ዐቢይ አሕመድ ለምን ወደ አምቦ አቀኑ?

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በአምቦ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት

የፎቶው ባለመብት, Office of the PM

የምስሉ መግለጫ,

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በአምቦ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት

ዛሬ ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ገደማ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድን የያዘች ሄሊኮፕተር አምቦ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ሳይተሰብ አረፈች። የጠቅላይ ሚንስተሩን ጉብኝት ያልተጠበቀ እንደመሆኑ ተማሪዎቹን እጅጉን አስደንቋል።

የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽሕፈት ቤትም ዐቢይ አሕመድ ከተማሪዎቹ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተማሪዎቹ እምቅ ችሎታቸውና የወደፊት ዕድሎቻቸውን በመገንዘብ ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ የሚያነቃቃ መልእክት አስተላልፈዋል ብሏል።

በዚህ የዐቢይ አሕመድ አጭር የአምቦ ቆይታ የ12ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው የሮስ ሄዪ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ጥያቄ የማቅረብ ዕድሉን አግኘቶ ነበር።

የማለዳውን ጉብኝት በተመለከተም ለቢቢሲ እንደተናገረው ''የጉብኝት በጭራሽ ያልጠበቅነው ነበር" ብሏል።

"...እንደተለመደው ከጠዋት ሰልፍ በኋላ ወደ ክፍል ገባን፤ የመጀመሪያውን ክፍለ ጊዜ ከጨረስን በኋላ ጠቅላይ ሚንስትሩ እየመጡ መሆኑን ተነግሮን ሰልፍ የሚወጣበት ሜዳ ላይ ሆነን ጠበቅናቸው።'' ይላል።

ጠቅላይ ሚስትሩ ለተማሪዎች ያደረጉት ንግግር ጠቅላል ሲደረግ 'እናንተ [ተማሪዎች] ትምህርታችሁ ላይ ብቻ ትኩረት አድርጉ፤ ፖለቲካውን ለእኛ ተዉት' የሚል ይመስላል ይላል፣ የሮስ።

ተማሪ የሮስ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ያነሳላቸው ጥያቄ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርሱ ዕድሜ የሚገኙ እኩዯቹ ላይ የሚብሰለሰል አንኳር ጥያቄን አዝሏል። "ለምን ትከፋፈላላችሁ?"

የተማሪውን ፍላጎት ያንጸባረቅኩበት ጥያቄ ነው ያነሳሁላቸው የሚለው የሮስ የጥያቄው ጭብጥ የሚከተለው ነበር፤

''ለአንድ ሕዝብ የምትታገሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነታችሁ ለምን ሰፋ? በእናንተ የፖለቲካ ፍላጎት ልዩነት ሳቢያ የኦሮሞ ሕዝብ እየተጎዳ እና እየሞተ ነው ያለው። ይህን ለውጥ እንድንመለከተው የአምቦ ተማሪ ብዙ መስዕዋትነት ከፍሏል። በመንግሥት እና በኦነግ መካከል አሥመራ ላይ የተደረስውን ስምምነት ዝርዝር እንዲሁም አሁን የተፈጠረውን ልዩነት በግልጽ ማወቅ አለብን፤ ብዙዎች መስዋእት የሆኑት እውነትን ፍላጋ ነው፤ አሁንም እውነትን ነው የምንሻው'' ሲል ነበር ጥያቄውን የቋጨው።

ይህ የተማሪ የሮስ ጥያቄ የአምቦ ተማሪዎች አእምሮ ላይ ብቻ የሚንከላስ አይደለም። የአካባቢው ነዋሪም ከመጋረጃ ጀርባ እየሆነ ስላለው ፖለቲካዊ ሽኩቻ ፍንጭ እንዲኖረው ይሻል።

ዐቢይ አሕመድ አምቦ መሄድ ለምን አስፈለጋቸው?

ቢቢሲ ከአምቦ ከተማ ነዋሪዎች ባገኘው መረጃ እንዳረጋገጠው፤ በከተማዋ ከዛሬ ሰኞ ጀምሮ በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ተጠርቶ ነበር።

የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ከዛሬ ጀምሮ ሳምንቱን ሙሉ እንዲዘልቅ የታሰበው በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ የተጠራው በከተማዋ ውስጥ በስፋት ተበትኖ በነበረ በራሪ ወረቀት ነው። ዓላማውም ከሰሞኑ በመንግሥትና በኦነግ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት መቃወም ነበር። ኾኖም ስማቸውን የማንጠቅሳቸው አንድ የከተማዋ ነዋሪ የአድማውን ጥሪ አልሰመረም፤ "ሁሉም ወደ ሥራው ወጥቷል'' ይላሉ።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአምቦ በቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማ ሲከናወን ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ የመንግሥት እና የንግድ ተቋማት አገልግሎት አይሰጡም ነበር። ከተማዋን አቋርጦ የሚያልፍ ተሽከርከሪም እምብዛምም አይስተዋልም።

ይህን ጠንቅቆ የሚገነዘበው የከተማዋ ነዋሪ እንዲህ ዓይነት አድማዎች ከመታወጃቸው በፊት ባሉ ቀናት የሚያስፈልገውን መሠረታዊ ፍጆታ ሽምቶ ከቤቱ የማኖር ልማድን አዳብሯል። በዚህኛው የአድማ ጥሪ ግን ይህ እምብዛምም አልተስተዋለም። ምናልባት ክስተቱ ይህ የአድማው ጥሪ በብዙኃኑ ቅቡልነቱ ዝቅተኛ እንደነበር አንድ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

ለቢቢሲ አስተያየቱን የሰጠ የአምቦ ከተማ ነዋሪ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአምቦ ጉብኝት ከተጠራው አድማና ከወቅቱ ሁኔታ ጋር ያገናኘዋል። ''ጠቅላይ ሚንስትሩ ተቃውሞ ሳይነሳ በፍጥነት ነገሩን ለማብረድ በማሰብ እንደመጡ እናምናለን'' ይላሉ።

ተማሪ የሮስንም ከዚሁ የተለየ ግምት የለውም። "እንዲሁ የጠቅላይ ሚንስትሩን ያልተጠበቀው ጉብኝት በአምቦ ሊነሳ የሚችለውን ተቃውሞ ለማምከን ያሰበ ይመስለኛል" ይላል።

''የተማሪው ጥያቄ በመንግሥት እና በኦነግ መካከል ያለው ልዩነት አንድም ጥይት ሳይተኮስ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል የሚል ነው።'' የሚለው የሮስ ''ጠቅላይ ሚንስትሩ ለጥያቄዎቻችን ምላሽ የማይሰጡ ከሆነ የአምቦ ተማሪ እጁን አጣጥፎ ይቀመጣል ማለት ግን አይደለም።'' ይላል።