በደብረ ማርቆስ ከተማ አንድ ግለሰብ ዛፍ ላይ ወጥቶ አልወርድም ካለ ከ24 ሰዓት በኋላ መውረዱ ታወቀ

ግለሰቡ የወጣበት ዛፍ ከርቀት ሲታይ Image copyright Debre MArkos Information communication Facebook

በደብረ ማርቆስ ከተማ ቀበሌ 03፣ ሰፈር አንድ፣ ድብዛ አካባቢ ከህዳሴ ጤና ጣቢያ ዝቅ ብሎ በሚገኝ ዛፍ ላይ የወጣ አንድ ግለሰብ አልወርድም ብሎ ከቆየ ከ24 ሰዓት በኋላ በራሱ ፈቃድ መውረዱን የቀበሌው ስራ አስኪያጅ አቶ አወቀ አዛዥ ለቢቢሲ ተናገሩ፡፡

በትናንትናው ዕለት የአካባቢው ሰዎች ስንት ሰዓት ላይ ዛፉ ላይ እንደወጣ ባያዩትም ከ4 ሰአት ጀምሮ ግን ዛፉ ላይ ወጥቶ መመልከታቸውን እንደነገሯቸው ለቢቢሲ ጨምረው አስረድተዋል።

ዛሬ ምሳ ሰአት አካባቢ ያለምንም ረዳት ከዛፉ ላይ እንደወረደ የሚናገሩት ስራ አስኪያጁ ለምን ዛፉ ላይ እንደወጣ ለመናገር ፈቃደኛ አልሆነም ብለዋል።

ከዛፉ ላይ እንደወረደ የአካባቢው ሰዎች የሚጠጣው ውሃና ያላቸውን ገንዘብ አዋጥተው እንደሰጡት ጨምረው ነግረውናል።

ግለሰቡ በአሁኑ ሰአት በከተማው ፖሊስ እጅ እንደሚገኝም ጨምረው አስረድተዋል።

የቀበሌው ስራ አስኪያጅ እንደሚሉት ግለሰቡ የወጣበት ዛፍ የሚገኝበት አካባቢ ገደላማ ሲሆን በተለምዶ የግምጭ ወንዝ የሚባለው የሚገኝበት ነው። ይህም ግለሰቡን ለማውረድ የሚደረገውን ጥረት ፍሬ አልባ አድርጎት ቆይቶ ነበር ብለውናል።

ዛፍ ላይ ወጥቶ አልወርድም ያለው ግለሰብ ዕድሜው ከ35 እስከ 45 የሚገመት ሲሆን የቆሸሸ ልብስ መልበሱን ክራንችም ከዛፉ ስር ወድቆ መገኘቱን ጨምረው ነግረውናል። እርሳቸውም አንድ እግሩና እጁ ላይ ጉዳት እንዳለበት መመልከታቸውን እና የአካል ጉዳተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።

"ነጭ የለበሰ 'መልአክ' በኦሮምኛ አናገረኝ"- የሬሳ ሳጥን ፈንቅለው የወጡት ግለሰብ

ወሎ በነዳጅ 'ልትባረክ' ይሆን?

«በሸካ ዞን የመንግሥት ቢሮዎች ለወራት ሥራ ፈተዋል. . .»

የደብረማርቆስ ከተማ ኮሚዩኑኬሽን የዜናና ሕትመት ባለሙያ ወ/ሮ ሐረጓ አበበ የወጣበት ዛፍ ትልቅ መሆኑን ተናግረው ለማውረድ በተሞከረ ቁጥር እርሱ ወደ ላይ ስለሚወጣ ተቸግረው ነበር።

የከተማው ኮሙዩኑኬሽን ባልደረቦች ዛሬ ማለዳ ሄደው እንዳዩት የሚናገሩት ወ/ሮ ሐረጓ ለማነጋገር ቢሞከርም ምላሽ እንደማይሰጥ ያስረዳሉ።

የወጣበት ባህር ዛፍ ትልቅ ቢሆንም እርሱ ግን ጫፍ ላይ የሚገኝ ቅርንጫፍ ላይ መውጣቱን ማየታቸውን ጨምረው አስረድተዋል።

ፖሊስ በአካባቢው ተገኝቶ እንደነበር የሚናገሩት የኮሙዩኑኬሽን ባለሙያ እንዲወርድ ለማድረግ የተለያዩ ሙከራቸውን ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።

Image copyright Debre MArkos Information communication Facebook

ግለሰቡ ደብረማርቆስ ቦሌ ኮንዶሚኒየም አካባቢ በጫማ ማሳመር ስራ ላይ ተሰማርቶ እንደነበር መረጃ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ተያያዥ ርዕሶች