በምዕራብ ኦሮሚያ ምን ተከሰተ?

በሆሮ ጉዱሩ ዞን ሆሮ ቡሉቂ በምትባል ወረዳ ውስጥ የሚገኝ 7 መስሪያ ቤቶችን የያዘ የወረዳ ጽ/ቤት መቃጠሉን የዞኑ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል። Image copyright ደሳለኝ ተረፈ

ባሳለፍነው ቅዳሜ እና እሁድ፤ ማለትም ጥር 4 እና 5፣ 2011 ዓ. ም. በምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ ባንኮች እንደተዘረፉና ንብረታቸው እንደወደመ እንዲሁም የወረዳ ጽህፈት ቤቶች በእሳት እንደጋዩ ተነገረ።

በሆሮ ጉዱሩ ዞን፤ ሆሮ ቡሉቂ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ ሰባት መሥሪያ ቤቶችን የያዘ የወረዳ ጽህፈት ቤት መቃጠሉን የዞኑ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ተረፈ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ደሳለኝ የታጠቁ ኃይሎች የሆሮ ቡሉቂ ወረዳ ዋና ከተማ ወደሆነችው ሰቀላ ከተማ በመግባት መሥሪያ ቤቶችን ማቃጠላቸውንና አዋሽ ባንክን መዝረፋቸውን ይናገራሉ።

''እነዚህ የታጠቁ ቡድኖች የአዋሽ ባንክ ሥራ አስኪያጅን ቤቱ ድረስ ሄደው በማምጣት ባንኩን አስከፈቱት።'' የሚሉት አቶ ደሳለኝ፤ ባንኩ ቢከፈትም የካዝናው ቁልፍ የባንኩ ሥራ አስኪያጅ እጅ ስላልነበረ ካዝናውን መክፈት ባለመቻላቸው ያገኙትን ገንዘብ ሰብስበው የባንኩን ሥራ አስኪያጅ አፍነው መሄዳቸውን ያስረዳሉ።

በተጨማሪም ከባንኩ ጥበቃዎች ሁለት ክላሺንኮቭ መዝረፋቸውን ይናገራሉ።

የአቢሲኒያ ባንክ የዝርፊያ ድራማ

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ሰማኒያ ሚሊዮን ብር እንዴት ተዘረፈ?

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የምዕራብ ዲስትሪክት ተጠባባቂ ሀላፊ አቶ ግርማ ጪብሳ፤ የባንክ ሠራተኞች በተለመደው ሁኔታ ደንበኞችን እያስተናገዱ ሳሉ ከረፋዱ አምስት ሰዓት አካባቢ ታጣቂዎች ወደ ባንኩ እንደገቡ ይናገራሉ።

በአጠቃላይ በምዕራብ ኦሮሚያ እና በቄለም ወለጋ በሚገኙ አሥር የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ላይ ጥቃት መሰንዘሩን አቶ ግርማ ይናገራሉ።

ሀላፊው፤ አምስት ቅርንጫፎች መዘረፋቸውን እንዲሁም በተቀሩት አምስት ቅርንጫፎች ውስጥ የሚገኙ መገልገያ ቁሳ ቁሶች ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ መደረጋቸውን ተናግረዋል። ኤቲኤም (ገንዘብ መክፈያ ማሽኖች) እና ኮምፒዩተሮች መሰባበራቸውንም ገልጸዋል።

ገንዘብ ከተዘረፈባቸው አምስት ቅርንጫፎች መካከል በሁለቱ አራት ሠራተኞች ታግተው እንደነበረ እና ሁለቱ እንደተለቀቁ አቶ ግርማ ጨምረው ተናግረዋል። "የተቀሩት ሁለት ሠራተኞች ስላሉበት ሁኔታ ግን ማወቅ አልቻልንም" ብለዋል።

በአካባቢው የደህንነት ስጋት ስላለ የደረሰውን ጉዳት ወደ ቅርንጫፎቹ ሄደን ለማጣራት አልቻልንም። መረጃም ተሟልቶ አልቀረበም የሚሉት አቶ ግርማ፤ እስካሁን በባንኩ እና በሠራተኞቹ ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን አለመታወቁን ይናገራሉ።

"ጥቃቱን ያደረሱት የታጠቁ ቡድኖች መሆናቸውን ሰምተናል። ይሁን እንጂ ዘረፋውን የፈጸመው አካል ይሄ ነው ብዬ መናገር አልችልም" በማለት አክለዋል።

በተመሳሳይ በምዕራብ ወለጋ እና ቄለም ወለጋ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ በርካታ ቅርንጫፎች እንዳሉት የሚያናገሩት የባንኩ የገበያ ጥናት እና የንግድ ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ በለጠ ዋቅቤካ፤ በባንኮቹ ላይ ጥቃት እንደተሰነዘረ ጠቅሰው፤ እስካሁን ምን ያህል የባንኩ ቅርንጫፎች እንደተዘረፉና ጥቃት እንደደረሰባቸው የጠራ መረጃ እንደሌላቸው ገልጸዋል።

አጭር የምስል መግለጫ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መለያዎች

የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ገመቺስ ተመስገን፤ ቅዳሜ ዕለት በዞኑ በሚገኙ ስድስት ወረዳዎች ውስጥ በመንግሥት እና በግል ባንኮች ላይ በተመሳሳይ ሰዓት ዘረፋ እንደተፈጸመ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ፣ ኅብረት ባንክ እና አዋሽ ባንክ እንደተዘረፉ ገልጸዋል። አቶ ገመቺስ እንደሚሉት፤ ዘረፋዎቹ የተፈጸሙት የሀገር መከላከያ ሠራዊት በሌለባቸው ስፍራዎች ነው።

ከባንክ ዘረፋው ጋር ተያይዞ ታፍነው የተወሰዱ የባንክ ሠራተኞች እንዳሉ የሚናገሩት አቶ ገመቺስ፤ ከመካከላቸው የተለቀቁ እንዳሉና፤ እስካሁን የት እንደደረሱ የማይታወቁ ሠራተኞችን እያፈላለጉ መሆኑን አስረድተዋል።

ይህን ጥቃት እየሰነዘረ ያለው የኦነግ ታጣቂ ነው የሚሉት አቶ ገመቺስ ''ከኦነግ ውጪ በእዚህ አካባቢ የታጠቀ ኃይል የለም'' ሲሉ ተናግረዋል።

የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምና የኦፕሬሽን ኃላፊ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ባለፈነው አርብ በሰጡት መግለጫ፤ በምዕራብ ኦሮሚያ ላለው የጸጥታ መደፍረስ የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን (ኦነግ) ተጠያቂ ያደርጋሉ።

ምክትል ኤታማዦር ሹሙ፤ በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦነግ ጦር ላይ መከላከያ እርምጃ እየወሰደ እንደሆነ ተናግረው ነበር።

ኦዲፒ፡ ኦነግ እንደ አዲስ ጦር መልምሎ እያሰለጠነ ነው

ከዚህ ቀደም የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ፤ በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ በኦሮሚያ በተለያዩ ስፍራዎች ይዘርፋል፣ አዲስ የኦነግ ጦር ይመለምላል፣ የክልል የመንግሥት ተቋሞችን ሥራ ያስቆማል፣ እንዲሁም የአካባቢውን አመራሮችን ይገድላል ሲሉ ተናግረዋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ የኦነግ ጦር አዛዥ ስለወቅታዊው ሁኔታ ምን ይላል?

የኦነግ ምላሽ

አቶ ሚካኤል ቦረና የኦነግ ሸኔ የሥራ አሰፈጻሚ ኮሚቴ አባል ናቸው። አቶ ሚካኤል ኦነግ ለበርካታ ዓመታት የኦሮሞን ሕዝብ ነጻ ለማውጣት ሲታገል የቆየ ድርጅት ነው። ኦነግ በምንም አይነት ሁኔታ እንዲህ ያለ ተግባር አይፈጽምም ይላሉ።

አቶ ሚካኤል የተፈጸመው ተግባር ሆነ ተብሎ የኦነግን ስም ለማጥፍት ነው ያሉ ሲሆን፤ ''መንግሥት ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ በርካታ ጦሩን አሰማርቷል፤ በየአካባቢው እየተካሄደ ስላለው ነገር ሙሉ መረጃ ለማግኘት ቸግሮናል'' ይላሉ።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የኦነግ የምዕራብ ዕዝ የጦር አዛዥ ኩምሳ ዲሪባ ወይም በቅጽል ስሙ መሮ፤ የክልሉ መንግሥት ኦነግ ላይ ያቀረበውን ወቀሳ በማስመልከት ለቢቢሲ ይህን ብሎ ነበር።

''. . . የተኩስ አቁም ስምምነቱን ከደረስን በኋላ ኦነግ በራሱ ተነሳሽነት መንግሥት ላይ ተኩስ ከፍቶ አያውቅም፤ አጸፋዊ እርምጃ ካልወሰድን በቀር። ይህ ሁሉ ክስ ግን ሃሰተኛ ነው። መንግሥት ይህን ክስ የሚያቀርበው በዚህ አካባቢ ላይ ጦሩን በማዝመት ጦርነት ለመክፈት ቅድመ ዝግጅት ሲያከናውን ነው እንጂ ኦነግ ያፈረሰው የመንግሥት ሥርዓት የለም፤ የዘረፈውም የጦር መሳሪያ የለም።''

የአየር ጥቃት

ዕሁድ ጠዋት የሀገር መከላከያ በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ የኦነግ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ላይ የአየር ጥቃት ሰንዝሯል የሚል መረጃ በስፋት ተሰራጭቶ ነበር።

የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ገመቺስ ተመስገን በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ጠይቀን፤ ''ይህ መረጃ እስካሁን አልደረሰኝም። በምዕራብ ኦሮሚያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ይንቀሳቀሳል። በተለያዩ አጋጣሚዎችም ከኦነግ ሠራዊት ጋር የተኩስ ልውውጥ አድርጓል። ዕሁድ ዕለት የአየር ጥቃት ተሰንዝሯል ወይም አልተሰነዘረም ማለት አልችልም'' ብለዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የአየር ጥቃት የተፈጸመው በቤጊ እና ጊዳሚ ወረዳዎች አዋሳኝ ድንበር ላይ መሆኑ በስፋት ተነግሯል። ይሁን እንጂ ያነጋገርናቸው የአከባቢው ነዋሪዎች "የአየር ጥቃት ተፈጽሟል ሲባል ሰማን እንጂ ያየነው ነገር የለም" ይላሉ።

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት፤ የአየር ጥቃት ሲፈጸም ባይመለከቱም በአከባቢው የጦር ሄሊኮፕተሮች በብዛት ስለሚመላለሱ ከፍተኛ ስጋት ገብቷቸዋል።

የኦነግ ሸኔ የሥራ አሰፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ሚካኤል ቦረና ግን መንግሥት በቤጊ እና ጊዳሚ ወረዳዎች ውስጥ የአየር ጥቃት እየሰነዘረ ነው ሕዝቡም እየተጎዳ ነው ብለዋል።

አቶ ሚካኤል እንደሚናገሩት፤ የኦነግ ጦር የነበረበትን ስፍራ ሳይለቅ እራስን የመከላከል እርምጃ እየወሰደ ነው።

ከፌደራል መንግሥት እንዲሁም ከመከላከያ ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ተያያዥ ርዕሶች