"የመከላከያ ሰራዊትን እንቅስቃሴ የሚያግድ ስራ አንቀበልም" ዶ/ር ደብረፅዮን

ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል

በትናንትናው ዕለት በሽረ እንዳስላሴ በኩል ሲያልፉ የነበሩ የመከላከያ ኃይል መኪናዎች ከእነ አሽከርካሪዎቻቸው በከተማዋ ነዋሪዎች መታገታቸው በተለያዩ ሚዲያዎች ተዘግቧል።

25 የሰራዊቱና አምስት የአመራሮች መኪናዎች ወደ አዋሳ እያመሩ በነበረበት ወቅት የአካባቢው ነዋሪዎቹ መስመሩን እንደዘጉ በቦታው ላይ የነበረ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ታዝቧል። የሰራዊቱን መሄድ በመቃወም መኪኖቹ ላይ የወጡ፤ መንገድ ላይ የተኙ እንዳልታጡና በመጨረሻም ወደ ስታዲየም እንዲገቡ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር።

የህግ የበላይነት ሳይሸራረፍ እንዲተገበር የሚጠይቀው የትግራይ ክልል መግለጫ

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለፁት "ሰራዊቱ ህዝቡን ለማን ትቶ ነው መሳሪያውን ይዞ የሚወጣው" የሚሉና እንዲሁም በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው የሰላም ግንኙነት "መንግሥት እንደሚለው አስተማማኝ ሳይሆን ስጋት አለን" የሚሉ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ተቀያሪ ሰራዊት የሚመጣም ከሆነ ያኛው ሰራዊት ሳይመጣ ለምን እነዚህ ይወጣሉ የሚሉ ነበሩ።

በትግራይ ልዩ ኃይል እንዲጠበቁና ህዝቡ ወደ ቤቱ እንዲሄድ ስምምነት ላይ የተደረሰ ቢሆንም የአካባቢው ህዝብ የከተማው ሚሊሻ አባላት እንዲጠብቋቸው እንፈልጋለን በማለታቸው ወደ አስራ አምስት የሚሆኑ የከተማው ሚሊሻ አባላት እንዲጠብቁ ተደርጓል።

ተጠርጣሪዎችን የመያዝ ዘመቻው ብሔር ላይ ያነጣጠረ ነው?

ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የሰራዊቱ አባልም ለቢቢሲ እንደገለፀው ሰራዊቱ መንግሥት በወሰነው መሰረት ወደ ሃዋሳ እንዲንቀሳቀስ ሌላ ተቀያሪ ሰራዊትም እንደሚመጣ ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው ነው።

ይህንና ሌሎች ተጓዳኝ ጉዳዮችን በሚመለከት የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በትናንትናው ዕለት መግለጫ የሰጡ ሲሆን የሰራዊቱን እንቅስቃሴ የሚያግድ ስራ ተቀባይነት እንደሌለው አስረድተዋል።

"በማንኛውም መልኩ ግጭትና ጦርነት የሚቀሰቅስ ስራ አንቀበልም" ሲሉ ገልፀዋል።

የመከላከያ ሰራዊት መሳሪያንና እንቅስቃሴን ማገድ ተገቢ እንዳልሆነ የተናገሩ ሲሆን ስለ ሰራዊቱ እንቅስቃሴ መነጋገር ያለበት አካል የክልሉ መንግሥት ከፌደራል መንግሥት ጋር ነው ብለዋል።

ምንም እንኳን የህዝቡን ስጋት እንደተረዱት ዶ/ር ደብረፅዮን ቢያስረዱም መፍትሄው ግን በስርአትና በውይይት ሊሆን እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

" ህዝቡ ውስጥ ያለው ጥርጣሬና ስጋት ይገባናል። ቢሆንም ግን የጦር መሳርያው የፌደራል መንግስት ንብረት ስለሆነ የጦር መሳሪያ አቀማመጡ ሰራዊቱን እንጂ እኛን አይመለከተንም።" ያሉት ዶከተር ደብረፅዮን " በጦር መሳርያ አንተማመንም ከዚህም በላይ የጦር መሳርያ ማምጣት ካስፈለገን ማምጣት እንችላለን፤ ነገር ግን የጦር መሳርያ ፋብሪካ ሳይሆን ፣ ሰላምና ልማት ነው የምንፈልገው።" ብለዋል

የጦር ሃይሎች ምክትል ጠቅላይ ምክትል ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ በትናንትናው ዕለት ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት መግለጫ ከሰሜን በኩል የሚመጣ ምንም ስጋት ባለመኖሩ ሰራዊቱ ወደ ሌላ አካባቢ እንዲዛወር ስምምነት ላይ መደረሱንና ከትግራይ ክልልም ጋር ውይይት መደረጉን ገልፀዋል።

"ሰራዊቱ የኢትዮጵያም ነው የትግራይም ነው። የፌደራል መንግሥት ስጋት ባይኖርበት የትግራይ ህዝብ ስጋት አለው፤ ቢሆንም የትግራይ ህዝብ ሰራዊቱን አያግትም፤ ነገር ግን ስጋት እየፈጠረ መኖር የለመደና ህዝቡን ሽፋን አድርጎ ትርምስ ለመፍጠር የሚሞክር ሃይል አለ። ጥቂቶች ናቸው እርግጠኛ ነኝ ይጋለጣሉ። የትግራይ ህዝብም ቢዘገይም ይገባዋል።"ብለዋል

ከዚህም በተጨማሪ ከሰሞኑ የሑመራ ኦምሐጀር ድንበር መከፈት ጋር ተያይዞ ለሚነሱ ጥያቄዎችም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ምላሽ ሰጥተዋል።

በዚህ ሳምንት የሑመራ-ኦምሓጀር ድንበር ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድና በኩል የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልና የአማራ ክልል መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በተገኙበት መከፈቱ የሚታወስ ነው።

ከድንበሩ መከፈት ጋር ተያይዞ ለሶስት ወራት ተከፍቶ የነበረው የዛላምበሳና የራማ ድንበሮች መዘጋታቸው በአካባቢው ህዝብ ዘንድ ጥርጣሬንና ጭንቀትን መፍጠሩን አስመልክቶ ዶ/ር ደብረፅዮን ግንኙነቱን ፈር ለማስያዝ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዚህ ሳምንት በይፋ የተከፈተው ሑመራ- ኦምሐጀር ድንበር መከፈት በሁለቱ ኃገራት መካከል የተደረገው ስምምነት አንዱ አካል ሲሆን ሁሉም ድንበሮች ክፍት እንዲደረጉ ስምምነት ላይ መደረሱን ዶ/ር ደብረፅዮን ተናግረዋል።

ብዙዎች የዛላምበሳ ድንበር መዘጋቱንና የይለፍ ወረቀት መጠየቁ ጋር ተያይዞ የዚህ ድንበር መከፈት የዛላምበሳው ማካካሻ ተደርጎ መታየቱ ትክክል እንዳልሆነም አስረድተዋል።

የዛላምበሳው መስመር ድንገት መዘጋቱንና የተዘጋውም ከኤርትራ በኩል እንደሆነ ገልፀው በወቅቱም ለፌደራል መንግሥት መጠየቃቸውን እንዲሁም የሑመራ-ኦምሓጀር ድንበር ሲከፈትም ከፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ጋር መወያየታቸውን ገልፀዋል።

መስመሩ የተዘጋው ግንኙነቱን ህግና ስርዓት ለማስያዝና በፌደራል ደረጃ ይህንን ጉዳይ የሚከታተል ኮሚቴም የተቋቋመ ሲሆን ስራዎቹም እየተጠናቀቁ እንደሆነ ተናግረው የሑመራ-ኦምሓጀር ድንበር ስርዓት እስኪይዝ ለህዝብ ክፍት እንደሚሆንም ጨምረው አክለዋል።

በወቅቱም ከፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው ሲነጋገሩ በመታየታቸው ድርጊቱ የዕርቅና የሰላም ምልክት ሊሆን ይችላል ወይ ተብለው የተጠየቁት ዶ/ር ደብረጽዮን "አዎ ከአሁን በኋላ ተመልሰን ወደ ጦርነትና ግጭት የምንገባበት ምክንያት አይኖርም" ብለዋል።

ድንበሩ ሲከፈት በነበረው ዝግጅት የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ሑመራ ከተማ መግባት የለባቸውም የሚሉ የተቃውሞ ሰልፎች መነሳታቸውን አስመልክቶ ዶ/ር ደብረፅዮን ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን ችግሮች ቢኖሩም በውይይት መፈታት እንዳለባቸው አስረድተዋል።

መከላከያ በዛላምበሳ ድንበር እንዲቆይ ስምምነት ተደረሰ

" የሐሳብ ልዩነት ቢኖርንም ልዩነታችን በውይይት ለመፍታት መስራት አለብን እንጂ ዓይኑን ማየት የለብኝም የሚል አካሄድ የፖለቲካ ትግልን አያሳይም። እኛ አይደለም አብረውን እየታገሉ ከመጡ ሰዎች ይቅርና ከሰይጣን ጋርም ቁጭ ብለን ለመነጋገር ችግር የለብንም።" ያሉ ሲሆን ከአማራ ክልል አመራር ጋር እንደማይነጋገሩ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት ገልፀው " አንድ አገር ውስጥ ነው ያለነው ተደጋግፈን ማደግ አለብን ነው እያልን ነው ያለነው።" ብለዋል።

ከዚህ በፊት በውይይት የተፈቱ ጉዳዮች እንዳሉ የተናገሩት ዶ/ር ደብረፅዮን ለዚህም እንደምሳሌነት ያነሱት ያለ ክልሉ እውቅና በመቐለ የአሉላ አባነጋ አየር ማረፍያ የተያዙት ታጣቂዎችን ጉዳይ ነው።

"ባንታገስ ኖሮ ከፌደራል መንግስት ሳናውቅ ድንገት መጥተው የመሸጉት ታጣቂዎች የመጡ ዕለት ጦርነት መጀመር ነበረበት። ይዘን ማሰር እንችል ነበር ግን መጨረሻው የት ይሆን ነበር? መታገስን መርጠናል። ተገደን ካልሆነ በስተቀር ጦርነት ውስጥ አንገባም።" ያሉት ዶ/ር ደብረፅዮን ከፌደራል መንግሥት ጋር እንደማይፈልጓቸው ተነጋግረው ታጣቂዎቹን እንደመለሷቸው ገልፀዋል።

በጉዳዩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ተጠይቀው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የፌደራል ፖሊስ አባላት ለሌላ ጉዳይ እንደሄዱና ጉዳያቸውንም አከናውነው እንደተመለሱ ጠቅሰው ከክልሉም ጋር የመረጃ ክፍተት ነበር ብለዋል። ትንንሽ ጉዳዮችንም ማጋነን አይገባም ማለታቸው የሚታወስ ነው።