ያንክሲ ፓላስ፡ በ2018 በጉግል ላይ በብዛት የተፈለገው የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማ

የ ያንክሲ ፓላስ ገፀ ባህርያት

የፎቶው ባለመብት, IQiyi

በፍቅር፣ በጥላቻ፣ በበቀል፣ በግድያ የተሞላ ድራማ ነው፤ ጨቅላ ህፃናት ሲገደሉ ጭምር ይታይበታል። የቻይናው የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማ።

ይህ ያንክሲ ፓላስ የተሰኘ ተከታታይ ድራማ በዚህ አመት በዓለም ላይ እጅጉን በጉግል ማሰሻዎች ላይ የተፈለገ ሆኗል። የዚህ ተቃርኖ ሆኖ እጅን በአፍ ያስጫነው ነገር ደግሞ በቻይና ጉግል የታገደ መሆኑ ነው።

ስለድራማው ለማንበብ ብዙ የፈለጉት ከሲንጋፖር፣ ማሌዢያ፣ብሩኔ እና ሆንክ ኮንግ ያሉ ኤስያውያን ሲሆኑ በቻይና ያለው ተወዳጅነትም ከአድናቆት በላይ ነው።

የፎቶው ባለመብት, IQiyi

ድራማው በቴሌቪዥን ከመተላለፉ በፊት በድረገፅ ላይ ነው የተሰራጨው።

የድራማው አዘጋጅ የነበረውና ለህዝብ እንዲደርስ ያደረገው ደግሞ የቻይናው ኔትፍሊክስ አይ ኪዪ ነው።

ይህ በቻይና ተደራሽነቱም ስሙም የገዘፈ ኩባንያ ድራማው ለበርካቶች እንዲደርስና ዝነኝነቱ እንዲጨምር የራሱን አስተዋፅኦ እንዳደረገ ተነግሯል።

በቻይና በሚገኙ እንደ አይ ኪዪ ያሉ ትርኢቶችን ማሰራጫ (የቻይናው ኔት ፍሊክስ ) ድረ ገፆች 15 ቢሊዮን ሰዎች ያዩት ሲሆን ይህ የሆነው ደግሞ በቴሌቪዥን ጣቢያዎች ላይ መተላለፍ ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ነው።

ይህም ባለፈው ክረምት ለ 39 ተከታታይ ቀናት በኢንተርኔት ከታዩ ሁሉ ከፍተኛ ቁጥርን እንዲይዝ አስችሎታል።

70 ክፍል ያሉት ይህ ድራማ በ1700 ያለ ንጉሳዊ ቤተሰብ መካከል ያለን የስልጣን ሽኩቻ ያሳያል።

በቻይና ቴሌቪዥንም ሆነ ሬዲዮ የሚቀርቡ ትርኢቶች የመንግሥትን ይሁንታ ማግኘት ብቻ ሳይሆን በሚገባ ታይተው ይበጠራሉ።

የቴሌቪዥን ስራዎች ከመቀረፃቸው በፊት የሚታዩ ሲሆን ተበጥረውና ተብጠርጥረው ነው ወደ ስራ የሚገቡት።

ለዚህ የቴሌቪዥን ድራማ ግን ይህ እጣ ቀንሶለታል።

ድራማው የተሰራው ገና የዝና ማማ ላይ ባልወጡ ተዋንያን ነው። የረዳት ገፀባህርይ ሚናን ወስዳ ከተጫወተችው የሆንግ ኮንጓ ተዋናይቷ በቀር ማንም ስም አለኝ የሚል ከመካከላቸው አይገኝም።

ስለዚህ በክፍያ ደረጃም የስማቸውንና የሚናቸውን ያህል አነስ ያለ ክፍያ ነበር የተዋዋሉት። ስለዚህ ይህንን ተከታታይ ድራማ ለመስራት የወጣው ወጪ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም።

የተመልካችን ቀልብ ሰቅዞ የያዘው ሌላው ነገር ለተዋንያኑ አልባሳት፣ ለትርኢቱ መቼትና ሜካፕ የተሰጠው ትኩረት እንደሆነም የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ።

ስለዚህ ድራማ ሰምተው የማያውቁ ከሆነ ይኸው ነገርንዎ፤ በሉ ተጨማሪ ለማንበብ እርስዎም የድርሻዎን ጉግል ያድርጉ። የመጀመሪያው አይሆኑም።