ቴክኖሎጂ የመጥፋት አደጋ የጋረጠባቸው ሙያዎች

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency
«ማንኛውም ዓይነት ሥራ፤ በተለይ ደግሞ ብዙ ሊከብድ የማይችል ተብሎ የማይታሰብ፤ ከአምስት እና አሥር ዓመት በኋላ በሂሳብ ቀመር ሊሠራ ይችላል።»
'ሮቦቶቹ እየመጡ ነው' በሚለው አነጋጋሪ መፅሐፉ የሚታወቀው ጆን ፑሊያኖ መፃዒውን ሲተንብይ ነው እንዲህ ሲል ያስቀመጠው።
ፑሊያኖ፤ ከቢቢሲ ጋር ወግ ሲጠርቅ ነው ወደፊት በሰዎች የሚሠሩ ሙያዎች፤ በተለይ ደግሞ የፋብሪካ ሥራዎች በዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂዎች ይወረሳሉ ሲል የተደመጠው።
ይህ ዜና ለሰሚ ጆሮ አዲስ አይደለም፤ አዲሱ ነገር ቴክኖሎጂ ብዙ አይነካቸውም ተብለው የሚታሰቡ መስኮችም አደጋ ላይ መሆናቸው ነው።
«ዶክተሮች አሊያም የሕግ ባለሙያዎች ሥራቸውን በቴክኖሎጂ ላይነጠቁ ይችላሉ፤ ነገር ግን ተያያዥ ሥራዎቻቸው አደጋ ላይ ነው።»
ተስፋ ያላቸው ያልተጠበቁ ችግሮችን መፍታት የሚችሉ ሰዎች ቴክኖሎጂ ሊያከናውን የሚችለውን ነገር የሚሠሩ ከሆነ 'አበቃላቸው' ባይ ነው ፑሊያኖ።
ፑሊያኖ፤ የኮምፒውተር ደህንነት ባለሙያዎች በሚመጣው ዘመን ተፈላጊነታቸው እጅግ የላቀ ነው፤ በተለይ የሳይበር ጥቃትን ቀድመው መገመት እና መከላከል የሚችሉቱ ሲል ያምናል።
«ግን እንዲህ ስላችሁ ሌላው ሙያ አፈር በላ ማለቴ አይደለም» ይላል ፀሐፊው፤ የሳይኮሎጂ (ስነ-ልቡና) ባለሙያዎች፤ የአእምሮ ጤንነት አማካሪዎች እና ተያያዥ ሙያዎችም ተፈላጊነታቸው እየላቀ ይመጣል።
ቢያንስ ባደጉት ሃገራት ከታች የምንጠቅሳቸው ሰባት የተከበሩ ሙያዎች በቴክኖሎጂ ምክንያት አደጋ የተጋረጠባቸው ናቸው፤ በፀሐፊው ቀመር መሠረት።
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሕክምና
ይህ ሃሳብ የሚዋጥ ባይሆንም ግን ሃቅ ነው ሲል ፑሊያኖ ያትታል። ባደጉ ሃገራት የሚገኙ የሕክምና ባለሙያዎች ወደፊት ጤና የሚጠበቀው በቴክኖሎጂ እገዛ ስለሚሆን ሙያቸው አደጋ ላይ ነው። የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች እና የቀዶ ጥገና ባለሙያዎች ግን ከዚህ አደጋ የተረፉ ናቸው።
የሕግ ባለሙያዎች
ተሽከርካሪ ወንበራቸው ላይ እየተንፈላሰሱ ከጠረጴዛ ጋር የተገናኘ ሥራ የሚሰሩ የሕግ ባለሙያዎች ወዮላቸው፤ ፑሊያኖ እንደሚለው። ፀሐፊው፤ በአንድ የተለየ የሕግ ሃሳብ ላይ የረቀቀ እውቀት የሌላቸው የሕግ ሰዎች፤ እመኑኝ አደጋ ላይ ናቸው ሲል ማስጠንቀቂያ ቢጤ ጣል ያደርጋል።
የሥነ-ሕንፃ ባለሙያዎች
'ምጡቅ' ተማሪዎች ብቻ ተመርጠው የሚገቡበት የሥነ-ሕንፃ ትምህርት ክፍል ሰዎች ይህን ቢሰሙ ይኼ ሰውዬ አበዛው ማለታቸው አይቀርም። ፑሊያኖ ግን ነገሩ ወዲህ ነው ይላል። የህንፃ ዲዛይኖች በቀላሉ የኢንተርኔት አውታር ላይ በሚገኙበት ዓለም ላይ እንዴት ሆኖ ነው 'አርክቴክቶች' በጣም ተፈላጊ ናቸው የምንለው የሚል መከራከሪያ በማቅረብ።
ተስፋ ቢጤ ግን ጣል ሳያደርግ አላለፈም። እጅግ የተለየ ጥበባዊ ሥራ የሚሠሩ 'አርክቴክቶች' የማይደገም ዲዛይን ሊሠሩ ስለሚችሉ ተስፋ አላቸው ይላል ፑሊያኖ።
አካውንታንቶች [የሒሳብ ሰራተኞች]
በጣም ውስብስ የሆኑ ፈተናዎችን መመፍታት የሚችሉ አካውንታንቶች እንኳ ችግር የለባቸውም፤ ነገር ግን የተለመዱ ሥራዎችን የሚሠሩ የአካውንቲንግ ባለሙያዎች በገበያው የመፈለጋቸው ነገር አስጊ ነው።
የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጦር አውሮፕላን አብራሪዎች
አሁንም እያየነው እንዳለነው ሃገራት ሰው አልባ የጦር አውሮፕላኖችን በመጠቀም ላይ ናቸው። ይህ ደግሞ ወደፊትም የሚቀጥል እንጂ የሚቆም አይደለም።
ፖሊስ እና መርማሪ
እኚህ ሙያዎችም መቼም አይጠፉም፤ ነገር ግን አስፈላጊነታቸው እየመነመነ እንጂ እየጨመረ አይመጣም። በምትኩ በተለይ ያደጉ የሚባሉ ሃገራት እጅግ የረቀቁ መሣሪያዎችን በመጠቀም ወንጀልን መከላከል ይመርጣሉ።
ድለላ
ድለላ መቼም የማይነጥፍ ሥራ ሊመስለን ይችላል፤ ቢሆንም የምንፈልጋቸውን ዕቃዎች እና አገልግሎቶችን ይዘው በኮምፒውተር መስኮቶቻችን ብቅ የሚሉ ድረ-ገፆች ተበራክተዋል። እርግጥ በይነ-መረብን ተጠቅመው የሚደልሉ ላይጠፉ ይችላሉ፤ እንደቀደመው ጊዜ ግን በእግር መንከራተቱ የሚያበቃለት ይመስለኛል ሲል ይተነብያል።
ፑሊያኖ ከላይ የጠቀሳቸው መስኮች አደጉ በሚባሉ ሃገራት የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸው ናቸው ይባሉ እንጂ በጊዜ ሂደት በማደግ ላይ ወዳሉ ሃገራት መምጣታቸውን መገመት ግን የሚከብድ አይመስልም፤ ዘመኑ የቴክኖሎጂም አይደል!