"ህልም ያላቸው ወጣቶች ድህነትን ከላያቸው ላይ ነቅለው መጣል ይችላሉ" የጠብታ አምቡላንስ ባለቤት

የጠብታ አምቡላንስ

የፎቶው ባለመብት, Kibret Abebe

ከ20 ዓመት በላይ ከባሌ- ጊኒር እስከ ጥቁር አንበሳ በመንግሥት ሥራ ተቀጥረው ሠርተዋል፤ ከነርስነት እስከ አኔስቴዢያ ባለሙያነት (የማደንዘዣ ህክምና) አገልግለዋል። አቶ ክብረት አበበ የሥራ ሕይወት የጀመረው እንዲህ ነው።

አቶ ክብረት የመጀመሪያው የግል አምቡላንስ ጠብታን የመሰረቱ ግለሰብ ናቸው። ለ17 ዓመታት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በማደንዘዣ ህክምና ክፍል ውስጥ ሲሰሩ ያዩት ነገር ጠብታን በውስጣቸው እንዲፀንሱ አደረገ።

ይሰሩበት የነበረው ጥቁር አንበሳ በአዲስ አበባ መሃል ላይ የሚገኝ ትልቅ ሆስፒታል ነው፤ ማንም ሰው ታሞ ከጥቁር አንበሳ የሚቀር አይመስልም ነበር።

ወደዚህ ስሙም አገልግሎቱም የገዘፈ ሆስፒታል መኪና የገጨው፣ ደም የሚፈሰው፣ መተንፈስ የተቸገረ ወዘተርፈ ሁሉ ይመጣል።

"ማንም ሰው አጠገቡ ሌላ ሆስፒታል ቢኖር እንኳ ጥቁር አንበሳ የመጀመሪያ ምርጫው ይመስል ነበር" ይላሉ የነበረውን ሁኔታ ሲያስታውሱ።

በ2001 ዓ. ም. የወጣ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በየ10 ሺህ መኪናው 194 ሞት ይከሰታል። የመኪና ፈጣሪና ፈብራኪዎች ጃፓኖች ጋር ግን በ20 ሺህ መኪኖች አንድ ሰው ብቻ በመኪና አደጋ ይሞታል።

ከሁሉም የከፋው ይላሉ አቶ ክብረት፤ "የተገጨው ግለሰብ በታክሲ ወይም በገጨው መኪና ወንበር ላይ የወሳንሳ አንስተው ጭነውት እያርገፈገፉ መማምጣታቸው ነው"።

የፎቶው ባለመብት, kibret Abebe

ሕክምና የሚጀመረው ሆስፒታል አይደለም

መኪኖቹን አምርተው የላኩት ሳይሞቱ የእኛ የተቀባዮቹ ሞት የሚያሳየው ጥንቃቄ እንደጎደለን ነው የሚሉት አቶ ክብረት፤ እንዴት መኪና አደጋ የደረሰባቸውን ሰዎች ማትረፍ እችላለሁ? የሚለው ጥያቄ ለሥራቸው መነሻ እንደነበር አይዘነጉም።

በድንገተኛ አደጋ ወደ ሆስፒታል የሚሄድ ሰው በቀጠሮ ወደ ሆስፒታል እንደሚሄድ ሰው አይደለም የሚሉት አቶ ክብረት፤ የድንገተኛ ህክምና አሰጣጥ ችግርን ዓለም እንዴት ፈታው? ብለው ማጥናት ጀመሩ።

ማኅበረሰቡ ድንገተኛ አደጋ የደረሰበትን ሰው ደም ለማቆም፣ ትንፋሽ ለመስጠትና የበለጠ ሳይጎዳና ህይወቱ አደጋ ላይ ሳይወድቅ ወደ ሆስፒታል ማድረስ ያለበት እንዴት ነው? የሚለውን ሲያሰላስሉ የጠብታ አምቡላንስ ሀሳብ መጣላቸው።

ይህንን ሀሳባቸውን ከባልደረቦቻቸው ጋር ሲያወሩ፤ ሁልጊዜም የሚነግሯቸው በድንገተኛ አደጋ የተጎዱ ሰዎችን ህይወት ለማዳን መሥራት ያለበት መንግሥት እንደሆነ ነው።

እሳቸው ግን፤ መንግሥት ሲባትል የሚውልበት ነገር ብዙ ነው፤ ይህንን ስራዬ ብሎ ላያየው ይችላል። ስለዚህ አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ ብለው ተነሱ።

"ከመላ ሀገሪቷ ትንፋሽ ያጡ ሰዎች ወደ ጥቁር አንበሳ ሲመጡ፤ እኛ የሞት ሰርተፊኬት እንደፃፍን መኖር የለብንም፤ ለውጥ መምጣት አለበት"

የመልካም አጋጣሚና እድል ቀጠሮ

በዚህ መካከል ከለንደን ለሥራ የመጡ አንድ ሰው የመተንፈስና የደም ዝውውር ችግር ገጥሟቸው ወደ ለንደን በፍጥነት ሄደው መታከም እንዳለባቸው ተነገረ።

ያኔ አቶ ክብረትንና ለድንገተኛ አደጋ ህክምና ያላቸውን ፍላጎትና ዝግጁነት የሚያውቁ እርሳቸው ከታካሚው ጋር አብረው እንዲሄዱ ጠቆሙ።

ከዛም ወደ ለንደን ታካሚውን ይዘው ሄዱ፤ ለንደን አየር ማረፊያ ሲደርሱ ታካሚውን ለመቀበል የጠበቃቸውን ሲያዩ "አንድ አገር አንድ ሰው ነው" አሉ ለራሳቸው።

ኢንቨስተር መሆን ይፈልጉ ስለነበር አንድ ቀን አምቡላንስ የምገዛበት በማለት የቁጠባ ሂሳብ ከፍተው ለሰባት ዓመት ይቆጥቡ እንደነበር የሚናገሩት አቶ ክብረት፤ የቆጠቡት ገንዘብ እንኳን አምቡላንስ ጎማውን የሚገዛ እንዳልነበር ያስታውሳሉ።

በሆስፒታል ሲሠሩ የተመለከቱትን የድንገተኛ አደጋ ህክምና ክፍተት ለመሙላት የራሳቸውን ጠብታ ጠብ ማድረግ የፈለጉት አቶ ክብረት የባንኮችን ደጃፍ መቆርቆር ጀመሩ።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

የጠብታ አምቡላንስ ባለቤት ምክር ለስራ ፈጣሪ ወጣቶች

የትኛውም ባንክ ሊጀምሩ የፈለጉትን ሃሳብ ከሶስት ደቂቃ በላይ ለመስማት አለመፈለጉን የሚናገሩት አቶ ክብረት፤ "እንዴት ገንዘብ እንደምታመጣና እንዴት እንደምትከፍለን በሚገባ አላስረዳህም" ስለተባሉ ሌላ አማራጭ መፈለግ ጀመሩ።

የቀራቸው አማራጭ አራስ ልጅ ታቅፈው ጥሪቴ ሀብቴ ብለው የሚኖሩበትን ቤት መሸጥ ነበር። ከባለቤታቸው ጋር ተነጋግረው የዛሬን ሳይሆን የነገን አስበው ሸጡት።

ወዲያውኑ ወደ ዱባይ አቅንተው ሶስት አሮጌ መኪኖችን በመግዛት ወደ አምቡላንስ አስቀይረው መጡ።

አምቡላንሶቹ ከቀረጥ ነፃ የገቡ ቢሆንም ለትራንስፖርት ሚኒስቴርና ለጉሙሩክ የሚከፈለውን ገንዘብ መክፈል ስለነበረባቸው መኪናቸውን ጨምረው ሸጠዋል።

ሁሌም በተግዳሮት ውስጥ መኖር

አቶ ክብረት ፈተናው ግን አምቡላንስ መግዛቱ ብቻ አልነበረም ይላሉ። ከለንደን እንደተመለሱ ሥራቸውን በመልቀቅ የአምቡላንስ አገልግሎት መጀመር እንደሚፈልጉ ተናገሩ።

ሆኖም የወቅቱ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሰዎች "በጎ አድራጎት ድርጅት ብትሆን እንደ ቀይ መስቀል አይነት ፈቃድ መስጠት ይቻላል። ካልሆነ የግል ክሊኒክ ወይንም ሆስፒታል ነው መክፈት ያለብህ እንጂ፤ ለግል አምቡላንስ ተቀመጠ ምንም አይነት መስፈርት የለም" አሏቸው።

ስድስት ወር መሉ በየቢሮው በመግባትና ሀሳቡን በማስረዳት የራሳቸው 17 ገፅ ስታንደርድ በመፃፍ እና በማስገባት ፈቃድ ማግኘት ቻሉ።

"የድንገተኛ አገልግሎት ልቡ የጥሪ ማዕከሉ ነው" የሚሉት አቶ ክብረት፤ ሥራ ሲጀምሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ያጓጓዙት አብራቸው ትሰራ የነበረች አንዲት ነርስ እናት ታመው ወደ ቤተ-ዛታ እንደሆነ ያስታውሳሉ።

"ስለሥራችን የሚያውቅ ማንም አልነበረም። የግል ስልኬን ነበር እንደ ጥሪ ማዕከል የምጠቀመው"

በግል ዘርፉ ነጋዴው በየሰከንዱ ከተግዳሮት ጋር ነው የሚሰራው የሚሉት አቶ ክብረት፤ "የግሉ ዘርፍ ነጋዴ ነው። ነጋዴ ደግሞ ሌባ ነው የሚል አመለካከት ተንሰራፍቶና ተስፋፍቶ በሚገኝበት ማኅበረሰብ ውስጥ መሥራት ፈተናውን ያከብደዋል" ይላሉ።

በአስር ዓመት የስራ ህይወታቸው የገጠሟቸው ተግዳሮቶች ከራስ ፀጉር እስከ እግር ጥፍር ናቸው ይላሉ። ሆኖም በብርታት ያቆሟቸውን ሦስት ነገሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ለመጀመር ለሚያስቡ ሰዎች ያካፍላሉ።

  • በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ውስጥ ሊያስቆሙ የሚችሉ የተለያዩ ሰዎች ስለሚገጥሙ ላለመቆም ለሚሠሩት ሥራ አትኩሮት መስጠት
  • አትኩሮት ለሠጡት ነገር ቁርጠኛነት ማሳየት
  • ለምንሠራው ነገር ጥልቅ ፍቅር ከሌለ አለመስራት እና ጊዜ አለማጥፋት ተገቢ ነው ሲሉ ይመክራሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ ሃሳብ ያለው ሰው በፍፁም ትርፍ አላገኝበትም በማለት በጎ አድራጎት ድርጅት ይከፍታል ወይም ሀሳቤ ሁሉ ትርፍ በትርፍ ያደርገኛል በማለት ንግድ ያቋቁማል የሚሉት አቶ ክብረት፤ በዚህ መካከል ተፅዕኖ ፈጥሮ የሚገኝ ትርፍ ላይ ሕግም ማበረታቻም የለም በማለት በመንግስት በኩል ካሉት ተግዳሮቶች መካከል አንዱን ያነሳሉ።

ጠብታ ዛሬ

የፎቶው ባለመብት, kibret Abebe

"እያንዳንዳችን በምናየውና በምናዋጣው ጠብታ ልክ የኢትዮጵያን ችግር ብሎም የአፍሪካን እንደፍናለን" የሚሉት አቶ ክብረት ጠብታ ከተቋቋመ ጀምሮ ከ 65 ሺህ በላይ ሰዎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ማመላለሱን ይናገራሉ።

"ተፅዕኖ አምጥተን፤ ችግራችን ፈተን ትርፍ ማግኘት ነው ምንፈልገው" የሚሉት አቶ ክብረት፤ ጠብታ ድርጅታቸው ብቻ ሳይሆን የሕይወታቸው ፍልስፍናም እንደሆነ ያስረዳሉ።

ለ10 ዓመት ያህልም የራሳቸውን ጠብታ በዚህ ፍልስፍና መሰረት መወጣታቸውን በኩራት ይናገራሉ።

በሦስት አምቡላንሰ የተጀመረው የጠብታ አምቡላንስ ጉዞ ዛሬ 13 አምቡላንስ ደርሷል።

ሦስቱ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ያሟሉ እንደሆኑ የነገሩን አቶ ክብረት፤ በውስጣቸው የልብ ምት ማስነሻ ያላቸው፣ ኦክስጅን አቅርቦት የተሟላላቸው፣ ከኤር ላይ ኦክስጅንን ተቀብሎ ማዘዋወር የሚችሉ ናቸው ይላሉ።

በቅርቡም አስመራ ድረስ ታካሚ እንዳጓጓዙ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ ጠረፍ ድረስ ህሙማንን አጓጉዘው እንደሚያውቁ ይናገራሉ። አቶ ክብረት "ህልማችን በምስራቅ አፍሪካ በድንገተኛ ህክምና የልቀት ማዕከል መሆን ነው" ብለዋል።

በ10 ዓመታት የጠብታ አምቡላንስ አገልግሎት ውስጥ ከ45 ሺህ በላይ ሰዎችን በድንገተኛ ህክምና አሰጣጥን አሰልጥነዋል። 20ሺዎቹ የትራፊክ ፖሊሶች ሹፌሮች ሲሆኑ የመጀመሪያውን ፓራ ሜዲክ ኮሌጅም ከፍተዋል።

"የማኅበራዊ ሥራ ፈጣሪ እንደመሆኔ መፍታት የምፈልገው ማኅበራዊ ችግርን ነው" የሚሉት አቶ ክብረት፤ በኮሌጃቸው ገንዘብ ከፍለው መማር የሚችሉ ሳይሆን የመማር አቅም እያላቸው ነገር ግን መክፈል የማይችሉትን ወጣቶች እንደሚያስተምሩ ይናገራሉ።

ለዚህም ከሌሎች ገንዘብ ካላቸው ወገኖች ጋር በመሆን እና እነዚህን ወጣቶች አስተምሮ ሥራ ሲይዙ እንዲከፍሉ በማድረግ የእነርሱ ክፍያ ቀጣይ ተማሪዎችን እንዲያስተምር የሚያስችል እቅድ ነድፈው እየሰሩ መሆኑን ያስረዳሉ።

አሁን ከአንድ የኖርዌይ ድርጅት ባገኙት የገንዘብ ድገፍ 15 ልጆች ስልጠና እየወሰዱ መሆኑን ነግረውናል።

በተመረጡ አምስት ክልሎች የአምቡላንስ አገልግሎት ለመጀመርናና ኮሌጁን ለማስፋት እቅድ መያዛቸውን የገለፁት አቶ ክብረት፤ ከተለያዩ የባህር ማዶ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በመነጋገር በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ 5ሺህ የሚሆኑ ወጣት ፓራ ሜዲኮችን ለማሰልጠን አቅደዋል።

እነዚህ ወጣቶች መክፈል የማይችሉ ግን ተምረው ስራ ይዘው የሚከፍሉ እንደሚሆኑም ይናገራሉ። ኢትዮጵያ ወደ 24 ሺህ ፓራ ሜዲኮች ትፈልጋለች በማለትም ሀሳባቸውን ይቋጫሉ።