ሚሼል ኦባማ በአሜሪካ እጅግ ተወዳጇ ሴት ተባሉ

ሚሼል ኦባማ

የፎቶው ባለመብት, PA

የቀድሞዋ የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ በአሜሪካ እጅግ ተወዳጇ ሴት ተብለዋል። ላለፉት 17 ዓመታት የአሜሪካ ተወዳጅነት ማዕረግን ያገኙት ሂላሪ ክሊንተን ነበሩ።

በተወዳጅ ሴቶች ዝርዝር ውስጥ የቶክ-ሾው አዘጋጇ ኦፕራ ዊንፍሬይ ሁለተኛ፤ ሂላሪ ክሊንተን ደግሞ ሦስተኛ ሆነዋል። የእንግሊዟ ንግሥት ለ50ኛ ጊዜ በዝርዝሩ ምርጥ 10 ውስጥ ገብተዋል።

የቀድሞው ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ለ11 ዓመታት ያህል የተወዳጆች ዝርዝርን በአንደኛነት ሲመሩ ነበር። ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለአራት ዓመታት በዝርዝሩ ሁለተኛ ነበሩ።

ከአውሮፓውያኑ 1946 ጀምሮ በየዓመቱ መሰል ጥናት ሲካሄድ፤ አሜሪካውያን የሚወዷቸውን እንዲሁም የሚያደንቋቸውን ሰዎች ይመርጣሉ።

ዘንድሮ በጥናቱ የተሳተፉት 1,025 ግለሰቦች፤ በዓለም ላይ ካሉ ሰዎች የሚያደንቁትን እንዲመርጡ ተደርጓል። አጥኚው አካል ጋሎፕ ባወጣው መረጃ መሰረት፤ ተወዳጅ ወንዶችና ሴቶች ተከታዮቹ ናቸው።

እጅግ የሚወደዱ ሴቶች

  • ሚሼል ኦባማ - 15%
  • ኦፕራ ዊንፍሬይ - 5%
  • ሂላሪ ክሊንተን - 4%
  • ሜላንያ ትራምፕ - 4%
  • ንግሥት ኤልሳቤት ሁለተኛ- 2%

እጅግ የሚወደዱ ወንዶች

  • ባራክ ኦባማ - 19%
  • ዶናልድ ትራምፕ- 13%
  • ጆርጅ ደብሊው ቡሽ - 2%
  • ፖፕ ፍራንሲስ - 2%
  • ቢል ጌትስ- 1%

ሂላሪ ክሊንተን ያለፉትን 17 ዓመታት ጨምሮ፤ 22 ጊዜ ዝርዝሩን በበላይነት ጨርሰዋል። ኦፕራ ዊንፍሬይ በዝርዝሩ በበላይነት ባይሆንም ለ14 ዙር በሁለተኛነት አጠናቀዋል።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ድዋይት ኢሰንሆር 12 ጊዜ በጣም ተወዳጅ ሰው በመሆን ቀዳሚነቱን ይዘዋል። ባራክ ኦባማ የሚቀጥለውን ውድድር በአንደኛነት ካጠናቀቁ ድዋይት ኢሰንሆርን ይስተካከላሉ።

ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን ላይ ሳሉ የአንደኛነት ደረጃን ባለማግኘት ሁለተኛው ፕሬዘዳንት ናቸው።