ዋትስ አፕ ላይ በተነዛ ሐሰተኛ ወሬ ምክንያት ተቃጥለው የተገደሉት የሜክሲኮ ዜጎች

ሪካርዶና አልቤርቶ ሲቃጠሉ የነበረውን ሁኔታ ለማስቀረት ሰዎች በተንቀሳቃሽ ስልካቸው ሲቀርፁ Image copyright Enfoque

በሜክሲኮ አንዲት ትንሽ ከተማ ልጆችን ስለሚያግቱ ግለሰቦች ዋትስአፕ ላይ ወሬ ተነዛ። ወሬው ውሸት ነበር፣ ነገር ግን መንጋው ፍርድ ሰጠ። ሁለቱን ሰዎች ከነህይወታቸው እሳት ለኩሶ አቃጠላቸው።

ማንም የወሬውን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ አልሞከረም።

በነሐሴ ወር በአንዱ ቀን ሜክሲኮ የምትገኘው ትንሽ መንደር በሰልፈኞች ጩኸት ትናጥ ጀመር። ሰልፈኞቹ በአካባቢው ፖሊስ ጣቢያ በራፍ ላይ ተሰብስበዋል። በየደቂቃው ቁጥራቸው እየጨመረ ይሄዳል።

የዓመቱ ሐሰተኛ ዜናዎች በአፍሪካ

አይሸወዱ፡ እውነቱን ከሐሰት ይለዩ

'ሃሰተኛ ዜና '፡ የኢትዮጵያ የማሕበራዊ ሚድያ ተጠቃሚዎች ስጋት?

ፖሊስ በሌላ ጥፋት በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ሁለት ሰዎች ልጆችን በማገት አለመጠርጠራቸውን ለማስረዳት ቢሞክርም ሰሚ ጆሮ አልነበረም።

ፖሊስ ጣቢያው ውስጥ የ21 ዓመቱ ሪካርዶ ፍሎሬስ እና አጎቱ አልቤርቶ ፍሎሬስ ተቀምጠዋል።

ሪካርዶ በሌላ ከተማ የህግ ትምህርቱን የሚከታተል ወጣት ነው። አጎቱም ቢሆን መኖሪያው ሌላ ከተማ ነው። ሁለቱም ዘመድ ጥየቃ ብለው ነው ወደዚች ከተማ የመጡት። ትናንትና ደግሞ እቃ ለመሸማመት ብለው ገበያ ወጥተው ነበር።

ከፖሊስ ጣቢያው ውጭ የተሰበሰበው የሰው ጎርፍ ግን በዋትስ አፕ በሚንሸራሸረው መልዕክት ተወስዷል። "ወደ ከተማችን የህፃናት አጋቾች ገብተዋል ሁላችሁም ተጠንቀቁ" ይላል መልዕክቱ።

አክሎም "እነዚህ የህፃናት አጋቾች የአካል ውስጥን በመክፈት የተለያዩ የአካል ክፍሎችን ይወስዳሉ። ሰሞኑን እድሜያቸው 4፣ 8ና 14 የሆኑ ህፃናት ከጠፉ በኋላ ሞተው የተገኙ ሲሆን አካላቸው ተከፍቶ የውስጥ አካላቸው እንደተሰረቀ ማወቅ ተችሏል። የሆድ እቃቸው ባዶ ነበር።"

የሪካርዶ እና አልቤርቶ በአካባቢው በሚገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አካባቢ መታየት ወሬው ክንፍ አውጥቶ እንዲበርና በእያንዳንዱ የመንደሯ ነዋሪ ልብ ውስጥ ፍርሃት እንዲነግስ አድርጓል።

Image copyright Brett Gundlock

ወደ ፖሊስ ጣቢያ የተመመው አብዛኛው ሰው የፍራንሲስኮ ማርቴንዝን መልዕክት ተከትሎ ነው። እንደ ፖሊስ መረጃ ከሆነ ይህ በከተማዋ ለረጅም ጊዜ የኖረ ግለሰብ ይህንን መረጃ በፌስ ቡክና በዋትስ አፕ ሲያሰራጩ ከነበሩት ግለሰቦች መካከል አንዱ ነው።

ሪካርዶና አልቤርቶን ከመወንጀል አልፎ በፖሊስ ጣቢያ ተገኝቶ በስልኩ የፌስቡክ የቀጥታ ስርጭት ጀመረ።

በቀጥታ ለሚከታተሉትም የከተማችን ነዋሪዎች "ኑና ድጋፋችሁን አሳዩ፤ እመኑኝ ህፃናትን የሚሰርቁት ሌቦች እዚህ ናቸው" በማለት ቀሰቀሰ።

ፍራንሲስኮ ይህንን ሲያደርግ ማኑኤል የሚባል ግለሰብ ፖሊስ ጣቢያው አካባቢ የሚገኝ ቤተክርስቲያን ደወል ቤት ላይ በመውጣት ሪካርዶና አልቤርቶን ፖሊስ ሊለቃቸው ነው በማለት ደወል በመደወል የአካባቢውን ህዝብ ቀሰቀሰ።

ሶስተኛ ሰው በድምፅ ማጉያ ነዳጅ መግዣ ገንዘብ እናዋጣ በማለት እየቀሰቀሰ ፖሊስ ጣቢያውን የከበባትን ወፈ ሰማይ ሰው እየጠየቀ መሰብሰብ ጀመረ።

ከዚህ በኋላ ፖሊስ ጣቢያውን የከበባት ሰው በኋይል ወደ ውስጥ ገብቶ ሪካርዶንና አልቤርቶን እየጎተተ አወጣቸው። ሁሉም በቻለው ሁሉ ይቀጠቅጣቸው ገባ። ሌላው ደግሞ ይህንን በተንቀሳቃሽ ስልኩ ለማስቀረት መቅረፅ ጀመረ።

በኋላም ነዳጅ አርከፍክፈውባቸው ክብሪት ጫሩ።

የአይን እማኞች እንደመሰከሩት ከመቃጠላቸው በፊት ሪካርዶ በድብደባው ብዛት ሞቶ ነበር። አልቤርቶ ግን ከነህይወቱ ነው የተቃጠለው።

ተቃጥሎ የከሰለው የሰዎቹ ሬሳ ከሌላ ከተማ የመንግስት ሰዎች እስኪመጡ ድረስ መንገዱ ላይ ነበር። የቃጠሎውም ሽታም ከአየሩ ላይ አልጠፋም። የሪካርዶ አያት የሟቾቹን ማንነት መለየት እንዲችሉ ተጠርተው በስፍራው ሲደርሱ የተሰበሰበው ሰው ተበትኖ ጥቂት ግለሰቦች ብቻ ናቸው የቀሩት።

የሪካርዶ እናት የተሻለ ህይወት ፍለጋ አሜሪካ ከገባች ሰነባብታለች። ልጇ ህፃናት ስርቆት ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደዋለ በከተማዋ የሚገኙ ጓደኞቿ ልጅሽ ታሰረ ብለው መረጃ በፌስ ቡክ ገጿ ላይ የላኩላት ወዲያው ነበር።

መልዕክቱ ከአንድ ሰው ብቻ የመጣ አልነበረም። ከተለያየ ሰዎች እንጂ። በኋላ ላይም በቀጥታ የፌስ ቡክ ስርጭት ልጇ ሲደበደብ ኋላም ላይ ነዳጅ አርከፍክፈው ሲያቃጥሉት አየች። "እባካችሁ አትደብድቡት አትግደሉት ወንጀለኛ አይደለም" ስትል መልዕክት ላከች። ማንም የሚሰማት ግን አልነበረም።

መልካም ወሬን ያቀብላት የነበረው ማህበራዊ ሚዲያ የልጇን ሞት በቀጥታ አሳያት።

እንደ አካባቢው ባለስልጣናት ከሆነ 5 ሰዎች ለወንጀል በማነሳሳት 4 ደግሞ በግድያው በቀጥታ በመሳተፍ ተከሰው ታስረዋል። ነገር ግን ሌላ 2 ቀስቃሾችና 4 በግድያው የተሳተፉ ግለሰቦች አምልጠዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ