አለ፤ ፖሊስ አለ፤ በአካባቢ ደረጃ የተደራጁ ሚሊሻዎች አሉ። እነሱ የሚችሉትን ያህል እየተከላከሉ ነው። እያገዙት ነው ሕዝቡን። ግን አንድ ቦታ እንትን ስትል እኛ የምንሸፍነው እና እንቅስቃሴው ይለያያል።

በእንዲህ ዓይነት አጋጣሚ የሚፈጠር ካልሆነ በስተቀር ማን ከማን ጋር ነው ልትለው አትችልም። ይሄ ከተራ የወሮበላ ድርጊት ያለፈ ሌላ ሁኔታ ይኖረዋል ብዬ አላምንም። እና ስለሰጠኸኝ ዕድል በጣም አመሰግናለሁ።

ቢቢሲ፦ አንድ የመጨረሻ ጥያቄ ጀኔራል. . . ከመተማው ክስተት በኋላ የትግራይ ክልል መንግሥት መግለጫ አውጥቶ ነበር። መግለጫው ላይ 'አንዳንድ የአማራ ክልል ባለሥልጣናትም እጃቸውን አስገብተዋል' ይላል. . .

ጄነራል አሳምነው፦ ይሄ. . . በፍፁም ስህተት ነው። እንደተለመደው የሚድያ ሽፋን እውነት ነው፤ ስህተት ነው ለማለት አይደለም። በአካባቢው የተንቀሳቀሰ የመንግሥት አካል የለም። ካለም እኔ ነኝ የተንቀሳቀስኩት። እኔ ደግሞ ለአካባቢውና ለሃላፊነቱ እንግዳ ነኝ። ስለዚህ ከአካባቢው ሰዎች ጋር ለመተዋወቅ፤ ችግሩን አነጋግሮ ለመፍታት ነው የሄድኩት። ይሄን 'ኦፊሻሊ' እነሱም ያውቁታል።

የኔና የሕዝብ ግንኙነት ደግሞ ይታወቃል። እና 'አንዳንድ' የሚሉት እንዳው ለማለት ካልሆነ በቀር እውነታው ይህ ነው። ሶሳይቲው (ማሕበረሰቡ) መረጃ አይደርሰውም ተብሎ ስለሚታሰብ እውነት ለማስመሰል፤ እሳቱን እያቃጠሉ ያሉት እነሱ ሆነው እያለ፤ መልሰው ደግሞ ይህን መግለጫ ይሰጣሉ።

የክህደት ፕሮፓጋንዳቸው ሁሉ እንደቀጠለ ነው ያለው፤ እነዚህ ሰዎች አልደከሙም። እና እነሱ ያወጡት መረጃ እውነት አይደለም። የሄድኩትም እኔ ነኝ፤ ያነጋገርኩትም እኔ ነኝ። እኔ ደግሞ የዛ ምንጭ ልሆን አልችልም። ምክንያቱም ችግር ውስጥ ያሉ ሰዎችን ከመርዳት ውጭ ያለፈ ራዕይ የለኝም እኔ። ይሄንን ጥያቄ እንደው እንዲሁ በሌላ መንገድ ብታየው ጥሩ ነው።

ተያያዥ ርዕሶች