ሶስት ቻይናዊያን በኬንያ በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ዋሉ

የባቡር መንገድ ሰራተኛው ቀይ ባንዲራ ሲያውለበልብ Image copyright AFP

ሶስቱ ቻይናዊያን የኬንያ የባቡር ትራንስፖርት የቲኬት አገልግሎት ጋር በተያያዘ የተፈፀመ ማጭበርበርን ለሚያጣራው ቡድን ጉቦ ለመስጠት ሲሞክሩ በቁጥጥር ስር ዋሉ።

ከባቡር መንገድ ትራንስፖርቱ በቀን እስከ 300 ሺህ ብር ድረስ ይዘረፍ ነበር በማለት የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

እንደ አቃቤ ህግ ከሆነ ቻይናዊያኑ እስከ 150 ሺህ ብር ድረስ ጉቦ ለመስጠት ሲሞክሩ ነበር። ኬንያ ነፃነቷን ካገኘች ወዲህ ከተከናወኑ ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ ይህ የባቡር ትራንስፖርት ፕሮጀክት ትልቁ ነው።

የቀድሞ የዚምባብዌ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ መራመድ ተስኗቸዋል

ምርጫ ፡ የተቃዋሚዎችና የመንግሥት ወግ?

ታሪክ እየቀየሩ ያሉት ሴቶች

የቻይና መንግስት በሰጠው የሶስት ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ የተገነባው ይህ የባቡር ትራንስፖርት ከግንቦት ወር 2017 ጀምሮ በተለያዩ የሙስና ወንጀሎች ስሙ ሲብጠለጠል ነበር።

ሶስቱ ቻይናውያን ሊ ጄን፣ የትራንስፖርት መምሪያ ኃላፊ፣ ሊ ዡዋው፣ የደህንነት ኃላፊ፣ ሱን ዢን ሲአር ቢ ሲ የተሰኘው ኩባንያ ባልደረቦች ናቸው።

እነዚህ ቻይናውያን ጉቦ ሊሰጡ ሲሉ በቁጥጥር ስር የዋሉት አርብ ዕለት ሲሆን የተጠረጠሩበት ምዝበራ ግን ለምን ያህል ጊዜ ሲፈፅሙት እንደቆዩ የተባለ ነገር የለም።

እነርሱም የቀረበባቸውን ውንጀላ አጣጥለዋል።

የአቃቤ ህግ ፎቷቸውን በቲውተር ገፁ ላይ ያጋራ ሲሆን በዚህ ሳምንት ችሎት ፊት ቀርበው ጉዳያቸው መታየት እስኪጀምር ድረስ በማረሚያ ቤት ይቆያሉ።

ይህ ብዙ የተባለለት ባቡር መንገድ በተለያዩ የሙስና ቅሌቶች ስሙ ይብጠለጠላል።

ከነዚህም መካከል አንዱ የባቡር መስመሩ በሚያልፍባቸው አካባቢዎች መሬት የሌላቸው ግለሰቦች መሬታቸው በመስመር ዝርጋታው ምክንያት እንደተነካ በማስመሰል ካሳ ገንዘብ መጠየቅ ይገኝበታል።

በድርጅቱ ውስጥ የሚሰሩ ቻይናዊያን አለቆች በኬንያውያን ባልደረቦቻቸው ላይ የሚያደርሱት መገለልና ዘረኝነት ሌላው ነው።

ስራ በጀመረ በመጀመሪያ አመት ብቻ የ100 ሚሊየን ዶላር ኪሳራ አስመዝግቧል የተባለው ይህ የባቡር መስመር ትርፋማነትም በተደጋጋሚ የሚነሳ ጥያቄ ነው።

የዱር አራዊት መብት ተሟጋቾችም የባቡር መስመሩ አቋርጦ የሚሄድባቸው መስመሮች ላይ የሚገኙ የዱር እንስሳት ህይወት አደጋ ላይ ወድቋል በማለት ቅሬታቸውን ያሰማሉ።

ይህ የባቡር መስመር ሲመረቅ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ በምስራቅ አፍሪካ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ በማለት አንቆለጳጵሰውት ነበር።

ይህ የባቡር መስመር ከሞምባሳ ናይሮቢ ድረስ የተዘረጋ ነው።

ወደፊትም የባህር በር የሌላቸው ጎረቤት ሀገራትን ደቡብ ሱዳን፣ ሩዋንዳን፣ ብሩንዲን እና ኢትዮጵያን ከህንድ ውቅያኖስ ጋር ለማገናኘት ታቅዶ ነበር።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ