እውን እንጀራ ሱስ የሚያስይዝ ንጥረ ነገር አዝሏል?

እንጀራ Image copyright AFP

አቶ ወንድወሰን ግርማ በቤልጂየም የትራንስፖርት ሳይንስ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ ነው። ከዚያ ቀደም ብሎ ለሁለት ዓመትም ለሌላ ሁለተኛ ዲግሪ በኖርዌይ ቆይቷል።

"ያኔ ከአገር ስወጣ የመጀመርያዬ ስለነበር የእንጀራ አምሮቴ ከፍተኛ ነበር" ይላል።

እንደ አጋጣሚ ሆኖ ወንድወሰን የሚኖርበት ሰፈር ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ቅርብ ነበር።

ይህ ሁኔታ ሀበሾች በሰበብ አስባቡ ለመሰባሰብ ምክንያት ሆኗቸዋል "የእንጀራ አምሮታችንን በዚያው እንወጣው ነበር" ይላል።

ኖርዌይ ውስጥ ቤተሰብ መሥርተው የሚኖሩ ብዙ ኢትዮጵያውያን መኖራቸው ሌላው መልካም አጋጣሚ ነው።

"እነሱ እንጀራ ጋግረውና የተለያዩ ምግቦችን ሠርተው ይዘው ይመጣሉ" ይላል።

እንደ ወንድወሰን ዓይነቱ ከአገሩ የራቀ የእንጀራ ጽኑ ወዳጅ ቢያንስ በዓላትን ጠብቆ እንጀራን የማጣጣም ዕድል አለው። ሐበሾች በሚበዙባቸው የአውሮፓ ከተሞች እዚህም እዚያም ብሎ አምሮቱን መወጣት አያቅትም።

ከዚያ በብዙ ማይል የራቁትስ? ለዚህ ያልታደሉስ?

ጤፍን ሰዳ የምታሳድደው ኢትዮጵያ

ጤፍ ሃገሩ የት ነው? ደቡብ አፍሪካ? አውስትራሊያ? . . .

ረ ለመሆኑ እንጀራ ሱስ ያስይዛል?

ወንድወሰን ምንም እንኳ የእንጀራ አፍቃሪ ቢሆንም ሱስ ነው ብሎ ለመደምደም ይቸገራል።

ሰዎች በአቅራቢያቸው ምንም ዓይነት እንጀራ ማግኘት እንደማይችሉ ሲያውቁ ያገኙትን ለመመገብ አይቸገሩም ብሎ ያምናል። ነገሩ ከአስተሳሰብ ጋር እንደሚያያዝም ይገምታል።

ይህንኑ ጥያቄ ወደ ባለሙያ ይዘነው ብንሄድስ?

አቶ አብነት ተክሌ የሥነ ምግብ ባለሙያ ናቸው። እንደሳቸው ሐሳብ ጉዳዩ ደንበኛ ጥናትን የሚፈልግ ነው።

"እንጀራ ሱስ ያስይዛል ወይስ አያስይዝም የሚለውን ጥያቄ ጥርት ባለ መልኩ የሚመልስ ጥናት እኔ እስካሁን አላገኘሁም'' ይላሉ።

በመጀመሪያ ግን ሱስ ምንድነው የሚለውን ጥያቄ ይመልሳሉ።

እንደ ባለሙያው አስተያየት ሱስ በሁለት ደረጃዎች የሚከፈል ሲሆን፤ አንደኛው ሥነ አእምሯዊ ሆኖ የአንድን ጣዕም ከጥሩ ስሜት ጋር ከማያያዝ የሚመነጭ ነው።

ሁለተኛው የሱስ ዓይነት ደግሞ 'ፊዚዮሎጂካል' የሚባለውና ሰውነታችን የሆነን ንጥረ ነገር ሲለምድ የሚጠይቀን ነው፤ በብዛት የተለመደው የሱስ ዓይነትም ይኸው ነው።

"የእንጀራን ጉዳይ ሥነ-አእምሯዊ ከሚባለው የሱስ ዓይነት አንጻር ስንመለከተው..." ይላሉ አቶ አብነት ከሕይወታችን ጋር ያለው ቁርኝትን ሲያስረዱ፤ "...ከልጅነታችን ጀምሮ የለመድነው ጣዕም በመሆኑ ሥነ-አዕምሯዊ ሱስ ሊኖረው ይችላል" ይህም የሚሆነው በቀን ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ ስለምንመገበው ነው።

"እንጀራን ደጋግመን ከመመገባችን የተነሳ ውስጥ ውስጡን ያንን ጣዕም የመፈለግና ስናገኘው ደግሞ የመደሰት ስሜቶች ይከሰታሉ" ይላሉ።

ሥነ አእምሯዊ ገጽታውን በዚህ መልኩ የተነተኑት አቶ አብነት 'ፊዚዮሎጂካዊ' ሱስነቱን እንደሚከተለው ይገልጹታል።

"እንጀራ በውስጡ ኃይልና ጉልበት ሰጪ ንጥረነገሮች እንዲሁም አሲዶች አሉት። በእርሾ እንደመሠራቱ ግበአቶቹ ሲብላሉ አሲድ ይፈጠርና እንጀራውን ለጎምዛዛ የቀረበ ጣዕም ይሰጠዋል።"

Image copyright The Washington Post

ከዚህ በተጨማሪ እንጀራ በውስጡ ለሰውነት አስፈላጊ የሆኑ ፕሮቲንና ካርቦሃይድሬት ያለው ሲሆን፤ ሰውነታችን እነዚህን ንጥረነገሮች ለኃይልና ጉልበትም ይሁን ለሰውነት ግንባታ ይጠቀምበታል፤ ልክ እንደማንኛውም ምግብ እንጀራን ስንበላ የመደሰትና የመርካት ስሜት ይፈጠራል" ባይ ናቸው።

ልጆችዎ ጤናማ ምግብ እንዲመገቡ ማድረጊያ መላዎች

አትክልት ብቻ ስለሚመገቡ ሰዎች ሊያውቋቸው የሚገቡ ነገሮች

ነገር ግን በእንጀራ ውስጥ ካለው ከፍተኛ የአሲድ እንዲሁም የአልኮል ክምችት አንጻር ከሌሎች ምግቦች በተሻለ እርካታን ሊሰጠን ይችላል። ይህ ደግሞ ብዙ ጊዜ ሰዎች "እንጀራ ሱስ ያስይዛል" የሚል ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል ይላሉ ባለሙያው፤ አቶ አብነት።

ለእንጀራ የሚከፈል ዋጋ

በአሁኑ ሰዓት ኑሮዉን ቤልጂየም ያደረገው ወንድወሰን አሁን የሚኖርበት አካባቢ ለእንጀራ ቅርብ እንዳልሆነ ይገልጻል። ደረቅ እንጀራ ፍለጋ ከ1፡30 እስከ 2፡00 ሰዓት የሚፈጅ የባቡር ጉዞን ያደርጋል።

እንጀራው ሉቨን ከሚባል ቦታ የሚመጣ ሲሆን ቀደም ብሎ ስልክ በመደወል ቀጠሮ ማስያዝ የግድ ነው። ቀድሞ መደወሉ ያስፈለገው ቀድመው ላዘዙ ብቻ ስለሚጋገር ነው።

ክፋቱ ከዚህ ሁሉ እንክርት በኋላ የሚገኘው እንጀራ አንጀት አርስ አለመሆኑ ነው፤ "በመጠኑ ሰሐን የሚያክልና በጣም ትንሽ ነው። ጣዕሙ ደግሞ ኢትዮጵያ ካለው ጋር በጭራሽ አይወዳደርም" በማለት ምሬቱን ይገልፃል።

እንዲያውም ወንድወሰን ''አእምሯችንን አሳምነን እንጀራ ነው ብለን እንበላዋለን እንጂ የጤፍ ስለመሆኑ በመጠራጠር ነገሩ እንጀራ ነው ለማለት ይከብደኛል" ይላል

ጥርጣሬው ያለምክንያት አልተፈጠረም የሚለው ወንድወሰም የመለጠጥና መረር የማለት ባህሪ በመሆኑ ከጤፍ ይልቅ ለገብስ የቀረበ መሆኑን ይናገራል።

"የማማረጥ ዕድል በሌለበት አቃቂር ማውጣት ቅንጦት ነው። ይህን ሁሉ እያወቅህ 'እንጀራ እየበላሁ ነው' የሚለው ነገር በራሱ ከፍተኛ የአእምሮ እርካታን ያጎናጽፍሃል" የሚለው።

የሆነስ ሆነና እንጀራ ከሱስ ይመደባል?

የሥነ ምግብ ባለሙያው ቀጥተኛ መልስ የላቸውም። ነገር ግን እንጀራ እንደ ኒኮቲን አልያም አልኮል ያሉ ሱስ አስያዥ ንጥረ ነገሮች፣ መጠጦች ወይም ተክሎች ዓይነት ሱስ የማስያዝ አቅም የሌልውና፤ ደካማ እንደሆነም ይገልፃሉ።

ምናልባት እንጀራ ሲሠራ ሊጡ ከእርሾው እስኪብላላ ድረስ ሦስት ቀን ስለሚፈጅበት የአሲድ መጠኑ ከሌሎች አሲድ ያላቸው ምግቦች ከፍ ያለ ሊሆን ይችላል የሚሉት ባለሙያው የአሲድ መጠኑ ከፍ ማለቱና ጎምዘዝ ያለ ጣዕም መኖሩ መሠረታዊ ባይባልም መጠነኛ የሆነ ሱስ ሊያመጣ ይችላል ባይ ናቸው።

እንጀራን የሚመገቡ ሰዎች ላይ ከሚከሰተው ፊዚዮሎጂካል ሱስ ይልቅ የሥነ አእምሯዊው ሱሱ የበለጠ ኃይል እንዳለውም አቶ አብነት ያስባሉ።

"ብዙ ጊዜ ሰዎች እንጀራ ሳልበላ አንድ ቀን መቆየት አልችልም የሚሉት ሰውነታቸው እንጀራ ፈልጎ ሳይሆን ከልጅነታቸው ጀምሮ ያስለመዱት ነገር ስለሆነ ነው። ይህም ሱሱ ከአካላዊነቱ ይልቅ ሥነ አእምሯዊ ስለመሆኑ ሌላ አስረጅ እንደሆነም ይናገራሉ።

እንጀራ በይን የዞረ 'ለት

ወንድወሰን በድምሩ ለአራት ዓመታት ባሕር ማዶ በቆየባቸው ጊዜያት የእንጀራ ነገር በዓይኑ ይዞራል። በኖርዌይ ቆይታው ከዕለታት በአንዱ የእጀራ ሱሱ አየለበት፤ በአቅራቢያው በቀላሉ ማግኘት የሚታሰብ አልነበረም። ለምን ራሴ አልጋግርም የሚል ሐሳብ ብልጭ አለለት።

ጤፍን የሚተካ ገብስ አመጣ፤ የገብሱ ዱቄት ውስጥ ጨው ጨመረ፤ በሞቀ ውሃ አቀላቀለው፤ ከገብሱ ዱቄት ውስጥ የገብሱን ገለባ ማጥለልና ከአራት እስከ አምስት ቀናት ድረስ በደንብ እስኪብላላ መጠበቅ ነበረበት፤ አዲስ መጥበሻ በመግዛት በመጥበሻው ውህዱን ጋገረው።

Image copyright ወንድወሰን ግርማ
አጭር የምስል መግለጫ ወንድወሰን የጋገረው የገብስ እንጀራ

ውጤቱ እንደ አዲስ ሳይንሳዊ ግኝት አጓጊ ነበር።

የአገልግል ምግብ አምሮዎታል?

"ለመጀመሪያ ጊዜ የጋገርኩት እንጀራ ምንም የእንጀራ መልክ የሌለውና ከእንጀራነት ይልቅ የላስቲክ ባሕሪን የተላበሰ ነበር ይላል" ከሳቅ ጋር እየታገለ።

"ማባያ ይሁነኝ ብዬ ያዘጋጀሁትን ወጥ ስጨምርበት "እንጀራዬ" መያዝ እንኳ ተሳነው" ሲል ጀምሮት የነበረውን ሳቅ ይጨርሳል።

ወንድወሰንን ያየ እንጀራ ሱስ አይደለም ማለት ይቻለዋል?