በ2019 በጣም ተፈላጊ የሆኑ የዲጂታል ዘርፍ ሥራዎች የትኞቹ ናቸው?

ላፕቶፕ Image copyright Getty Images

የዲጂታል ሥራዎችና መሰል ተግባራት ከሌላ ጊዜ በተለየ መልኩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታዋቂ እየሆኑ መጥተዋል።

ባደጉት ሃገራት ላፕቶፖቻቸውን በጀርባቸው ተሸክመው ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱና ጥሩ የኢንተርኔት አገልግሎት አለበት በተባለ ቦታ ሁሉ የሚገኙ ወጣቶች በርክተዋል።

ሃሳባቸው ደግሞ የግድ ቢሮ ውስጥ ገብተን ሥራ መስራት የለብንም፤ ካለንበት ቦታ ሆነን ለምን ትርፋማ ሥራዎች መስራት አንችልም? ነው።

ስልክዎ እንደተጠለፈ የሚያሳዩ ሰባት ምልክቶች

ሁሉንም የሚያመሳስላቸው ደግሞ በይነ መረብን በአግባቡ ማወቃቸውና የዲጂታል ኢኮኖሚ ጥቅም የገባቸው መሆኑ ነው።

በዲጂታል የሥራ ብቃት ላይ ትኩረት ያደረጉ ብዙ ትልልቅ ድርጅቶችም ፊታቸውን ወደ እነዚህ ወጣቶች እያዞሩ ያመስላል።

በያዝነው የፈረንጆች አዲስ ዓመት የትኞቹ የዲጂታል ሥራ ዘርፎች የበለጠ ውጤታማ ሆነው በብዙዎች ዘንድ ተፈላጊ ይሆናሉ? ባለሙያዎችን አናግረን አምስት የሥራ አይነቶችን ለይተናል።

1. ሳይበርሰኪዩሪቲ ስፔሻሊስት (የመረጃ መረብ ባለሙያ)

በታህሳስ ወር ይፋ በተደረገ አዲስ ጥናት መሰረት በ2019 እጅግ በጣም ብዙ ሰራተኞች የሚፈለጉበትና ትርፋማ ሊሆን የሚችለው የዲጂታል የሥራ ዘርፍ የሳይበርሰኪዩሪቲ ስፔሻሊስትነት ነው።

የመረጃ ደህንነት እንዲሁም ኔትወርኪነግ ደህንነት በብዙ ድርጀቶች አሳሳቢ ነገሮች እየሆኑ መምጣታቸውን ተከትሎ ይህ የሥራ ዘርፍ ተፈላጊ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በሞባይልዎ የኢንተርኔት ወጪ ተማረዋል?

የሳይበርሰኪዩሪቲ ስፔሻሊስቶች ዋነኛ ሥራ የድርጅቶች መረጃና አዳዲስ ፈጠራዎች ከውጪና ከውስጥ ከሚሰነዘሩ የበይነ መረብ ጥቃቶች መከላከል ነው።

አሁን ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉ የፈጠራ ውጤቶችን ቶሎ ቶሎ መከታተልና ወደፊት ሊመጡ የሚችሉ ስጋቶችን ቀድሞ ማወቅ ደግሞ ግዴታቸው ነው።

2. ብሎክቼይን ቨሎፐር (በበይነ መረብ ውስጥ ዋጋ ያላቸውን መገበያያዎች የሚፈጥሩ)

በጥናቱ መሰረት ይህ የሥራ ዘርፍ በአዲሱ ዓመት በዲጂታሉ ዓለም በሁለተኝነት ተፈላጊ ሊሆን ይችላል።

'ሊንክድኢን' የተሰኘው ሥራ አፈላላጊ ተቋም እንዳስታወቀው በቀጣሪዎችም ሆነ በሥራ ፈላጊዎች ዘንድ ይህ ዘርፍ በጥብቅ ይፈለጋል።

የብሎክቼይን ዴቨሎፐሮች ፍላጎት በአሜሪካ ብቻ በአስገራሚ ሁኔታ በ33 እጥፍ እንደጨመረ ተቋሙ ገልጿል።

የስልክዎን ባትሪን ለረዥም ጊዜ ለመጠቀም

የባለሙያዎቹ ዋነኛ ተግባር ደግሞ 'ክሪፕቶከረንሲ' ማርቀቅ ነው። ለዚህ ደግሞ በቀዳሚነት የሚቀመጠው 'ቢትኮይን' የተሰኘው 'ክሪፕቶከረንሲ' ነው።

ባሳለፍነው ዓመትም 'ቢትኮይን' ምንድነው ብለው ጉግል ላይ መረጃ የጠየቁ ሰዎች ቁጥርም ከፍተኛ ነበር ተብሏል።

Image copyright Getty Images

3. አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ

'አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ' ገና ጅምሩ ላይ ያለ የሥራ ዘርፍ ይመስላል። ስለ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሲወራ፤ ሮቦቶች አልያም ሌላ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ሥራችንን ሊወስዱብን ነው ብለው የሚሰጉ ብዙ ሰዎች አሉ።

ይህ የሥራ ዘርፍ ግን ብዙ ባለሙያዎችን ለመቅጠር ትልቅ ዕድል ያለውና ጀማሪ በሚባል ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው።

በቅርቡ የተሰራው ጥናት እንደሚያመለክተው ከእያንዳንዱ 15 ተስፈኛ የሥራ እድሎች መካከል ስድስቱ ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር የተያያዙ ናቸው።

ከ2015 እስከ 2017 ባሉት ዓመታት ብቻ ከአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ጋር የተያያዙ እውቀቶችና ሥራ ልምዶች 190 በመቶ አድገዋል።

ራስዎን ካላስፈላጊ የስልክ ጥሪ እንዴት ይታደጋሉ?

እንደ አፕልና ኢንቴል ያሉ በአሜሪካ የሚገኙ የአዳዲስ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ባለሙያዎችን ዋነኛ ፈላጊ እንደሆኑ 'ሊንክድኢን' የተሰኘው ድርጅት ጠቁሟል።

4. ክላውድ ኮምፒዩቲንግ (የበይነ መረብ የመረጃ ቋት)

የተለያዩና ብዙ ቦታዎችን የሚይዙ መረጃዎችን በበይነ መረብ የመረጃ ቋት (ክላውድ ኮምፒዩቲንግ) ማስቀመጥ ተመራጭ ተግባር እየሆነ መጥቷል።

ለዚህም ነው የክላውድ ኮምፒዩቲንግ ባለሙያዎች በዲጂታሉ ዓለም በጣም ተፈላጊ እየሆኑ የመጡት።

የትልልቅ ድርጅቶችን መረጃዎች በቋቶቹ ውስጥ ማንም ሰው ሊያገኘው በማይችለው መልኩ ማስቀመጥና ማጠራቀም ደግሞ የእነዚህ ባለሙያዎች ዋነኛ ተግባር ነው።

በቴክኖሎጂ ኢ-ፍትሐዊነትን የምትታገለው ኢትዮጵያዊት

በዚህ የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ግለሰቦች ብዙ ጊዜ ጠቀም ያለ ደሞዝ የሚከፈላቸው ሲሆን፤ በዓመት እስከ 125 ሺህ ዶላር ያገኛሉ ተብሎ ይገመታል።

እስካሁን የጠቀስናቸው የዲጂታል ዓለም የሥራ ዘርፎች በሙሉ ክላውድ ኮምፒዩቲንግ መጠቀም ግድ ይላቸዋል።

5. የንግድ መረጃ ተንታኝ

አምስተኛውና በጣም ተፈላጊ የሆነው የዲጂታል ሥራ ዘርፍ ደግሞ የንግድ መረጃ ተንታኝነት ነው። ነገር ግን ምንድነው የሚሰሩት? ልትሉ ትችላላችሁ።

ዋነኛው ሥራቸው ብዙ ሰዎች በቀላሉ ማከናወን የማይችሉትን የብዙ ዓመታት መረጃዎች ማሰባሰብና ለውሳኔ እንዲያግዙ አድርጎ ማዘጋጀት ነው።

ማንኛውም አይነት መረጃ ጠቃሚ ነው ብለው ያምናሉ እነዚህ ሰዎች።

የኮምፒዩተር ሳይንስ እውቀታቸው ከፍ ያለ ሲሆን፤ ከንግድ ተጋር የተያያዙ ማኛውንም አይነት መረጃዎች አያመልጧቸውም። አንድ ንግድ ትርፋማ ይሆናል ወይስ አይሆንም የሚለውን ጥያቄ በቀላሉ መመለስ ይችላሉ።

ትርፋማ መሆን ያልቻለ የንግድ ዘርፍንም ማነቃቃትና ትርፋማ እንዲሆን ለማድረግ እነዚህ ባለሙያዎች እጅግ ወሳኝ ናቸው።