በኢትዮጵያ የሚገኙ ቤተ እስራኤላውያን ወደ "ተስፋይቱ ምድር" ፅዮን ውሰዱን ተማፅኖ

በእስራኤል የሚገኙ ቤተ እስራኤላውያን Image copyright MENAHEM KAHANA

ሰሞኑን በኢትዮጵያ የሚገኙ ቤተ እስራኤላውያን ላምበረት በሚገኘው ምኩራባቸው የእስራኤል መንግሥት የገባልን ቃል አላከበረም በሚል የፀሎት አድማ አካሂደዋል።

ወደ እስራኤል እንዲመለሱ ከሶስት አመት በፊት የእስራኤል መንግሥት ቃል ቢገባም ቃሉ እንደታጠፈ ይናገራሉ።

ተቃውሞው በኢትዮጵያ ብቻ ውስጥ ሳይሆን በእስራኤል የሚገኙ ቤተ እስራኤላውያን የተቃውሞ ሰልፍ በማድረግ የእስራኤል መንግሥት ቃሉን እንዲያከብር እንደጠየቁ በአዲስ አበባ የሚገኙ ቤተ እስራኤላውያን ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ አንዱአለም ውብ ምህረት ለቢቢሲ ገልጿል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት በእስራኤል የሚገኙ ቤተ እስራኤላውያን ላይ የዘር ማምከን ወንጀል ተፈፅሟል በሚል አስተዳደሩ ከፍተኛ ውግዘት ደርሶበታል።

ዘርንም በመጨፍጨፍ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ወንጅለውታል። በተደጋጋሚም በቤተ እስራኤላዊያን ላይ የሚደርሱ ተደጋጋሚ የዘረኝነት ጥቃትን በመቃወም ከፍተኛ ተቃውሞዎችም ተካሂደዋል።

ምንም እንኳን እስራኤል እንደ ሁለተኛ ዜጋ ብታያቸውም አሁንም ሀገራችን እስራኤል ነው የሚሉ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ቤተ እስራኤላውያን ፅዮንን ሙጥኝ እንዳሉ ነው።

"በባቢሎን ወንዞች አጠገብ በዚያ ተቀመጥን፤ ፅዮንንም ባሰብናት ጊዜ አለቀስን" እንደሚለው ጥቅስ የፅዮን ማዕከልነትን መቼም እንደማይዘነጉ ይናገራሉ።

ለአስርት ዓመታትም ወደ እሥራኤል ለመሔድ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ 9146 ቤተ እስራኤላውያን ከሶስት ዓመታት በፊት የእስራኤል መንግሥት ሁሉንም እንደሚወስድ ቃል ቢገባም ቃሉን እንዳላከበረ ኢትዮጵያ ላሉ ቤተ እስራኤላውያን የሚደረጉት እንቅስቃሴዎች ኃላፊ አቶ ንጉሴ ዘመነ አለሙ ይናገራል።

እንዲህ የተጓጓተተበት ዋነኛው ምክንያት የእስራኤል መንግሥት በተደጋጋሚ የበጀት እጥረትን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ ውሳኔዎች እያስተላለፉ እንደሆነ ገልጿል። ከመጀመሪያው ውሳኔ በተቃርኖም የተቀሩትን ዘጠኝ ሺ ሰዎች አንድ ላይ ሳይሆን በተለያየ ጊዜ 1300ና አንድ ሺ ሰዎች እንደወሰዱ ተናግሯል።

"ይህ ውሳኔ ደግሞ ቤተሰብን ከሁለት የሚከፋፍል በመሆኑ መጀመሪያ የተወሰነውን ውሳኔ እንዲከበር እየጠየቅን ነው ያለነው" ይላል።

ከተለያየ ሀገር ለሚመጡ ይሁዲዎች የበረራ ወጪያቸውን የእስራኤል መንግሥት የሚሸፍን ሲሆን ከዚያም በተጨማሪ የቤት መግዣና ለአንድ አመት ያህል ሀገሪቱን እስኪለምዱ ድረስ የሚሰጥ ወርሃዊ የኪስ ገንዘብ ይሰጣቸዋል።

Image copyright JEROME DELAY

ለአቶ ንጉሴ ግን የበጀት እጥረት ነው ቢባልም አሳማኝ እንዳልሆነ ይናገራል። ለዚህም እንደ ምሳሌ የሚያነሳው ከሶስት አመታት በፊት የእስራኤል አዲስ ገቢዎች ሚኒስትር የተናገሩትን ነው።

የእስራኤል አዲስ ገቢዎች ቢሮ ትርፍ ብር በየዓመቱ በጀት እየተረፈ ሲመልስ እንጂ ተቸግሮ እንደማያውቅ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

"በጀት የሚለው ጉዳይ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች የሚሰሩ ኃላፊዎች ያመጡት ችግር እንጂ እውነት የበጀት እጥረት ነው ብየ አላምንም" ይላል።

በእስራኤል ታሪክም በተደጋጋሚ ከመቶ በላይ ኃገራት አዲስ ገቢዎች ሲመጡ የበጀት ችግር አጋጥሞኛል ብላ እስራኤል እንደማታውቅ ይናገራል።

ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ይሁዲዎች እንዲመለሱ በተወሰነበት ሰዓት ነው የበጀት ጥያቄ መነሳት የጀመረው አሁን እንደሆነ ጠቅሶ የዘረኝነትና የፖለቲካ ምክንያቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይጠቅሳል።

አቶ አንዱአለም በበኩሉ እንደ ምክንያትነት የሚያቀርበው እስራኤል በአፍሪካውያን ላይ ያላትን እይታ ነው።

"የቤንያሚን ኔታንያሁ መንግሥት አቅም አንሶት ሳይሆን ዘረኝነት ነው። ኢትዮጵያዊ እንዲሁም አፍሪካዊ በመሆናችን እንጂ ሀገሪቱ የኢኮኖሚ አቅም ችግር አላት ብለን አናምንም" ይላል።

ለዚህም ምላሽ በእስራኤል የሚገኙ ከ150 ሺ በላይ የሚገኙ ቤተ እስራኤላውያንም እያቀረቡት ያለውም ሀሳብ "ስንመርጥህ ቤተሰቦቻችንን ከኢትዮጵያ እንደምታመጣልን ቃል ስለገባህልን ነው" እንዳሉም አቶ አንዱአለም ለቢቢሲ ገልጿል።

ብዙዎች ለአስርት ዓመታት ከቤተሰቦቻቸው ተነጣጥለው እንደሚገኙ የሚናገሩት አቶ አንዱአለም እንደ ምሳሌም የሚያነሱት የራሳቸውን ቤተሰቦች ነው።

ከሰባ አመት በላይ ዕድሜ ያላቸው አባትና እናቱ ወደ እስራኤል የሄዱ ከ16 ዓመታት በፊት ሲሆን ሶስት ታናናሽ ወንድሞቹም አብረው ሄደዋል።

"ከቤተሰቦቻችን ጋር ኢሰብዓዊና ፍትሀዊ በሆነ ሁኔታ ተለያይተናል። ለምን እንደለያዩን አላውቅም፤ ለመኖር በሚከብድ ሁኔታ ላይ ነው ያለነው" ይላል

አባቱን በሰባት ዓመት ውስጥ አናግሯቸው የማያውቅ ሲሆን የተሰማውንም ለመግለፅ ቃላት ያንሰዋል "ህልውናውን ስቶ ሰው እያነሳ እየጣለው ድምፁን እንኳን ሰምቼ አላውቅም። ይህም በስነ ልቦናየ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ አሳድሮብኛል። ጥዋት ማታ ላየው የምፈልገው አባቴን ድምፁን እንኳን መስማት ሲያቅተኝ የሚሰማውን ስሜት መገመት ይቻላል" ይላል።

ከዚህም በተጨማሪ እናቱም በለቅሶና በሐዘን ላይ መሆናቸውም የአቶ አንዱአለም የሌት ተቀን ራስ ምታት የሆነበት ጉዳይ ነው። " እናቴ ሌት ተቀን በማልቀስ አይኗ ሁሉ ጎድጉዶ እንደ ሉሲ በአፅም አለች ማለት ይቻላል።" በማለት እናታቸው የደረሰባቸውን ጥልቅ ሀዘንም ይገልፃል።

በዚህም ምክንያትም በእስራኤል መንግሥት ላይ ምንም አይነት ተስፋ የለውም "ለእስራኤል መንግሥት ጥሩ አመለካከት የለኝም። በኛ ላይ ያደረሰው ጭካኔ ነው" ይላል

ከዚህም በተጨማሪ ቤተ እስራኤላውያን የእስራኤል ባለስልጣናት የፖለቲካ ፍጆታ ማስፈፀሚያ እንደሆኑም አቶ አንዱአለም ይሰማዋል። ለዚህም እንደምሳሌ የሚያነሳው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ተገኝተው ያደረጉትን ንግግር ነው።

"ከአፍሪካ የወሰድናቸውን ኢትዮጵያውያንን ከፍተኛ ስልጣን በመስጠት ላይ ነን፤ ከኛ ተማሩ" ማለታቸውን ገልፆ ይህ አባባል ግን ፍፁም ከእውነት የራቀ እንደሆነ ይናገራል።

በተቃራኒው አቶ አንዱአለም " " እኛ ሰው መስለን አንታያቸውም" ይላሉ።

Image copyright DEA / C. SAPPA

ለአስርት ዓመታትም እስራኤል እንሄዳለን በሚል ጥበቃ ብዙዎች ከገጠር ተሰደው አዲስ አበባ ላይ ኑሮን መቋቋም እንደከበዳቸው አቶ ንጉሴና አቶ አንዱአለም ይናገራሉ።

"ኑሮው በጣም ከባድ ነው፤ በእንግልትም ላይ ነው ያሉት ግን ወደ ፅዮን እንሔዳለን ብለው ነው ይህን ያህል መከራ እየከፈሉ ያሉት" ይላል አቶ ንጉስ

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ መልስ ይሰጡናል የሚል ተስፋ ቢኖራቸውም ጥያቄያቸው መልስ ካላገኘ ምን አይነት እርምጃ ይወስዱ ይሆን? አቶ ንጉሴ የሚለው አለው።

" ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁ ፅዮናዊ ናቸው፤ እንዲሁም በመላው አለም የሚገኙ ይሁዲዎችን ለመመለስ በጣም ከፍተኛ ጥረትም ያደርጋሉ" በሚል አቶ ንጉሴ ተስፋውን ገልጿል።

ምላሽ ካልተሰጣቸው በእስራኤል የሚገኙ ቤተ እስራኤላውያን በሚሰጡት መመሪያ እንደሚቀጥሉ ይናገራል።

የረሀብ አድማ አንዱ የተቃውሞ መንገድ ሊሆን እንደሚችል ጠቁሞ ከዚህም በተጨማሪ በእስራኤል የሚገኙ ቤተ እስራኤላውያን መፍትሔ ለማግኘት ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ወስደውታል።

አቶ አንዱአለም በበኩሉ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ቤተ እስራኤላውያን አቅም ስለሌላቸው ይህ እንደሚፈፀምባቸው ጠቁሞ " ወደ አምላክ ከመጮህ ውጭ ምንም ነገር የለም። የኛ ዋስትና እስራኤል ውስጥ ያሉ ቤተ እስራኤላውያን የሚያደርጉት ጫና ይወሰናል" ይላል።

የቤተ እስራኤላውያን አመጣጥ የንግሥት ሳባ ልጅ የሆነውን ሚኒልክን አጅቦ ከመምጣት ጋር የሚያይዙት እንዳሉ ሁሉ የእስራኤል በባቢሎናውያን መወረርን ተከትሎ ከተሰደዱት መካከልም እንደሆኑ ታሪክን አጣቅሰው ይናገራሉ።

በታሪክ ውስጥም የተለያዩ ስያሜ የተሰጣቸው ሲሆን ቤተ እስራኤል የተባሉትም በአብርሃ ወአፅብሃ ዘመነ መንግሥት ክርስትናን አልቀበልም በማለታቸው እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ይጠቅሳሉ።

በተለያዩ አመታትም ቤተ እስራኤላውያንን የመመለስ ስራ የተሰራ ሲሆን ከነዚሀም ውስጥ ኦፐሬሽን ሙሴና ኦፐሬሽን ሰለሞን ይጠቀሳሉ። በነዚህም ጉዞዎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቤተ እስራኤላውያን ሄደዋል።