አቶ ኤርምያስ አመልጋ ፍርድ ቤት ቀረቡ የሚልና ሌሎችም ዜናዎች

በሚያንማር የታሰሩት ሁለት የሮይተርስ ጋዜጠኞች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

በሚያንማር የታሰሩት ሁለት የሮይተርስ ጋዜጠኞች

ኢትዮጵያ

የኦዲፒ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አለሙ ስሜ፤ መንግሥት ኦነግ በሰላማዊ መንገድ እንዲታገል መንገድ በማመቻቸቱ ሦስተኛ ወገን አስፈላጊ እንዳልሆነ ለቢቢሲ ገልጸዋል። ኦነግ በጉዳዩ የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ያስፈልጋል ብሎ እንደነበረ ይታወሳል።

• የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ስነ ምግባር ጎድሏቸዋል ያላቸውን 184 ፖሊሶችን እንዳባረረ የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል።

• የአክሰስ ሪልስቴት መስራች አቶ ኤርምያስ አመልጋ ዛሬ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አሥረኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል። አቶ ኤርምያስ የተጠረጠሩት ለሜቴክ ከሸጡት ኢምፔሪያል ሆቴል ጋር በተያያዘ መሆኑ ተዘግቧል።

ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ

የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ምርጫ ውጤት ይፋ መደረጉን ተከትሎ በተነሳ ግጭት አምስት ሰዎች መሞታቸውን ፖሊስ አስታውቋል። በምርጫው ካሸነፉትን ፌሊክስ ተስኬዲ ያነሰ ድምጽ ያገኙት ማርቲን ፋዩሉ ምርጫው ተጭበርብሯል እያሉ ነው።

ጋና

አንድ ጋናዊ የወርቅ ደላላ በማጭበርበር ከተከሰሰ በኋላ ከሀገሩ መሸሹ ተሰምቷል። ደላላው ከኢንቨስተሮች የወሰደውን ገንዘብ ለመመለስ እየሞከረ ነው የሚል መረጃ ቢናፈስም የጋና ከፍተኛ ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ አውጥቶበታል።

ማይናማር

ማይናማር የሮሂንጋ ሙስሊሞችን ግድያ የዘገቡት ሁለቱ የሮይተርስ ጋዜጠኞች ያቀረቡትን አቤቱታ ሳትቀበል ቀርታለች። ጋዜጠኞቹ የተፈረደባቸውን የሰባት ዓመት እስር ዓለም አቀፉ ማኀበረሰብ አውግዞታል።

ኔፓል

ኔፓላዊት እናትና ሁለት ልጆቿ ለወር አበባ በተከለለ ቤት ውስጥ ጭስ አፍኗቸው ህይወታቸው አልፏል። በኔፓል ባህል ሴት የወር አበባ በምታይበት ወቅት በተገለለ ቦታ ማስቀመጥ ቢከለከልም አሁንም በገጠሪቷ ክልል ይከናወናል።

ጓቲማላ

የጓቲማላ ሕገ መንግስታዊ ፍርድ ቤት የሀገሪቱ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መርማሪ ቡድንን ለማባበር ያስተላለፈውን ውሳኔ ቀለበሰ። መርማሪ ቡድኑ የሀገሪቱን ፕሬዘዳንት ከምርጫ 2015 የገንዘብ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ እየመረመረ ነበር።

ሳዑዲ አረቢያ

ሳዑዲ አረቢያዊቷ ራሀፍ አል-ቁኑን ወደ ካናዳ አቅንታ ጥገኝነት ልትጠይቅ ነው። ራሀፍ እስልምናን በመካዷ ቤተሰቦቿ ሊገድሏት እንደሚችሉ በመስጋት ከባንኮክ አውሮፕላን ማረፊያ አልወጣም ብላ እንደነበረ ይታወሳል።

እንግሊዝ

አንዲት የዘጠኝ ዓመት ታዳጊ በአስም በሽታ መሞቷን ተከትሎ እናቷ ክስ ልትመሰርት ነው። ታዳጊዋ ትኖርበት የነበረው መንገድ የተጨናነቀ በመሆኑ እናትየዋ የአየር ብክለትን ለመከላከል በቂ ጥረት አልተደረገም ስትል እንደምትከስ ጠበቃዋ ተናግረዋል።