በሱዳን የኦማር አል-በሽር ተቃዋሚዎች አደባባይ ወጥተዋል የሚሉና ሌሎችም አጫጭር ዜናዎች

Image copyright MOHAMED N ELMAHDI
አጭር የምስል መግለጫ በሱዳን የኦማር አል-በሽር ተቃዋሚዎች አደባባይ ወጥተዋል

ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ውጤት እንዲከበር አሳስቧል። በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባወጣው መረጃ መሰረት ባለፈው ወር ብቻ ወደ 16ሺህ ሰዎች ግጭት ሸሽተው ከሀገሪቱ ወደ ብራዛቪል ተሰደዋል።

ሱዳን

ሱዳን ውስጥ የኦማር አል-በሽር አስተዳደርን የሚቃወሙ ሰልፈኞች አሁንም ወደ አደባባይ መውጣታቸውን ቀጥለዋል። ባለፈው ወር አጋማሽ ላይ መንግሥት የነዳጅና ዳቦ ዋጋ ጭማሪን ይፋ ካደረገ በኋላ ሕዝቡ ተቃውሞውን እያስተጋባ ነው።

ኮንጎ በታሪኳ አስከፊ በሆነው የኢቦላ ወረርሽኝ እየተናጠች ነው

የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች የሰላም ስምምነት ተፈራረሙ

ዚምባብዌ

የዚምባብዌ መንግሥት የሥራ ማቆም አድማ ያደረጉ ሀኪሞችን ለመተካት 200 ክፍት የሥራ ቦታ ማስታወቂያ አውጥቷል። ሀኪሞቹ የመድሀኒት እጥረት እንዲሁም የሥራ ሁኔታ አለመመቻቸትን ምክንያት በማድረግ የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸው ይታወሳል።

ዛምቢያ

አንዲት የ16 ዓመት ዛምቢያዊት አጭር ቀሚስ ለብሳ በፖሊስ ጣቢያ በኩል በማለፏ ከታሰረች ሁለት ሳምንት ሆኗታል። ከታዳጊዋ ጋር አብራ የነበረችው አክስቷ ፖሊስ በሴቶች ቀሚስ ቁመት ምን ጥልቅ አደረገው? ብላ የእስሩን ኢ-ፍትሀዊነት በፍርድ ቤት ብትሟገትም ሰሚ አላገኘችም።

ዚምባብዌ የነዳጅ ቁፋሮ ልትጀምር ነው

የዚምባብዌ ፖለቲከኛው የጥገኝነት ጥያቄ ውድቅ ተደረገ

ጋና

ጋና፣ አክራ ውስጥ የሚገኙ ፓስተር የሃገሪቱ ዋና ኢማም በ2019 ይሞታሉ ብለው በመተንበያቸው የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ጥቃት አድርሰውባቸዋል። ዋና ኢማሙ ኑሁ ሻራቡቱ ግን ጥቃት አድራሾቹን ተቃውመዋል።

ኬንያ

የኬንያ ሴቶች ከትምህርት እረፍት አድርገው ወደ ትምህርት ቤት ሲመለሱ ተገርዘው እንደሆነ መፈተሽ መጀመሩ እያነጋገረ ነው። ግርዛት አሁንም እልባት ያልተገኘለት ችግር ቢሆንም ተማሪዎችን መፈተሽ ምን ያህል መፍትሄ ይሆናል ብለው የጠየቁ መምህራንም አሉ።

ቡርኪናፋሶ

በቡርኪናፋሶ የተነሳውን የጎሳ ግጭት ተከትሎ ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች 46 መድረሳቸውን መንግሥት አሳውቋል። በሞሲና ፉላኒ ጎሳዎች መካከል ግጭት የተቀሰቀሰው ሰኞ እለት ነበር።

ጀርመን

የጀርመኗ መራሄተ መንግሥት አንግላ መርኬልን ጨምሮ የጀርመን ፖለቲከኞች መረጃ ተመዝብሮ በድረ ገጽ ተለቋል። የፖለቲከኞቹ የግል የስልክ መልዕክት ልውውጦችና ሌሎችም መረጃዎች በትዊተር ላይ ይፋ ተደርገዋል። መረጃዎቹ በማን እንደተመዘበሩ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

ሁዋዌ

ሁለት የሁዋዊ ሠራተኞች አይፎን ተጠቅመው ትዊት በማድረጋቸው መቀጣታቸው ተሰምቷል። ሠራተኞቹ በሁዋዊ የትዊተር ገጽ ላይ መልካም አዲስ ዓመት ብለው ትዊት ያደረጉት አይፎን ተጠቅመው መሆኑ የተቋሙ መርህ ይጻረራል ተብሏል።