"ፓስፖርት መስጠት አልተከለከለም" የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች ተቋም

የኢትዮጵያ ፓስፖርት

አንዲት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አራተኛ ዓመት የሕክምና ሳይንስ ተማሪ ናይጄሪያ የሚገኝ ዩኒቨርስቲ በሚያካሄደው ጉባኤ ላይ እንድትገኝ ግብዣ ቀርቦላታል።

በምትማርበት ተቋም የምትመራው ኮሚቴን ወክላ ወደ ናይጄሪያ ለመጓዝ ግን ፓስፖርት ለማውጣት ወደ የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች መሥሪያ ቤት የቀበሌ መታወቂያዋንና ያስፈልጋል ያለችውን ክፍያ ይዛ ሄደች።

ከመሥሪያ ቤቱ ያገኘችው መልስ ግን ከጋባዡ አካል ደብዳቤ እስካላመጣች ፓስፖርት ማግኘት አንደማትችል የሚገልፅ ሆነ።

ምንም እንኳ ፓስፖርት ማግኘት እጅግ አዳጋች እንደሆነ የሚገልፁ መረጃዎች እየወጡ ቢሆንም ፓስፖርት ማግኘት የሁሉም ሰው የዜግነት መብት በመሆኑ አለመከልከሉን የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች ዋና መመሪያ ሕዝብ ግንኙነት ምክትል ኃላፊ አቶ የማነ ገብረ መስቀል ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ዜግነት ለመግዛት ምን ያህል ይከፍላሉ?

ፓስፖርት፡ የሰዎችን እንቅስቃሴ የወሰነ ሰነድ

"የኖርዌይ ፓስፖርቴን መልሼ ኢትዮጵያዊ መሆን እችላለሁ" አቶ ሌንጮ ለታ

የኢትዮጵያ መንግሥት ከሦስት የመካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት አድርጓል ያሉት አቶ የማነ ከቀሪዎችም ጋር ለማድረግ እየተነጋገረ መሆኑን ገልፀዋል።

መንግሥት ቀደም ሲል ወደ እነዚህ ሃገራት ይደረግ የነበረውን ሕገ ወጥ ጉዞ አስቁሟል ካሉም በኋላ ጉዞው ሕጋዊ በሚመስል ነገር ግን በሕገ ወጥ መንገድም ሲደረግ ቆይቷል በማለት ያስረዳሉ።

እናም የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች መምሪያ አንደኛ የዜጎችን ሕጋዊ እንቅስቃሴን ፣ የዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥ እንዲሁም መንግሥት ባቋቋመው ግብረኃይል ውስጥም ስላለ ሕጋዊ ስምሪቱን እንዲጠናከር እያደረገ እንዳለ አቶ የማነ ይገልፃሉ።

እሳቸው እንደሚሉት የተቋማቸው እንቅስቃሴ ከሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ የመጣ አንድ አዋጅ ከመንግሥትም የመጣ ሌላ ትእዛዝን መሠረት ያደረገ ነው።

"መንቀሳቀስ የዜጎች ሕገ-መንግሥታዊ መብት ነው። እየከለከልን አይደለም ልንከለክልም አንችልም። የዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥ ግን የተቋሙ ስልጣን ነው" የሚሉት አቶ የማነ የዜጎች ፓስፖርት የማግኘት መብት አሁንም ሕጉን ተከትሎ ተፈፃሚ እየሆነ እንዳለ ይገልፃሉ።

ፓስፖርት የጉዞ ሰነድ እንጂ የቀበሌ መታወቂያን የሚተካ መሆን የለበትም የሚሉት ኃላፊው ቅርንጫፎቻቸውን ጨምሮ በቀን አስር ሺህ የሚሆን ፓስፖርት እንደሚሰጡ ገልፀዋል። ቢሆንም ግን የሚጠቀሙበት ጥቂቶች ብቻ እንደሆኑ ከዚህ ሲያልፍም ብዙዎቹ ፓስፖርታቸውን ለደላላ ሰጥተው በድጋሚ የሚያወጡ መሆናቸውንም ያስረዳሉ።

እንደ የጉዟቸው ዜጎች ማቅረብ ያለባቸውን ሰነድ ካሟሉ ፓስፖርት ማግኘታቸው ምንም ጥያቄ እንደሌለው አቶ የማነ አስረግጠው ያስረዳሉ።

አቶ የማነህ ማንኛውም ፓስፖርት የሚፈልግ ግለሰብ ከሚያስፈልጉት ሰነዶች መካከል አንደኛው መታወቂያ ሲሆን ወደ መካከለኛው ምስራቅ ለሥራ ሊሄድ ከሆነ ግን አስፈላጊውን መስፈርት ማሟላታቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ ማቅረብ አለበት ብለዋል።

ወደ ሌላ ሃገር ለጉብኝት የሚሄድ ከሆነ የጉብኝት ደብዳቤ፣ ሆቴል የያዘበትንናና የአየር ቲኬት የገዛበትን ማስረጃዎችን ማቅረብ ይጠበቅበታል ይላሉ።

"የሕክምና ጉዞም ከሆነ በተለይም አስቸኳይ ከሆነ በአንድ ወይም በሁለት ቀን ፓስፖርት ይሠራል" ብለዋል ኃላፊው ። እንደዚህ ያሉ የሕክምና ተጓዦችም ማሳየት ያለባቸው የሚሄዱበት ሃገር ሆስፒታል ቀጠሮን ወይንም ከአገር ውስጥ ሐኪሞች የተፃፈላቸውን የሕክምና ማስረጃ ነው።

አፍሪካዊያን ሌሎች የአፍሪካ ሃገራትን መጎብኘት ለምን ይከብዳቸዋል?

ኃላፊው እንደሚሉት ፓስፖርት ለማደስም አካሄዱ ተመሳሳይ ነው። እንደ አቶ የማነ በአጠቃላይ ተቋማቸው በአሁኑ ወቅት ፓስፖርት አሰጣጥም ሆነ እድሳት ላይ እየተከተለ ያለው አሠራር በተለይም ወደ መካከለኛው ምስራቅ የሚደረግ ሕገወጥ ዝውውርን ከመቆጣጠርና ከመግታት ጋር የተያያዘ እንደሆነ አስረግጠው ተናግረዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ