የሂትለር ሥዕሎች ለምን አልተሸጡም?

የሂትለር ሥዕል እንደሆነ የተገመተው የውሃ ቅብ ሥዕል Image copyright Reuters

ለናዚው መሪ አዶልፍ ሂትለር ሥዕል ነፍሱ ነበረች። አለመታደል ኾኖ ግን እርሷ አትወደመውም ነበር። ሂትለር ከአንዴም ሁለት ሦስቴ ከቪየና የሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት አመልክቶ "አትመጥንም" በሚል ተባሯል። ይህ ነገር ያበሳጨው ነበር።

ወደ ፖለቲካው መንደር ከመንደርደሩ በፊት በኦስትሪያ ቪየና የጉልበት ሥራ እየሠራ በዚያውም ያሰማመራቸውን ፖስትካርድና የሥዕል ሥራዎቹን በየመንገዱ እያዞረ ይሸጥ ነበር።

አንዳንድ ታሪክ ጸሐፊዎች ታዲያ ሰውየውን ጨካኝ ያደረገው ይኸው በሥዕል ለነበረው ፍቅር ዕውቅና የሚሰጠው ማጣቱ እንደሆነ ይገምታሉ።

ከሰሞኑ በሂትለር የተሳሉ እንደሆኑ የተነገረላቸው ሦስት ውሃ ቅብ ሥዕሎች ለጨረታ መቅረባቸውን የዓለም መገናኛ ብዙኃን ሲቀባበሉት ነበር።

የጀርመን ፖሊስ ግን ከሰዓታት በፊት ነገሩ 'ጭቦ' ሳይሆን አይቀርም፤ ተጠርጣሪዎቹንም በቁጥጥር ለማዋል አስቢያለሁ ብሏል።

የመጀመርያው ሥዕል ወንዝ፣ መልከአምድርና ዛፍን የሚያሳይ ሲሆን ሂትለር የለየለት ጨፍጫፊ ከመሆኑ በፊት ሙኒክ ሳለ የሳላቸው እንደሆኑ ሲነገር ነበር።

Image copyright Reuters

ለጨረታ ሊቀርቡ የነበሩት ሦስት ሥዕሎች በሥዕል ተቺዎች ዘንድ "ፈጠራ የማይታይባቸው፣ ግልብና መናኛ ሥዕሎች" እየተባሉ ሲተቹ ቆይተዋል።

ያም ኾኖ ለእያንዳንዱ ሥዕል መነሻ ዋጋ 4ሺህ 500 ዶላር ገደማ ተመድቦ ነበር። በኦንላይን ተጫራቾች ከፍተኛ ዋጋ ሊቀርብባቸው እንደሚችልም ግምት ተሰጥቶ ቆይቷል።

ለቢቢሲ ቃል የሰጡት የጀርመን ፖሊስ ቃል አቀባይ ፓትሪሺያ እንዳሉት ከሆነ ግን ሥዕሎቹ ሐሰተኛ ሳይሆኑ አይቀርም። ይኸው ጥቆማ ደርሶን ምርመራ ጀምረናል ብለዋል። እስካሁን ግን በቁጥጥር ሥር ያዋሉት ግለሰብ እንደሌለ ተናግረዋል።

Image copyright Reuters

ጨረታውን ያሰናዳው ድርጅትም እስካሁንም በጉዳዩ ላይ ትንፍሽ አላላም።

ሂትለር ሥልጣን ከጨበጠ በኋላ ለረዳቶቹ ሥዕሎቹን በያሉበት ፈልገው እንዲያቃጥሏቸው ቀጭን ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። ያም ኾኖ ሁሉንም አግኝቶ ማቃጠል አልተቻለም።

ያኔ ከቃጠሎ የተረፉት በግለሰቦች እጅ እንደሚገኙ ይገመታል። በአሜሪካ ጦር ኃይል የተወሰዱም በርካታ ናቸው።

አዶልፍ ሂትለር በቀን ቢያንስ ሦስት ሥዕሎችን ይሥል እንደነበር ይገመታል።

ተያያዥ ርዕሶች