በዲሞክራቲክ ኮንጎ ተቃዋሚ ሰልፈኞች የኢቦላ ህክምና ማዕከልን አጠቁ

በከፊል የወደመው የኢቦላ ህክምና መስጫ ክሊኒክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እሁድ ዕለት የተረደገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በአንዳንድ ቦታዎች የሚካሄድበትን ጊዜ በመተላለፉ የተናደዱ ተቃዋሚ ሰልፈኞች የኢቦላ ህክምና የሚሰጥበትን ማዕከል አጠቁ።

በጥቃቱ የክሊኒኩ ድንኳኖች መቃጠላቸውን፣ ወንበሮችና ጠረጴዛዎች መዘረፋቸውን የሀገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ቃል አቀባይ የሆኑት ጄሲካ ኢኡንጋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በጥቃቱ ወቅት በክሊኒኩ ህክምና እየተከታተሉ ከነበሩ 21 ሰዎች መካከል 17ቱ መሻሻል እያሳዩ የነበሩና ተጨማሪ ምርመራ እየጠበቁ የነበሩ ናቸው።

ታካሚዎቹ ጥቃቱን በመሸሽ ያመለጡ ሲሆን፤ ሁኔታዎች ከተረጋጉ በኋላ ህክምናቸውን ለመከታተል መመለሳቸው ተነግሯል።

ጥቃቱ የደረሰው በሀገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል ምርጫው ከተላለፈባቸው ሶስት የሀገሪቱ ክፍሎች በአንዱ ነው። ስፍራው በኢቦላ ወረርሽን ክፉኛ ከተጎዱ የሀገሪቱ ክፍሎች መካከል አንዱ ነው።

የሀገሪቱ የምርጫ ቦርድ ለምርጫው መተላለፍ እንደ ምክንያት ያቀረበው በአካባቢዎቹ ያለውን የኢቦላ ወረርሽኝ ሲሆን፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግን መንግሥት ምርጫውን ሊያጭበረብር ነው ሲሉ ይከሳሉ።

ከፕሬዝዳንት ካፒላ ስልጣን የሚረከቡት ግለሰብ በሚቀጥለው ወር ቃለ መሀላ ይፈፅማሉ ተብሎ በሚጠበቅበት ሰዓት የሚሊየኖች ድምፅ ላይካተት ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።

ፕሬዝዳንት ካቢላ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ፤ በተወሰኑ ቦታዎች ለሌላ ጊዜ መተላለፉ ሕግን የተላለፈ አይደለም ሲሉ አስረድተዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP

"ምንም አትጨነቁ ሕጉ እንዲህ አይነት ጉዳዩችን በሚገባ እንዲያስተናግድ ተደርጎ የተቀመጠ ነው " ሲሉ ለሕዝባቸው መልዕክት አስተፈላልፈዋል።

ዲሞክራቲክ ኮንጎ በ1960 ከቤልጂየም ቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጣች ጀምሮ ነፃና ዲሞክራሲያዊ የሆነ የስልጣን ሽግግር አድርጋ አታውቅም።

ከ2001 ጀምሮ በስልጣን ላይ ያሉት ካቢላ በ2016 ከስልጣን መውረድ ነበረባቸው።

ነገር ግን የሚተካቸውን ሰው ለመምረጥ የሚካሄደው ምርጫ በአለመረጋጋት፣ መሰረተ ልማት ባለመሟላቱ እና አንዳንድ ስፍራዎች ለምርጫ ምቹ ባለመሆናቸው በተደጋጋሚ እየተላለፈ እስካሁን ድረስ ቆይቷል።

የተቃዋሚ መሪዎች ፕሬዝዳንት ካቢላ በዚህ ሰበብ አድርገው ስልጣን ላይ መቆየት አስበዋል ሲሉ ይከሳሉ። ፕሬዝዳንቱ ግን ይህንን ሀሳብ በማጣጣል ከተፎካካሪዎቹ መካከል የቀድሞ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር የነበሩትን ኢማኑዔል ራማዛኒ ሻዳሪን እንደሚደግፉ ገልፀዋል።

በዚህ መካከል የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአውሮጳ ህብረት አምባሳደር የሆኑትን ባርት ኦውቭሪ በ48 ሰዓታት ውስጥ ከሀገር ለቅቀው እንዲወጡ አዝዟል።

ለሳምንታት የኮንጎ ባለስልጣናት፣ የአውሮጳ ህብረት የሀገሪቱ ባለስልጣናት ላይ እንዲጣል ሲጠይቁ የነበረውን ማዕቀብ በሀገሪቱ ምርጫ ላይ እጅን ማስገባት ነው በማለት ሲከሱ ነበር።

በማዕቀቡ ከተጎዱት መካከል በ2017 በሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት ማዕቀብ ተጥሎባቸው የነበረውና አሁን ለፕሬዝዳንታነት እየተወዳደሩ ያሉት የቀድሞው የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር ናቸው።