ድምፅ ፈታዮቹ መረዋዎች

የመረዋ ኀብረ ዝማሬ ቡድን አባላት
የምስሉ መግለጫ,

የመረዋ ኀብረ ዝማሬ ቡድን አባላት

የኩኩ ሰብስቤ "ነገሩ እንዴት ነው" የሚለውን ሙዚቃ ሰምቶ ያጣጣመ አድናቂ፣ ዘፈኑ በአዲስ ጣዕም በኅብረ ዝማሬ ቡድን ቀርቦ ሰምቶታል። የግርማ በየነን "ፅጌረዳ" ያንጎራጎረ የሙዚቃ አፍቃሪ፣ በአዲስ ድምፃውያን ኅብረ ዝማሬ፣ በአዲስ ቅንብር ደግሞ አጣጥሞታል።

እነዚህን ነባር ሙዚቃዎች በአዲስ መልኩ ሠርቶ ለሙዚቃ አፍቃሪያን የሚያደርሰው ቡድን "መረዋ" ይሰኛል።

የመረዋ የኅብረ ዝማሬ ቡድን በጋራ መሥራት የጀመሩት 2005 ዓ. ም. መስከረም ላይ ነው። ያሰባሰባቸው ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ነው።

የ "መረዋ" ወጣቶች ጆሯቸውም ነፍሳቸውም ከለመዱት ውጪ፣ አዲስ ነገር የመሞከር ፍላጎት ወደ ሙዚቃ ስልቱ እንደገፋቸው ይናገራሉ።

ሁሉም የቡድኑ አባላት የሙዚቃ መሳሪያ መጫወት ብቻ ሳይሆን ያቀነቅናሉ። እያንዳንዱ የቡድኑ አባል ደግሞ የየራሱ ቀለም አለው።

የወንድ ወፍራም ድምፅ፣ የወንድ ቀጭን ድምፅ፣ የሴት ወፍራም ድምፅ፣ የሴት ቀጭን ድምፅ አንድ ላይ ተዋህዶ ለጆሮ ሲስማማ፣ የበለጠ መግለፅ የሚችለው ሲሰዘፍነው፣ በላቀ ሁኔታ የሚያሳምረው ሲያጅበው፣ ሁሉም ድምፀ መረዋ፣ ሁሉም የኅብሩ አንድ አካል ይሆናሉ።

አስራ አንድ እንደ አንድ፣ አንድ እንደ አስራ አንድ

11 አባላት ያሉት መረዋ ከተመሰረተ ጀምሮ የተለያዩ አባላት ተፈራርቀዋል። ስም ካላቸው እስከ አዳዲስ ሙዚቀኞች ድረስ መረዋን ተቀላቅለው ለቅቀዋል። አባላቱ ይህ የሆነው "ሙዚቃ የቡድን ሥራ በመሆኑ ነው" ይላሉ።

መረዋዎች እንደሚሉት ቡድኑ ውስጥ የተለያዩ ሰዎች መግባትና መውጣታቸው ሁለት ነገሮች ያሳያል።

"አንደኛውና ቀዳሚው፣ ሥራው ተደጋጋሚ ጥናት መጠየቁ ነው። መሰጠት፣ ቁርጠኝነት ስለሚፈልግ ነው።" ሲሉ ምክንያቱን ያስረዳሉ።

ሌላው ምክንያት ቡድኑ እንደሌሎች ባንዶች ክፍያ የሌለው መሆኑ ነው። በሳምንት የተወሰኑ ቀናት ሰርተው የሚያገኙት ቋሚ ገቢ የለም።

ስለዚህ ሙዚቀኞች ገንዘብ ወደሚያስገኙ ሥራዎች ፊታቸውን ያዞራሉ።

"የሥራ ስነ ምግባርም የሚጠቀስ ምክንያት ነው።" በማለት ያክላሉ። በዚህ ምክንያትም ከመረዋ ምስረታ ጀምሮ የተለያዩ አባላት ሲቀያየሩ ነው እዚህ የደረሱት።

ከቡድኑ ጋር የተለያዩ ሙዚቃዎች ያጠኑ ሰዎች ጣጥለው ሲሄዱ መጉዳቱ እንደማይቀር የሚናገሩት የቡድኑ አባላት፤ ዘወትር አዲስ ሰው በማምጣት ማስጠናት ፈታኝ ነው ይላሉ።

"በርግጥ አንድ ሰው ሙዚቃ አጥንቶ በትንንሽ ምክንያቶች ቡድኑን ጥሎ ሲወጣ ቡድኑ የሚያጣው ነገር ይኖራል። ማስጠናት ሥራ ይፈልጋል። ግን የማይቻል ሥራ አይደለም።"

የቡድኑ አባላት የተሰባሰቡት ከሙዚቃ ትምህርት ቤቶች መሆኑ ለድምፅ መረጣና ቅንጅቱ እንደረዳቸው ይመሰክራሉ።

"አንድ ትምህርት ቤት ስለተማርን አንድ ክበብ ውስጥ ነን" ድምፃዊ ማግኘት ለኛ ከባድ አይደለም"

የሙዚቃ መሳሪያ አልወጣም

መረዋዎች ድምፃቸው እየተስረቀረቀ ብቻ አይደለም ዜማ የሚያቀብሉን። የሙዚቃ መሳሪያዎችንም በድምፃቸው ይጫወታሉ።

ታዲያ የያሬድ ተማሪ ሆናችሁ፣ የሙዚቃ መሳሪያ አጥንታችሁ፣ ተክናችሁበት፣ ዲግሪ ከጨበጣችሁ በኋላ ምነው እርግፍ አድርጋችሁ ተዋችሁት? ስንል ጠየቅናቸው።

"በፍፁም ከሥራችን ውስጥ የሙዚቃ መሳሪያን ማስወገድ አልፈለግንም። እንደዛ የሚያስገድድም ትምህርት አልተማርንም፤ የለምም።" ያለ ቆምጨጭ ያለ መልስ አገኘን።

መረዋዎች፤ አዲስ ነገር ለመሞከር ስንል ነው ይህንን የጀመርነው ይላሉ።

ከኢትዮጵያ ውጪ የሚሰሩ መሰል ሙዚቃዎች ላይ ከሙዚቃ መሳሪያ በተለየ ድምፅ ላይ ብቻ አተኩረው መካናቸውን እንደ ማስረጃ ይጠቅሳሉ።

"ይህንንም በዩኒቨርስቲ ደረጃ ስልጠና መስጠት ጀምረዋል። የኛ ስርዓተ ትምህርት እዚህ ደረጃ ባይደርስም አሁን ከስር በሚመጡ ወጣቶች፣ ይህ ነገር ቢታይ፣ ቢሞከር፣ ክፋት የለውም። እኛም እሴት መጨመር ስለፈለግን ነው።"

ለሙዚቃ መሳሪያ መነሻው የሰው ልጅ ድምፅ ነው የሚሉት መረዋዎች፣ የሙዚቃ መሳሪያ ቀስ እያለ እግሩን እየሳበና እየዘመነ መጥቶ እንጂ የሰው ልጅ ድምፅ ብቻውን ውብ ተስረቅራቂ፣ ለጆሮ ጥዑም ነው ሲሉ ይከራከራሉ።

"የሙዚቃ መሳሪያዎች ስራ ላይ የዋሉት ድምፅን ወክለው ለመጫወት (ኢሚቴት) ለማድረግ ነው ተብለን ተምረናል። የሰው ልጅ በድምፅ ምንም አይነት ነገር ማድረግ ይችላል።" በማለት መሳሪያዎችን በድምፃቸው የተኩት ለዚህ እንደሆነ ያስረዳሉ።

ከዚህ በተጨማሪም ይላሉ አባላቱ፤ "በድምፅ ብቻ የሚጫወት የኅብረ ዝማሬ ቡድን አይደለንም።" በማለት በኅብረ ዝማሬ ቡድኑ ውስጥ በድምፅ ብቻ መጫወት አንዱ ዘርፍ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

በመሳሪያ ታጅቦ መጫወት ሌላው ዘርፍ በማለት "በሚቀጥሉት ሥራዎቻችን ላይ በማንኛውም ሰአት ከሙዚቃ መሳሪያ ጋር ልንጫወት እንችላለን"

ራሳቸውን ያለ ሙዚቃ መሳሪያ የሚጫወት የኅብረ ዝማሬ ቡድን ብቻ ብለው አይፈርጁም።

በአጋጣሚ በዩቲዩብ ላይ የተለቀቁት ሁለት ሥራዎቻቸው እንደዛ ቢሆኑም፤ መሳሪያ ተጠቅመውም ይጫወታሉ። ለምሳሌ በቅርቡ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ከሚያስተምረው ድራመር ተፈሪ ጋር በሠሩት ሙዚቃ ላይ በመሳሪያ ታጅበው እናያቸዋለን።

የቡድን አባላቱ ቁጥር መብዛት ዕድል ወይስ ተግዳሮት

መረዋ የኅብረ ዝማሬ ቡድን ያለ ሙዚቃ መሳሪያ ሙዚቃ በመጫወት እየታወቁ መጥተዋል። መነሻ የሆኗቸው የደቡብ አፍሪካ ''Black Mambazo'' ናቸው።

ከደቡብ አፍሪካ ውጪ በማዳጋስካርና የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ባህል ውስጥ ኅብረ ዝማሬ በርከት ባሉ ሰዎች ሲቀነቀን ማስተዋላቸውን ይጠቅሳሉ።

"መብዛታችን የኅብረ ዝማሬውን ውበት ለመጨመር ትልቅ አስተዋፅኦ አለው። የኅብረ ዝማሬ ቡድንም አወቃቀርም እንደዛ ነው"

ምዕራባውያን በአነስተኛ ሰው ስብስብ በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ተደግፈው ቡድን ያዋቅራሉ የሚሉት መረዋዎች፤ ይህ ግን በአፍሪካ ባህላዊ የህብረ ዝማሬ ሙዚቃ ላይ እንደማይታይ ያስረዳሉ።

ምንም አይነት መሳሪያ ድምፃቸውንና ቅኝታቸውን ለማረቅ አይጠቀሙም። "ቡድኑ ተፈጥሮን ተጠቅሞ፣ ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ ነው የሚሰራው" የሚሉት መረዋዎች፤ በሙዚቃ ስቱዲዮ ውስጥም ሆነ መድረክ ላይም ሢሰሩ አንድ አይነት መሆኑን ይናገራሉ።

መረዋዎች በጣሊያን ባህል ማዕከል ትልቅ ኮንሰርት አዘጋጅተው ነበር። በዚያ ኮንሰርት ከ20 በላይ ሙዚቃዎች ተጫውተዋል። በሙዚቃ መሳሪያም ታጅበውም የምርምር (ኤክስፐርመንታል) ሙዚቃ ሠርተዋል።

ያኔ ያውቋቸው የነበሩት በሙዚቃ ህይወት ውስጥ ያሉ ሰዎች ብቻ እንደነበሩ ያስታውሳሉ። ሙዚቃ ሲያቀርቡ ይታደሙ የነበሩትም ሙዚቀኞች እና በዙሪያቸው ያሉ ሰዎች ነበሩ።

ሆኖም የመጀመሪያ ሥራቸው በዩቲዩብ ላይ ከወተለቀቀ በኋላ ግን የአድናቂዎቻቸውና የተከታዮቻቸው ብዛት እንደጨመረ ይገልጻሉ።

የሙዚቃ ቡድኑ 11 አባላት መንገድ ላይ ሲሄዱ እስከመለየት ያደረሳቸውን እውቅና ያገኙት የ"ነገሩ እንዴት ነው" የሙዚቃ ቪዲዮ ከወጣ በኋላ ነው። በቡድን ሲንቀሳቀሱም አድናቂዎች በቀላሉ ይለይዋቸዋል።

"ያንን ኮንሰርት ዛሬ ብንሠራው የሚገኘው ሰው ቁጥር ከፍተኛ ይሆን ነበር" ይላሉ መለስ ብለው ጊዜውን በማስታወስ።

በተለያየ ጊዜ የተለያዩ መሪ ድምጻውያን እንደሚጠቀሙ የሚናገሩት የመረዋ ቡድን አባላት ምክንያቱን እንዲህ ያብራሩታል።

"መጀመሪያ የምንሠራቸውን ሙዚቃዎች እንለያለን። የምንሠራው ቅኝት ላይ ከሆነ ቅኝቱን በሚገባ ተረድቶ የሚዘፍን ብቃት ያለው ሰው ያስፈልገናል። ዳያቶኒክ ሙዚቃዎች የምንሠራ ከሆነ እዛ ውስጥ ያሉትን ቴክኒኮች የበለጠ የሚገልፅ ሰው ያስፈልጋል። ሰው ለመምረጥ የምንሰራው ሙዚቃ ወሳኝነት አለው"

ስለዚህም ዛሬ ከፊት ሆነው ሲያቀነቅኑ ያየናቸውን ሙዚቀኞች ከኋላ፣ ከጀርባ ሆነው ሲያጅቡ የነበሩ ደግሞ ከፊት ሆነው ሲያዜሙ እናያለን።

የተለመደውን ባልተለመደው መንገድ

ሙዚቃ ስናደምጥ ጆሯችን የሰለጠነበት መንገድ አንድ አይነት ማለትም ድምጽ በሙዚቃ ታጅቦ መስማት ነው።

የከበሮ ድምፅ ከጊታር ተዋህዶ፣ ኪቦርድ ከሳክስፎን አብሮና ውበት ፈጥሮ መስማት የለመድነው ነው።

ይህንን የተለመደ የጥበብ ስራ ወስዶ በአዲስ መልክ መስራት ለመረዋዎች ቀላል እንደነበር ትምህርታቸውን በመጥቀስ ያስረዳሉ።

". . . ቅንብር የሙዚቃ ትምህርት አንድ አካል ነው። ያሬድ እንደ አንድ ትምህርት ይሰጣል። የቡድኑ አባላት የተለያዩ ቅንብሮችን ይሠራሉ። ምዕራፍ ተክሌ ያቀናበራቸውን ሙዚቃዎችም በተለያዩ መድረኮች ላይ ተጫውተናል። የ"ፅጌረዳ"ን ቅንብር የሰራው ደግሞ እስራኤል ጥላሁን ነው"

በአንድ ወቅት የሚሠውራን ቅንብር በሌላ ወቅት ሌላ ሰው መልሶ ሊሠራ እንደሚችል፤ ካልሆነም መነሻ ሀሳቡን አንድ ሰው ከሠራ በኋላ የቡድኑ አባላት ቅንብሩን ሊያዳብሩት እንደሚችሉ ይናገራሉ።

በ"አካፔላ" የኅብረ ዝማሬ ቡድን ውስጥ የተለመደው የድምጻውያንን ሥራ ድጋሚ ማቀናበር መሆኑን የሚናገሩት መረዋዎች፤ መጀመሪያ ላይ ድምፃዊያኑ ከሌሎች አካላት ፈቃድ ማግኘት ይቸገሩ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ለዘርፉ አዲስ ሆኖ ድምፃዊ፣ ገጣሚ፣ ዜማ ደራሲ ለየብቻ ማናገር ፈታኝ ነበር የሚሉት መረዋዎች፤ ቀጣዩ ሥራዎቻቸው የመጀመሪያውን ያህል እንዳልከበደባቸው ይናገራሉ።

ዛሬ ዛሬ ሥራቸውን ያዩ ባለሙያዎች "የኔንም ሙዚቃ ብትሠሩ" ብለው እንደሚጠይቋቸው ይገልፃሉ።

ለወደፊት የራሳቸውን አልበሞች አሳትመው በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ትልልቅ የሙዚቃ ትርዒቶች መሥራት እንዲሁም፤ በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች መጫወትም ይፈልጋሉ።

በ"አካፔላ" ዘርፍ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ የራሳቸውን አስተዋፅኦ ማበርከት ይሻሉ። በተለያዩ ክልሎች በመዘዋወር የየአካባቢውን ሙዚቃ በማጥናት በኅብረ ዝማሬ መግፋትም ይፈልጋሉ።

የወደፊት እቅዳቸው ላይ በደማቅ ቀለም ከተፃፉት መካከል በዓለም አቀፍ ፌስትቫሎችና ውድድሮች ላይ መሳተፍም ይገኝበታል።