የአለማየሁ ተፈራ ፖለቲካዊ ካርቱኖች

ከአለማየሁ ወቅታዊ ካርቲኖች አንዱ

የፎቶው ባለመብት, AlEMAYEHU TEFERA

የምስሉ መግለጫ,

ከአለማየሁ ወቅታዊ ካርቲኖች አንዱ

መድፈር፣ ብልት ላይ የውሃ መያዣ ፕላስቲክ ማንጠልጠል፣ በፒንሳ የብልት ቆዳን መሳብ፣ ዛፍ ላይ ሰቅሎ መግረፍ፣ በኮረንቲ መጥበስ፣ በአፍንጫ እስክሪብቶ ማስገባት፣ በአፍ እና በአፍንጫ እርጥብ ፎጣ መወተፍ፣ ሙቀታማ ስፍራዎች ላይ ለረዥም ጊዜ ማስቀመጥ፣ ጥፍር መንቀል. . .

እነዚህ አሰቃቂ ማሰቃያ መንገዶች በሰብአዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ፈጽመውታል የተባሉ ናቸው።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ብርሀኑ ጸጋዬ በሙስናና በሰብአዊ መብት ጥሰት የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ካሳወቁ በኋላ፤ ጉዳዩን መገናኛ ብዙሃን ለቀናት ዘግበውታል፣ በማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆኖም ነበር።

ነዋሪነቱን በእንግሊዝ ያደረገው ካርቱኒስቱ አለማየሁ ተፈራ፤ በትውልድ ሀገሩ ኢትዮጵያ የበርካቶች መነጋገሪያ የሆነውን ርዕሰ ጉዳይ የሥራው ግብአት አድርጎታል።

ሆዱ ከመላ ሰውነቱ በላይ የገዘፈና ወታደራዊ ልብስ የለበሰ ግለሰብ ፒንሳ ይዞ እጅግ የኮሰሱና ግድግዳ ላይ ወደተንጠለጠሉ ሰዎች ሲጠጋ በካርቱኑ ላይ ይታያል።

አለማየሁ መሰል ካርቱኖችን መሥራት ከጀመረ ከሁለት አሰርታት በላይ ተቆጥረዋል። የየወቅቱን የፖለቲካ ትኩሳት የሚገልጹ ካርቱኖች ሰርቷል። ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ዳሷል። ካርቱኖቹ ፈገግታ የሚያጭሩ፣ የሚተቹ፣ ሁነቶችን ከተለያየ አቅጣጫ የሚያሳዩም ናቸው።

97 ምርጫ እንደ መነሻ. . .

የአለማየሁ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ካርቱኖች ጎልተው መውጣት የጀመሩት ከ97 ምርጫ ወዲህ ነው። ያኔ ከሚኖርበት እንግሊዝ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ በሀገሪቱ ያስተዋለው ውጥንቅጥ ለበርካታ ሥራዎቹ መነሻ ሆኗል።

የያኔውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተመርኩዞ ሥራዎቹን በፌስቡክ ማቅረብ የጀመረው፤ ካርቱን ስሜቱን የሚገልጽበት መሳሪያ በመሆኑ እንደነበረ ያወሳል።

በወቅታዊ ፖለቲካ ላይ በሚያተኩሩ ሥራዎቹ ይታወቃል

የፎቶው ባለመብት, AlEMAYEHU TEFERA

የምስሉ መግለጫ,

በወቅታዊ ፖለቲካ ላይ በሚያተኩሩ ሥራዎቹ ይታወቃል

"የሀገሪቱን ውስጣዊ ጣጣዎች ሳያቸው ወደ ፖለቲካ የሚያዘነብሉ ካርቱኖች መሥራት ጀመርኩ። የሰፈሬ ልጆች ሞተዋል። በተገደሉት ሰዎች አዝኜ ነበር። ጊዜው ከባድና አስጨናቂ ነበር"

ሀሳብን እንደልብ በአደባባይ መግለጽ ያስገድል፣ ያሳስር፣ አካል ያስጎድል፣ ያሰድድ፣ የነበረበት ወቅት እንደነበረ አይዘነጋም።

"ካርቱን መልዕክት ማስተላፍ የሚቻልበት መሳሪያ ነው። ግን አደጋ ነበረው"

ካርቱኖቹን እንግሊዝ ሆኖ መስራቱ በተወሰነ ደረጃ ስጋቱን ቢያቀልለትም፤ ከሀገር ርቆም ከጫና አላመለጠም። የሚሠራቸውን ካርቱኖች ተከትሎ ማስፈራሪያ ይደርሰው ነበር። የጥቃት ሙከራ እንደተደረገበትም ይናገራል።

ካርቶኖቹን የሚያሰራጭበት ፌስቡክ የበርካቶች መንደር ነው። ሥነ ጥበብ የሚወዱ፣ የሚያደንቁ፣ የፖለቲካ ግንዛቤ ያላቸው፣ እንዲሁም ለጥበቡ ግድ የሌላቸው፣ ፖለቲካውም ከአንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲታይ የሚፈልጉም ሀሳባቸውን ያለ ገደብ በፌስቡክ ይገልጻሉ።

በወቅታዊ ፖለቲካ ላይ በሚያተኩሩ ሥራዎቹ ይታወቃል።

ከዓመታት ስደት በኋላ ወደሀራቸው የተመለሱ የጥበብ ሰዎች ያሳየበት ሥራ

የፎቶው ባለመብት, AlEMAYEHU TEFERA

የምስሉ መግለጫ,

ከዓመታት ስደት በኋላ ወደሀራቸው የተመለሱ የጥበብ ሰዎችን ያሳየበት ሥራ

"ሰዎች ጉዳት ሊያደርሱብኝ የሞከሩበት ጊዜ ነበር። ሦስት አራት ጊዜ ጥቃት ተሞክሮብኛል። ለፖሊስ ሪፖርት አድርጌ ሰዎቹ በአካባቢዬ እንዳይደርሱም ተደርጓል"

እንግሊዝ በመሆኑ ሊሠራቸው የቻላቸው ካርቱኖች ኢትዮጵያ ቢሆን እንደማይሞከሩ ይናገራል።

"ኢትዮጵያ ብሆን እሞት ወይም አንዱ ጆሮዬን፣ አንዱ ጥፍሬን ነቅሎት ነበር። 'እጁን መቁረጥ ነው' የሚሉ ሰዎች እዛ [ኢትዮጵያ] ብሆን ይሳካላቸው ነበር"

ሥራው የግል ህይወቱን ማደነቃቀፉም አልቀረም። አለማየሁ እንደሚለው፣ የሀበሻ ሬስቶራንት፣ ጭፈራ ቤት የማይሄድባቸው ወቅቶች ነበሩ።

ዓመት በዓመት ላይ ሲደረብ፣ ሀገሪቱ በሕዝባዊ ተቃውሞ ተንጣ፣ ዛሬ ላይ ደግሞ አንጻራዊ ለውጥ ይስተዋላል እየተባለ ነው። ካርቱን ለአለማየሁ የሂደቱ ነጸብራቅ ነው። ሆኖም የአንጻራዊ ለውጥ መኖር ካርቱንን ክፍተቶችን ነቅሶ ከማውጣት ሚናው እንደማይገታው ይናገራል።

ዘመናት በአለማየሁ ካርቱኖች ሲገለጹ. . .

ካርቱን የመንቀፍ፣ የማሳቅ፣ ለለውጥ የማነሳሳት፣ ለሀሳብ ወይም ለክርክር የመጋበዝ ባህሪ አለው። አለማየሁ ሥራዎቹ ሙገሳም ወቀሳም ቢያስከትሉበትም ከሙያው ሕግጋት ዝንፍ የሚል አይመስልም።

"ጠቅላይ ሚንስትሩ የኢትዮጵያን ካርታ ይዘው ሲሮጡ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዘራፊዎች የሰረቁትን ይዘው ሲሸሹ"

የፎቶው ባለመብት, AlEMAYEHU TEFERA

የምስሉ መግለጫ,

"ጠቅላይ ሚንስትሩ የኢትዮጵያን ካርታ ይዘው ሲሮጡ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዘራፊዎች የሰረቁትን ይዘው ሲሸሹ"

ከአንድ ወገን ምስጋና ከሌላ ወገን ኩነኔ ካመጡበት ሥራዎቹ መካከል የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ የሰራውን አይዘነጋም።

"መለስ በህይወት ሳለ ከአየር መንገድ ወደ ቤተ መንግሥት በሚሄድበት ሰዓት ህጻን፣ አዋቂ ሳይባል የመንገድ ጥግ ይዘው ፊታቸውን ያዞራሉ። 'ደህንነት የለም' በሚል እሱና ሕዝቡ ፊትና ኋላ ይሆኑ ነበር። ከሞተ በኋላ፤ ሬሳው በመኪና ተደርጎ ሲሄድ ሰዎች ከየአካባቢው እየመጡ መኪናው ላይ እየተንጠለጠሉ፣ እየተደፉ ያለቅሱ ነበር. . ."

ሥራው የሁለት ዘመናትን ተቃርኖ የሚያሳይ ነው። ኑሮ ሲወደድ፣ ሚዲያ ለፕሮፖጋንዳ መንዣ ሲውል መመልከት እርሳሱን እንዲያነሳ ይስገድደዋል።

"የዓመቱ ኮከብ ሆዶች" እና "ወያኔ ስትቆነጠጥ" የተሰኙ ካርቱኖቹን ሲገልጽ፤ "ዛሬ ዘርፈዋል ተብለው የተከሰሱ ሰዎችን እኔ ድሮ ራቁታቸውን ሰርቻቸዋለሁ።"

"በእስልምናና ክርስትና መካከል ግጭት ለመፍጠር ተብሎ የተሰራ ዘጋቢ ፊልም ነበር። "ወያኔ ስትቆነጠጥ" በሚል የሰራሁት ካርቱን የእስልምናና ክርስትና ሀይማኖት መሪዎችን ሲቆነጥጡ ያሳያል።"

እነዚህ ካርቱኖች ዛሬ ላይ በሀገሪቱ ላይ ለሚስተዋለው አንጻራዊ ለውጥ የድርሻቸውን አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ያምናል። "ያለፉት ዓመታት ልፋቴ ከንቱ አልቀረም" የሚለውም ያለ ምክንያት አይደለም።

አንድ ሀገር ከአንድ አስተዳደር ወይም ከአንድ የፖለቲካ ሥርዓት ወደሌላው ብትሸጋገርም፤ ሁሌም መሰናክሎች ስለማይጠፉ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት የለውጥ ድምጽ መሆን ያስፈልጋል።

"ካርቱን [ሁሌም] ይተቻል"

የፎቶው ባለመብት, AlEMAYEHU TEFERA

የምስሉ መግለጫ,

"ካርቱን [ሁሌም] ይተቻል"

"ለውጥ ሰው የሚያስፈልገውን ነገር [በአጠቃላይ] አያሟላም። ወደፊትም አያሟላም። ስለዚህ ካርቱን [ሁሌም] ይተቻል።"

አለማየሁ እንደሚለው፤ ካርቱኒስት በሥራዎቹ እይታውን ይገልጻል። የሚዝናናበት፣ የሚበሳጭበት፣ የሚቆረቆርበትን ለሕዝብ ያካፍላል።

"እንደ ካርቱኒስ በመደመርም በመቀነስም ውስጥ መኖር የለብኝም። ምክንያቱም እንደ ካርቱኒስት በችግሮች ዙሪያ 'ሂውመር' [ፈገግታ] ለመፍጠር ነው የምሞክረው። የሙያው ግዴታ ነው። ጎራ ተይዞ የሚሰራ አይደለም። ሁሌም ውጪ ሆኖ ነው የሚሠራው። መሠራት ያለበት በሕዝብ ወገን ነው። የሕዝብ ድምጽ ነው። ነጻነታቸውን ያጡ፣ ሀሳባቸውን በነጻነት መግለጽ የማይችሉትን ለመግለጽ [ለመወከል] ነው የምንሞክረው።"

ዛሬም ችግሮች እንዳሉ ለማሰየት ከሠራቸው አንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ የኢትዮጵያን ካርታ ይዘው ሲሮጡ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ዘራፊዎች የሰረቁትን ይዘው ሲሸሹ፣ በየክልሉ ያለውን ሽኩቻም ያሳያል።

ካርቱን 'የትግል መሳሪያ'?

ካርቱኖች መንግሥት ትኩረት እንዲሰጣቸው የተፈለጉ ነገሮች ማሳያ ሆነው ያገለግላሉ።

በፖለቲካ ካርቱኖች ሙሰኞች፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የፈጠሩ ግለሰቦችና፣ ሰብአዊ መብት የጣሱ ሰዎች በጥበባዊ መንገድ ይገለጻሉ።

"ካርቱንን ለነጻነት ትግል ቁልፍ መሳሪያ ነው"

የፎቶው ባለመብት, AlEMAYEHU TEFERA

የምስሉ መግለጫ,

"ካርቱንን ለነጻነት ትግል ቁልፍ መሳሪያ ነው"

ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ ሙሰኛው ሆዱ ተቆንዝሮ፣ ጠብ አጫሪው ተንኮል በአእምሮው ሲመላለስ፣ ገዳይ በደም ተነክሮ ይሳላል። ሸረኛ በእባብ እንዲሁም ሌሎች ሰዎችንም እንደየባህሪያቸው በተለያዩ እንስሳት መመሰል ሌላው መንገድ ነው።

አለማየሁ ካርቱንን "ለነጻነት ትግል ቁልፍ መሳሪያ ነው" ይለዋል።

ከተቀረው ዓለም አንጻር ኢትዮጵያ ውስጥ ካርቱንን የማየት፤ እንደ ሀሳብ ማስተላለፊያ የመጠቀም ልምድ ባይዳብርም፤ የማኅበረሰቡን ድምጽ ለማስተጋባት የዋለባቸው ጊዜያት ይጠቀሳሉ።

አሁን ላይ ካለው በላቀ ካርቱን በነጻነት የሚሰራበት ወቅት እንደሚመጣ ያምናል። ካርቱኒስቶችን የሸበቧቸው ስጋቶች እየተቀረፉ እንደሚሄዱም ተስፋ ያደርጋል።

"ካርቱን ሲሠራ የግል ወይም የቡድን ጨዋታ ሳይሆን ሀሳብ ላይ ያተኮረ ትችት መኖር አለበት።"

በእርግጥ በቂ የካርቱን ሙያተኛ የለም። ያሉትም ጎልተው መውጣት አልቻሉም። ሙያተኞቹ ሀሳባቸውን በነጻነት ለመግለጽ ከመቸገራቸው ባሻገር ለሥራቸው ተመጣጣኝ ክፍያ አለማግኘታቸውም ሌላ ጫና ይፈጥራል።

አለማየሁ ወደኋላ እና ወደፊት. . .

ያደገው አዲስ ከተማ አካባቢ፣ ለሥነ ጥበብ በተመቸ ቤተሰብ ውስጥ ነው። እናቱ ወረቀት፣ ቀለም. . . ያቀርቡለታል። የፋሽን ዘርፍ ይማርከው ስለነበረም የፋሽን ዲዛይን መጽሔት ይሰጠው ነበር።

በልጅነቱ 'ስኬች' ከማድረግ ተነስቶ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለም በሥነ ጥበቡ ገፋበት። አለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት ሳለ ዓመታዊ መጽሄት እንዲሠራ ተሰጠው።

ያ የመጀመሪያው የኅትመት ውጤቱ ነው።

ካርቱን ከተማሪነት ዘመኑ አንስቶ ይስበዋል። ለካርቱን ዝንባሌ ብቻ ሳይሆን ተፈጥሯዊ ስጦታ እንዳለውም ያምናል። ከኢትዮጵያ ወደ እንግሊዝ ሲሄድ ነበር ካርቱን የተከበረ ጥበብ መሆኑን የተገነዘበው።

እዛው እንግሊዝ ውስጥ "ሀበሻኒ" የሚል አስቂኝ የፖለቲካ ኮሚክ መጽሐፍ አሳተሟል። የተለያዩ ዘመናት ነጸብራቅ የሆኑ ሥራዎቹን አሰባስቦ ለማሳተምም ከፀሀይ ፐብሊሸርስ ጋር ተስማምቷል።

ከካርቱኖቹ ጎን ለጎን ዋነኛ የገቢ ምንጩ የአኒሜሽን ፕሮዳክሽን፣ የኢሉስትሬሽን መጽሐፍና ስቶሪ ቦርድ ሥራ ነው።

ካርቱኖች ሲሠራ ፖለቲካውን እንዲሁም ፈገግታ ለማጫር የፈለገበትን መንገድ የሚረዱ ወዳጆቹን ያማክራል። ሆኖም ካርቱን በስቱድዮ፣ በሙያተኞች በውይይት ቢሰራ ይመርጣል።

"ካርቱን እንደ ሀገር ትልቅ ሀላፊነት የሚጠይቅ ነው። ጠንካራ የፖለቲካና ኤድቶሪያል ብቃት ያለው ተቋም ያስፈልጋል። በስቱዲዮና በባለሙያ ታግዞ ሙሉ ሰዓት የሚሰራም ነው።"

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

ፖለቲካዊ እውነታዎች በአለማየሁ ተፈራ እርሳስ