የቴክኖሎጂ ተቋማት ግላዊ መረጃዎትን ያለአግባብ እንደሚጠቀሙበት ያውቃሉ?

ማርጋሬት ቬስታጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ማርጋሬት ቬስታጋር

ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋማት የተጠቃሚዎቻቸውን ግላዊ መረጃ ያለአግባብ እየተጠቀሙበት መሆኑ የቴክኖሎጂን በጎ ገጽታ እያጠለሸው እንዳለ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽነር ማርጋሬት ቬስታጋር ይገልጻሉ።

ሊገባደድ ጥቂት ቀናት የቀሩትን 2018 ወደ ኋላ መለስ ብለው ሲቃኙ፤ የቴክኖሎጂ ተቋማት የመረጃ አጠቃቀምን ይተቻሉ። እነዚህ ተቋማት የተጠቃሚዎችን መረጃ ያለአግባብ በመጠቀም የግለሰቦችን ነጻነት እየገፈፉ ነው።

ተቋማቱ አወንታዊ ሚና ሊኖራቸው ቢገባም፤ ሚናቸው ተሸርሽሮ የተጠቃሚዎችን መረጃን ያለ ፈቃድ በማግኘት ያለአግባብ ተጠቅመዋል።

ማርጋሬት ቬስታጋር "ለሰዎች ግላዊ መብት ዋጋ አልተሰጠም። መብታቸው እየተጣሰ ነው" ብለው አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

እንደ ማጣቀሻ በ2018 የተጠቃሚዎች መረጃ የተመዘበሩባቸው አጋጣሚዎችን እንመልከት።

የ2018 የቴክኖሎጂ ተቋሞች ቅሌቶች

  • ፌስቡክ የ87 ሚሊየን ተጠቃሚዎቹን መረጃ መጠበቅ ተስኖት መረጃው በካምብሪጅ አናሊቲካ ለፖለቲካዊ ፍጆታ በመዋሉ ይቅርታ ጠይቋል።
  • የትዊተር፣ የፌስቡክና የዩቲዩብ ተጠቃሚዎች መረጃ ሩስያ በምዕራቡ ዓለም ምርጫ ላይ ተጽእኖ እንድታሳድር ጥቅም ላይ ውሏል።
  • አንድሮይድን በሕገ ወጥ መንገድ በመጠቀም በጉግል የሚፈለጉ መረጃዎችን ለመቆጣጠር የአውሮፓ ኅብረት ለጉግል አምስት ቢሊዮን ዶላር ከፍሏል።

የእነዚህ ተቋማት ተግባር፤ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ቦታ እያሳጡ መጥተዋል።

የአውሮፓ ኅብረት የመረጃ ጥበቃ ሰነድ የሆነው 'ጄነራል ዳታ ፕሮቴክሽን'፤ የሰዎች ግላዊ ነጻነት እንዲጠበቅ እንዲሁም መረጃዎቻቸውም እንዳይጋለጡ የሚያስችል ማዕቀፍ አውጥቷል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሆኖም ማርጋሬት ቬስታጋር የበለጠ መሥራት እንደሚያሻ ይናገራሉ። ግለሰቦች በቴክኖሎጂያዊ መሳሪያዎች ከሚጭኗቸው፣ አስተያየት ከሚሰጡባቸው ወይም ከሚጋሯቸው ነገሮች መረጃ በመሰብሰብ እየተጠቀሙ የሚገኙ የቴክኖሎጂ ተቋማት አሰራራቸውን ግልጽ የሚያደርጉበት መንገድ መፈለግ ይኖርባቸዋል ይላሉ።

ስለ መረጃና መረጃን ለሌላ ወገን የማስተላለፍ ሂደት ግልጽ አሰራር ከሌለ፤ ጥቂት ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋማት የግለሰቦች መረጃ መቆጣጠራቸው አይቀርም።

ማርጋሬት ቬስታጋር፤ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ትልልቅ የቴክኖሎጂ ተቋማት መረጃ የሚያገኙበትን መንገድ መፈተሽ ጉልበታቸውን መገደብ ይችላል ሲሉ መፍትሄ ያስቀምጣሉ።