ጣና ሀይቅ ላይ ጀልባ ተገልብጦ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት አለፈ የሚሉና ሌሎችም አጫጭር ዜናዎች

Image copyright DEA / A. TESSORE

ኢትዮጵያ

• ዛሬ ጣና ሀይቅ ላይ አንድ ጀልባ ተገልብጦ የዘጠኝ ሰዎች ሕይወት አለፈ። ከጣና ሀይቅ ትራንስፖርት ድርጅት በተገኘው መረጃ መሰረት የአደጋው መንስኤ እስካሁን አልታወቀም።

• በአራቱ የወለጋ ዞኖችና በምዕራብ ጉጂ ዞን በተከሰተ የጸጥታ ችግር ሳቢያ ኅብረተሰቡ የጤና አገልግሎት ማግኘት አለመቻሉን የኦሮሚያ የጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ደረጄ ዱጉማ ገለጹ። በአካባቢዎቹ በርካታ የጤና ተቋሞች ተዘግተዋል።

• በቡሌ ሆራ ዩኒቨርስቲ ተቋርጦ የነበረው ትምህርት ጥር አንድ እንደሚጀመር የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር መግለጹን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን ዘገቡ። ትምህርት የተቋረጠው በተማሪዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ምክንያት መሆኑ ይታወሳል።

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ

• የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምርጫን ተከትሎ የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል። የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር መንግሥት የምርጫውን ውጤት ለመሸፋፈን እየሞከረ ነው ብለዋል።

ግብጽ

• አማል ፋቲ የተባለች ግብጻዊት የሴቶች መብት ተሟጋች የግብጽ መንግሥት ወሲባዊ ጥቃትን ለመግታት ጥረት አለማድረጉን ከተቸች በኋላ የሁለት ዓመት እስር ተፈርዶባታል። አምንስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ የመብት ተቆርቋሪዎች ፍርዱን ተቃውመዋል።

• የግብጽ ፖሊስ ባለፈው አርብ ከደረሰው የቦምብ ጥቃት ጋር በተያያዘ 40 ታጣቂዎችን እንደገለ ገለጸ። ታጣቂዎቹ የተገደሉት በአብያተ ክርስቲያናትና በጎብኚዎች ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲዘጋጁ ነበር ተብሏል።

እንግሊዝ

ስደተኞች አነስተኛ ጀልባ በመጠቀም ወደ እንግሊዝ ለመግባት የሚያደርጉትን ጥረት ለመቆጣጠር እንግሊዝና ፈረንሳይ የጋራ ቡድን ለማቋቋም ተስማሙ። ወደ እንግሊዝ ለመግባት ከሚሞክሩት አብዛኞቹ ኢራናውያን እና ሶሪያዊያን ናቸው።

ፊሊፒንስ

የፊሊፒንስ ፕሬዘዳንት ታዳጊ ሳሉ የቤት ሠራተኛቸው ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ማድረሳቸውን መናገራቸውን ተከትሎ እየተወገዙ ነው። ፕሬዘዳንቱ ሥልጣን አይገባቸውም ተብለዋል። ከዚህ ቀደም አንዲት ሴትን መድረክ ላይ አስገድደው መሳማቸው ቁጣ መቀስቀሱ ይታወሳል።

ኢራን

የኢራን ቴሌቭዥን ጣቢያ ሀላፊ፤ ጄኪ ቻን የሚተውንበት ፊልም ላይ የሚታይ ወሲባዊ ትዕይንት ሳይቆርጥ በማስተላፉ ተባሯል። ኢራን ውስጥ መሰል ፊልሞች በቴሌቭዥን ማሰራጨት አይፈቀድም።

አሜሪካ

ነገ የሚከበረውን የፈረንጆች አዲስ ዓመት አከባበር ለመቆጣጠር ድሮን እንደሚጠቀም የኒዮርክ ፖሊስ አስታወቀ። በድሮን የሚጠበቀው ከአንድ ሚሊየን በላይ ሰዎች በአሉን የሚታደሙበት ታይምስ አደባባይ ይሆናል።

ሩስያ

ሩስያ ሲሰልል እጅ ከፍንጅ ይዤዋለሁ ያለችውን አሜሪካዊ በቁጥጥር ስር አውላለች። ግለሰቡ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኝ እስከ 20 ዓመት ሊታሰር ይችላል። አሜሪካ ስለጉዳይ እስካሁን ያለችው ነገር የለም።