"ሕዝብ እንዲጠይቅ አድርገናል፣ በተቋሙ ላይ እምነት ማሳደር እንዲችልም ሞክረናል" ዋና ኦዲተር

ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ

የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር የሆኑት አቶ ገመቹ ዱቢሶ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ የመሥሪያ ቤቱ እንቅፋት ካሏቸው መካከል ብቃት ያለው ባለሙያ ፍልሰት ይገኝበታል።

"የቁጥር ችግር ባይኖርብንም፤ ብቁ የሰው ሀብት እጥረት ፈተና ሆኖብናል" የሚሉት ዋናው ኦዲተሩ፤ በኦዲት ሙያ የተካነ ብቁ ሰው አለመገኘቱና ከተገኘም መሥሪያ ቤቱን ቶሎ መልቀቁ ፈተና እንደሆነባቸው በአፅንኦት ገልጸዋል።

ብቃት ያለው ባለሙያ ፍልሰት በሥራው ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደረ ያስረዱት ዋና ኦዲተሩ፤ የሚሰማራው የሰው ሀይል በሚፈልጉት የብቃት ደረጃ ላይ ያለመሆኑን ችግር ለመቅረፍ የራሳቸውን ማሰልጠኛ ለማቋቋም እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ተናግረዋል።

ዋና ኦዲተሩ፤ ከሕግ ማዕቀፍና ከደረጃ አንጻር የተሟላ የሕግ ማዕቀፍና ደረጃ እንዳላቸው በመግለጽ፤ "ሥራችንን እንዳንሠራ የከለከለን መሰረታዊ ነገር የለም" ብለዋል።

በአቶ ገመቹ ገለጻ፤ የመሥሪያ ቤቱ ሪፖርት ውጤት ላይ የማይውልበት ጊዜ መኖሩ ሌላው መሰናክል ነው። "ሥራችን ኦዲት አድርጎ ሪፖርት ማቅረብ ብቻ አይደለም" ብለው፤ ሪፖርታቸው ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን እንዳለበት ያብራራሉ።

መሥሪያ ቤቱ የሚያቀርበው የኦዲት ሪፖርት አሰራር ላይ፣ ሀብት አጠቃቀም ላይ እንዲሁም አፈፃፀም ላይ ውጤት ማምጣት እንዳለበት ይገልጻሉ።

"በኦዲት ሪፖርቱ መሰረት የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ ረገድ እኛ በምንፈልገው መልኩ እየሄደ አይደለም። ይህ መሰረታዊ ችግር ነው። ሥራችን ውጤት ካላመጣ እርባና የለውም።"

ሪፖርትን ውጤታማ ማድረግ ከኦዲት መሥሪያ ቤቱ አቅም ውጪ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ገመቹ፤ ችግሩ በምክር ቤትና በመንግሥት ደረጃ መፈታት እንዳለበት ይመክራሉ።

ውጤታማ መሆን ለሥራቸው ማበረታቻና ማትጊያ መሆኑን ገልጸው፤ የኦዲት ሪፖርታቸውን ተመርኩዘው የማስተካከያ እርምጃ በማይወስዱ ተቋማት ላይ እርምጃ እንዲወሰድም ያሳስባሉ።

"እርምጃ ካልተወሰደ ሌሎች ተቆሞችን ተመሳሳይ መንገድ ካለመከተል የሚገድባቸው ነገር የለም፤ ምክንያቱም ማንም ተጠይቆ አላዩም።"

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች ጥሩ መሆናቸውን የሚናገሩት ዋና ኦዲተሩ፤ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች ሲገመገሙ አንዱ የመገምገሚያ ነጥብ ተደርጎ የተወሰደው የኦዲት ማስተካከያ እርምጃ መውሰድ መሆኑና ማስተካከያ ያላደረጉ ከፍተኛ ነጥብ እንዲያጡ መደረጉ ተስፋ ሰጭ ነው ይላሉ።

"መንግሥት እየወሰደው ያለው ተጠያቂነትን የማረጋገጥ እርምጃ ተስፋ ሰጪ ነው። እስካሁን የነበረው ጫጫታ ነበር። አሁን ግን ተግባራዊ እርምጃ እየተወሰደ ነው። ስለዚህ እስካሁን ፈተና የሆኑብን ነገሮች ሊቀረፉ ይችላሉ ብዬ ነው የማስበው"

ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ተመሳሳይ ሪፖርት ማቅረባቸውን የሚያስረዱት ዋና ኦዲተሩ፤ ከዓመት ዓመት ለውጥ አለመታየቱን ያስገርጣሉ። ሆኖም በ2011 በጀት ዓመት ሂሳብ ሪፖርት መሰረታዊ ለውጥ ይመጣል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ።

"መንግሥት አሁን እያሳየ ያለውን ቁርጠኛ አቋም የሚቀጥልበት ከሆነ በሁሉም ደረጃ መሰረታዊ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል" ብለው አቶ ገመቹ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

እስካሁን መሰረታዊ የሚሉት ለውጥ ባያዩም፤ ተቋማት ላይ የተጠያቂነት ፍራቻ ማየታቸውን ጥሩ ጅማሮ ነው ይሉታል።

"እስካሁን ለውጥ አልታየም። ለውጥ ነው ማለት ቢከብደኝም ትንሽ ፍራቻ አያለሁ። ይህንን ሁለት ዓመት ገደማ 'ተጠያቂነት ወደ እኛ እየመጣ ነው' የማለት ፍራቻ አለ። ይህ ለውጥ ባይሆንም ወደ ለውጥና መሻሻል ይወስደናል" በማለት ለውጥ ለማድረግ የሚጣጣሩ ግለሰቦች መበረታታት እንዳለባቸው ይናገራሉ።

የተወካዮች ምክር ቤት በተደጋጋሚ የሂሳብ ኦዲት ሪፖርት ላይ ክፍተት የተገኘባቸውን ጠርቶ እያነጋገረ ነው ያሉት ዋና ኦዲተሩ፤ ምን እርምጃ እንደወሰዱና እያከናወኑ ያሉትን እየተከታተለ ነው በማለት እየታየ ያለውን ለውጥ ያስረዳሉ።

ኦዲተሩ አክለውም፤ "ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የኦዲት ጉዳይ እየተነሳ እየተመከረ፣ ገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር መርሃ ግብር አዘጋጅቶ እርምጃ መውሰዳቸውን አጣርቶ ሪፖርት እንዲያቀርብላቸው የሚኒስትሮች ምክር ቤት እየጠየቀ ነው። ይህ የሚያበረታታ ቢሆንም፤ በተጨባጭ መሬት ላይ እርምጃ መውሰድ ላይ ያለው ነገር ዘገምተኛ ነው" ብለዋል።

ዋናው ኦዲተር መስሪያ ቤት፤ ለዜጎች እሴት ጨማሪ ሪፖርት የሚያቀርብና በአፍሪካ ደረጃ ምርጥ ከሚባሉት ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቶች አንዱ መሆን እንደሚፈልግ አቶ ገመቹ ይናገራሉ።

መሥሪያ ቤቱ የሚያደርገው ኦዲት ወደ ጠንካራ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ስርዓት እንዲያደርስ እንደሚፈልጉም አክለዋል።

በተጨማሪም ግልፅነትና ተጠያቂነት ወደ መልካም አስተዳደር ግንባታ እንዲሁም ወደ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ግንባታ እንዲወስድ እንደሚፈልጉ የሚናገሩት ዋና ኦዲተሩ፤ መሥሪያ ቤቱ ለዚህ ጉልህ አስተዋፅኦ የሚያደርግ ነፃና ገለልተኛ፣ ንቁና ሙያዊ ስነ ምግባሩን የጠበቀ ተቋም ሆኖ እንዲገነባ ያላቸውን ፍላጎት ለቢቢሲ አስረድተዋል።

"መሥሪያ ቤቱ ይህን ራዕይ ይዞ እየሰራ ነው" የሚሉት ዋና ኦዲተሩ፤ ይሳካል የሚል እምነትም አላቸው። "አሁን ሕዝብ እንዲጠይቅ አድርገናል" ብለውም፤ ሕዝብ በተቋሙ ላይ እምነት ማሳደር እንዲችል እየሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሥራቸው ተጠናክሮም ሕዝብ የኔ ብሎ የሚተማመንበት ተቋም ሆኖ ማየት እንደሚሹ ተናግረዋል።