በሃሰተኛ ዜናዎች "የሞቱ" የኪነጥበብ ሰዎች-ገነት ንጋቱ፣ ጋሽ አበራ ሞላ እና አምለሰት ሙጩ

ከግራ ወደቀኝ ስለሽ ደምሴ፣ ጌታቸው ማንጉዳይ እና ገነት ንጋቱ Image copyright ETMDB.COM
አጭር የምስል መግለጫ ከግራ ወደቀኝ ስለሽ ደምሴ፣ ጌታቸው ማንጉዳይ እና ገነት ንጋቱ

በግለሰብም ሆነ በሀሰተኛ የድርጅት ማህበራዊ ሚዲያ ገፆች የሚሰራጩ ሀሰተኛ ዜናዎች የበርካቶችን ቤት አንኳክተዋል። በተለይ የኪነጥበብ ባለሙያዎች እንዲሁም ታዋቂ ፖለቲከኞች በሀሰተኛ ገፆች ሰበር ዜና ስር ሕይወታቸው ማለፉ ተዘግቧል።

እንደነዚህ ያሉ ዜናዎች ብዙዎችን አስደንግጠዋል።

ህልፈታቸው በሃሰተኛ ዜናዎች ከታወጀ መካከል አርቲስት ስለሺ ደምሴን (ጋሽ አበራ ሞላ)ና አርቲስት ገነት ንጋቱን ማንሳት ይቻላል።

የ7 ዓመቷ ህጻን ግድያ፡ ''ከልክ ያለፈ ቅጣት የልጄን ህይወት አሳጣኝ''

በሞያሌ በተከሰተ ግጭት የ19 ሰዎች ህይወት አለፈ

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር በጋዛ ተኩስ አቁም ውሳኔ ምክንያት ለቀቁ

አርቲስት ስለሹ ደምሴ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ባይሆንም በተለያዩ ግለሰቦች ላይ ያልሆነው ሆነ፣ ያልተፈጠረው ተፈጠረ፣ ያላጋጠመው አጋጠመ፣ ያልተደረገው ተደረገ እየተባሉ የሚሰራጩ ሃሰተኛ ወሬዎችን ከሰው ከሰው እንደሚሰማ ይናገራል።

ከዓመታት በፊት ስለሺ ደምሴ ሞቷል የሚል ሃሰተኛ ዜና ተሰራጨ፤ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችም ተቀባበሉት። እርሱ ግን የሚዲያው ተጠቃሚ ባለመሆኑ ቶሎ ጆሮው አልደረሰም ነበር፤

እንደ አጋጣሚ አንድ ቦታ ቁጭ ብሎ ሳለ አንድ ወዳጁ ይመጣና " ሞተሃል ተብሎ አልነበረም እንዴ?" ሲል እየሳቀ ይጠይቀዋል።

ለማህበራዊ ሚዲያ ትኩረት ሰጥቶ እንደማያውቅ የሚናገረው ስለሺ ደምሴ "ታዲያ መሞትማ አይቀርም፤ እኔ አንደውም ብዙ ጊዜ ነው የሞትኩት፤ በየቀኑ አይደል እንዴ የምሞተው?" ብሎ በቀልድ የታጀበ ምላሽ እንደሰጠው ያስታውሳል።

ይህንን ዜና ተከትሎ በቤተሰቡ ላይ የደረሰው ተፅዕኖ ምን ነበር ስንል የጠየቅነው አርቲስቱ "እንኳንስ እንዲህ አይነት አሉባልታዎችን ይቅርና ትክክለኛ ዜናዎችን ቁጭ ብሎ የሚሰሙ ሰዎች ቁጥራቸው ብዙ አይደለም" ሲል ይመልሳል።

በርካታ ሰዎችም ሳይሞቱ ሞቱ እየተባለ ይናፈሳል ይህም የተለመደ በመሆኑ ትኩረት አይሰጠውም።

በአብዛኛው በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ መረጃዎች እንደ እውነት አይወሰዱም የሚለው አርቲስት ስለሺ አጋጣሚ ሆኖ በተነዛው ሀሰተኛ ወሬ ሳቢያ ቤተሰቦቹም ድንጋጤ እንዳልተፈጠረባቸው ይናገራል።

እንዲህ ዓይነት መረጃዎችን የሚያስተላልፉትም ሰሚ አናጣም፣ ተከታይ አለን፤ ወሬ የሚፈልግ አለ በሚል እንደሆነ ያምናል። " ችግሩ ያለው ከፀሐፊዎቹ ሳይሆን ወሬያቸውን ሳያጣራ እህ ብሎ ከሚሰማው ነው" የሚለው አርቲስቱ ደግሞ ይባስ ብሎ ያላጣሩትን ወሬ ለሌላ ሰው ማቀበላቸው አግራሞት ይጭርበታል።

ተከታዮችና ሰሚዎች እንዲህ ዓይነት የሚነዙ አሉቧልታዎችን ባይሰሙ፣ ባይከተሉና ባያሰራጩ ፀሐፊዎቹም ይመክናሉ ሲል ምክንያቱን ያስቀምጣል።

ይሁን እንጂ ቀስ በቀስ ሰው እየተገነዘበው ሲመጣ ይህ እንደሚለወጥ ተስፋ ያደርጋል።

እንዲህ አይነት ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ሆነ ብሎ ትኩረት ሰጥቶ መከታተሉና ማራገቡ ስራ ማጣት፤ በጊዜና በገንዘብ ላይ መቀለድ በመሆኑ እውነተኛና ሃሰተኛ መረጃን ለመለየት ማጣራት እንደሚያስፈልግም ያስረዳል።

አርቲስት ገነት ንጋቱም የዚሁ ሐሰተኛ መረጃ ተጎጂ ናት፤ በአንድ ወቅት በህመም ላይ በነበረችበት ጊዜ አርፋለች ተብሎ ሀሰተኛ መረጃ ተሰራጭቶ ነበር።

"ህመም ላይ እያለሽ መዳን በምትፈልጊበት ጊዜ እንዲህ ዓይነት ዜና መስማቱ ያማል" ትላለች።

ሀሰተኛ ዜናውን የሰማችው መረጃው የደረሳቸው ዘመድ አዝማዶች መርዶውን ሰምተው እያለቀሱ ወደ ቤት ሲገቡ ነው፤ ከዚያም በኋላ ስልክ እየደወሉ ድምጿን ሲሰሙ ይረጋጉ አንደነበር ታስታውሳለች።

በተለይ እናቷ በተሰራጨው የሀሰት ዜና ተንሰቅስቀው እንዳለቀሱ የምትረሳው አይደለም። "እንደው ምን ብታደርጊያቸው ነው?" ሲሉ እንደጠየቋትም አትዘነጋውም።

አንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ተመሳሳይ መረጃዎች ይናፈሱ ነበር የምትለው ገነት፤ ለህክምና ወደ ህንድ አገር ስትሄድም "አውሮፕላን ላይ አረፈች ተብሎ" መወራቱን ትናገራለች።

ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት ሃሰተኛ ዜናን የሚፈጥሩ ሰዎች ምን አይነት አስተሳሰብና አመለካከት እንዳላቸው የዘወትር ጥያቄዋ ነው።

ስለ ቴዎድሮስ ካሰሁንና ባለቤቱ አምለሰት ሙጨ ምን ተባለ?

የድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ሥራ አስኪያጅ ጌታቸው ማንጉዳይም "ሰው ለምን ሰውን በሀሰት ይገላል? ምን ጥቅም ያገኛል" በማለት ከገነት ጋር ተመሳሳይ ጥያቄ ይሰነዝራል።

ሀሰተኛ መረጃ ሲሰራጭ ብዙዎችን ቢያደናግጥም፤ መረጃውን የሚያስተባብል ምላሽ አይሰጥም። ሀሰተኛ ዜና የሚያሰራጩ ሰዎች፤ ትኩረት ማግኘት ቀዳሚ ግባቸው በመሆኑ፤ መረባቸው ውስጥ ላለመውደቅ ጆሮ አለመስጠትን ይመርጣል።

"የተቆፈረ ጉድጓድ አለ፤ ወጥመድ ይዘጋጅልሀል። ለምን ወደጉድጓድ ትገባለህ" ሲል መልስ መስጠት እንደማያሻ ያስረዳል።

የምዕራቡ ዓለም የኪነጥበብ ሰዎች እያንዳንዱን እንቅስቃሴያቸውን ማኀበራዊ ሚዲያ ላይ ያጋራሉ። የኢትዮጵያ እውነታ ከዚህ ይለያል።

ጌታቸው እንደሚለው ሁኔታው እንደየሰው ባህሪ ይለያያል። "በኛ ባህል እዚህ ገባሁ እዚህ ወጣሁ ማለት አይደለም። ይህ የምእራባውያን ባህል ነው" ይላል።

ፈጠራ ሥራ ላይ ያለ ሰው አእምሮው መረጋጋት አለበት የሚለው ጌታቸው፤ "ለሀሰተኛ ዜና ጆሮ ክፍት ካደረጉ ፈጣሪ መሆን አይቻልም" ሲል ያክላል።

በቅርቡ የኢትዮጵያና ኤርትራ የወዳጅነት ሩጫ በባህርዳር እንደተካሄደና በስፍራው ላይ ቦንብ ፈንድቶ በርካቶች እንደሞቱ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ስም በተከፈተ ሐሰተኛ የፌስ ቡክ ገፅ ላይ ተዘግቦ ነበር። በዚህ ገፅ ላይም በፍንዳታው ቴዲ አፍሮ መጎዳቱንና ባለቤቱ አምለሰት ሙጬም እንደሞተች ተወርቷል።

ጌታቸው "ብዙ ነገር ይወራል። እኛ አንሰማም። በራችን ዝግ ነው። ቴዲ አፍሮ ጥሩ ሥራ የሚያቀርበው ለዚህ ነው" ይላል።

"ለሀሰተኛ ዜና ትኩረት ከተሰጠ አንድ እርምጃም መሄድ አይቻልም" የሚለው ጌታቸው ሀሰተኛ ዜና ቢያስደነግጥም፤ ማኀበረሰቡ እውነተኛ መረጃን ከሀሰተኛ መለየት እንደሚችል ይተማመናል።

ተያያዥ ርዕሶች