የኢትዮጵያ ምርጫ ፡ የተቃዋሚዎችና የመንግሥት ወግ?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ጋር ውይይት እያካሄዱ Image copyright PM Office Facebook

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በአገር ውስጥ ከነበሩና ከውጭ አገር ከተመለሱ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ውይይት በማድረግ ላይ ናቸው።

ተቃዋሚ ፓርቲዎቹን የዛሬው ህዳር 18 ቀን 2011 ውይይትን ጨምሮ ከዚህ በኋላም ከሚመለከተው የመንግስት ተቋምና ሃላፊዎች ጋር በሚያደርጉት ውይይት አንገብጋቢ ብለው የሚሏቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

ምንም እንኳ በአገሪቱ ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ የሚያስችሉ ተቋማዊና የአሰራር ለውጦችን ማድረግ ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመንግሥት በኩል እንዲደረግ የሚጠብቁት ነገር ቢሆንም የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታና መጭው ምርጫ መቼ ይካሄድ? የሚለው ላይ ለየት ያለ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች አሉ።

"ምርጫው ይራዘም"

የአርበኖች ግንቦት ሰባት ቃል አቀባይ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ፓርቲያቸው ምርጫን ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና ምርጫ መታዘብን የሚመለከቱ ህጎች እንዲፈተሹ እንደሚፈልግ ይገልፃሉ።

ከተሰቀለበት ዛፍ አልወርድም ያለው ግለሰብ ከ24 ሰዓት በኋላ ወረደ

"የኖርዌይ ፓስፖርቴን መልሼ ኢትዮጵያዊ መሆን እችላለሁ" አቶ ሌንጮ ለታ

በኢትዮጵያ የሚገኙ ቤተ እስራኤላውያን ወደ ፅዮን ውሰዱን ተማፅኖ

እሳቸው እንደሚሉት በአንድ በኩል ምርጫ ቦርድ እስከ ዛሬ ይሰራባቸው የነበሩ ህጎችና የምርጫ ስርአቱ ራሱ ትልቅ ጥያቄ የሚያነሱባቸው ጉዳዮች ናቸው

እስከዛሬ በኢትዮጵያ ምርጫ የተካሄደበትን ስርአት መቀየር ማለትም እንደ ምርጫ ቦርድ ያሉና ፣ የፍትህ ስርዓቱን ፣ የመከላከያ ፣ የደህንነት እንዲሁም በመንግስት ስር ያሉ መገናኛ ብዙሃንን ከፖለቲካ ነፃ ማድረግ ጊዜ የሚወስድ ስለሆነ ምርጫው እንዲራዘም እንደሚፈልጉ አቶ ኤፍሬም ይናገራሉ።

"የምርጫ ስርአቱ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ መቀየር አለበት ካልን ቁጭ ብለን አይደለም የምንለውጠው። በምሁራን ከዲሞክራሲ ልምዳችን፣ ከማህበረሰባዊ አደረጃጀታችን አኳያ ምን አይነት የምርጫ ስርዓት ያስፈልገናል? የሚለውን ማጥናት አለብን አማራጮች ቀርበውም በፓርላማ መፅደቅ አለባቸው" የሚሉት አቶ ኤፍሬም እነዚህን ነገሮች ለማድረግ ደግሞ ቀሪዎቹ አስራ ስድስት ወራት በቂ እንደማይሆኑ ያስረዳሉ።

ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ፓርላሜንታዊ ወይስ ፕሬዝዳንታዊ ስርዓት የሚለውም ጭምር አርበኞች ግንቦት ሰባት ንግግር ያስፈልገዋል ብሎ የሚያምንበት ጉዳይ ነው።

የፍትህ ተቋማት ገለልተኝነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም የህዝብ መገናኛ ብዙሃን እንደ ባለፉት ዓመታት በወገንተኝነት እንደማይንቀሳቀሱ ማረጋገጥ ጊዜ እንደሚወስድም ያስረግጣሉ።

Image copyright OFFICE OF THE PRIME MINISTER

ምን ተይዞ ወደ ምርጫ?

በሌላ በኩል ዲሞከራሲን ለማስፈንም ሆነ ነፃ ምርጫ ለማካሄድ ሰላም ወሳኝ በመሆኑ የአገሪቱ መረጋጋት ከምንም በላይ ያሳስበኛል የሚለው አረና ፓርቲ የመንግስት የህግ የበላይነትን ማስፈን ቅድሚ የምሰጠው ጉዳዬ ነው ይላል።

"መፈናቀል፣ግጭትና ሁከትን በማስቆም የመንግስት ህግና ስርዓትን ማስከበር ዋናው ጉዳያችን ይሆናል ። ይህ በሌለበት ምርጫና ዲሞክራሲን ቢበል ዋጋ የለውም" ይላሉ የፓርቲው መስራችና አመራር አቶ ገብሩ አስራት።

ከዚህ በመለስ ግን ተቋማትን ነፃ ማድረግ ትኩረት የሚሰጡት ጉዳይ እንደሆነም አቶ ገብሩ ይናገራሉ።

ሲቪል ማህበራት በነፃነት እንዲደራጁና እንዲንቀሳቀሱ ማድረግም ሌላው ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ገብሩ ይህን ሁሉ ግን መንግሥት ብቻውን ያድርግ እንደማይባል ፤ ይልቁንም ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሳተፉበት ፍኖተ ካርታ ተነድፎ ወደ ተግባር መገባት እንደሚያስፈልግ አቶ ገብሩ ያስረዳሉ።

"የፖለቲካ ምህዳሩ ካልሰፋ፣ ከምርጫ በኋላ የሚዳኝ ገለልተኛ የፍትህ ተቋም የማይኖር ከሆነ ምርጫ ዛሬም ዝርፊያና ወደ ቀውስ የሚከተን ነገር ነው የሚሆነው" የሚሉት አቶ ገብሩ ምርጫን ፍትሃዊና ተአማኒ የሚያደርጉ ስርዓቶች እስከተዘረጉ ድረስ ምርጫ ቀረበም ረዘመ አረና ችግር እንደሌለበት ይገልፃሉ።

Image copyright OFFICE OF THE PRIME MINISTER

ምርጫ መቼ ይካሄድ የሚለውን የሚወስነው...

የምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት ፣ የምርጫ ጉዳዮችን የሚዳኝ ገለልተኛ የፍትህ ስርአትና የህዝብ መገናኛ ብዙሃንን ከወገንተኝነት ነፃ ማድረግ የኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ ቀዳሚ ጉዳዮች እንደሆኑ ሊቀ መንበሩ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ይገልፃሉ።

አሁን ላይ ምርጫ መቼ ይደረግ? የሚለው ዋናው ጉዳይ አይደለም ለፕሮፌሰር በየነ።

እሳቸው እንደሚሉት ምርጫው መቼ ይካሄድ ከሚለው በፊት ምርጫውን ፍትሃዊ የሚያደርጉ ነገሮች መከናወን አለባቸው።

"የእነዚህ ነገሮች እውን መሆን ነው ምርጫው መቼ ይካሄድ የሚለውን የሚወስነው" ይላሉ ፕሮፌሰር በየነ።

ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ ለውጦች መደረግ ጥያቄ የሌለው ነገር ነው የሚለው ሰማያዊ ፓርቲም ከሁሉም በላይ የመንግስት የህግ የበላይነትን አስፍኖ አገሪቱን ማረጋጋት ያሳስበኛል ይላል።

ወ/ሪት ብርቱካን በወዳጆቻቸው አንደበት

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት ለህግ ባላቸው ቀናኢነት መሆኑ ተገለፀ

በመጀመሪያ አገሪቱን ማረጋጋትና ከዚያም ወደ ፍትሃዊ ምርጫ የሚወስዱ ለውጦችን ማድረግ ግን ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ ምርጫ የሚካሄድበት ጊዜን በሚመለከት ስጋት እንዳላቸው የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አበበ አካሉ ይናገራሉ።

ስለዚህም በዚህ ጉዳይ ላይ የህዝብን ስሜት ማንበብና ከህዝብ ጋር መምከር እንዲሁም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር መነጋገር እንደሚያስፈልጋቸው ያምናሉ።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ