በሴራሊዮን የገባበት ያልታወቀው 100 ሚሊዮን ዶላርና ሌሎች አጫጭር ዜናዎች

Image copyright EPA

ኢትዮጵያ

• የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግስት በ1987 ዓ.ም ከጸደቀ በኋላ የመጀመሪያው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ በመሆን ያገለገሉት አምባሳደር ዳዊት ዮሀንስ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

አምባሳደር ዳዊት በ1983 ዓ.ም የሽግግር መንግስት ሲመሰረት በህግ ቋሚ ኮሚቴና በሕገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን ፀሀፊ ሆነውም አገልግለዋል።

'ለሼህ አላሙዲ መፈታት የጠቅላይ ሚንስትሩ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር'

ብዙ ስላነጋገረው ኮሚሽን ማወቅ የሚገባዎ 5 ነጥቦች

ሱዳን

• በሱዳን እየካሄደ ያለውን ተቃውሞ ከአረብ አብዮት ጋር ለማያያዝ የሚመክሩ አካላት ስለመኖራቸው የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር ተናገሩ።

የዳቦና የነዳጅ ዋጋ ላይ በመንግስት የሚደረገው ድጎማ መቀነሱን በመቃወም የተጀመረው ሰልፍ ለ30 ዓመታት የመሩትን ፕሬዝዳንት ከስልጣን ማባረር በሚል ተቀይሯል።

ኬንያ

• ደብቀው ያስገቡትን ተንቀሳቃሽ ስልክ ወስዶብናል በሚል ሰበብ አስተማሪያቸው ላይ ግድያ ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሶስት ኬንያውያን ተማሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ።

ናኩሩ በተባለው የኬንያ ግዛት ሆፕዌል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የፊዚክስ መምህር የሆነው ፒተር ኦማሪ በተማሪዎቹ ጥቃት የተፈፀመበት ባለፈው ሳምንት መጠናቀቂያ ላይ ነበር።

ሴራሊዮን

• የገባበት ያልታወቀው 100 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ ላይ የተጀመረው ምርመራ ውጤት እንዲነገራቸው ላይቤሪያውያን ለፕሬዝዳንት ጆርጅ ዊሃ ጥያቄ አቀረቡ።

ባለፈው መጋቢት ወር ታትሞ ወደ ሃገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ ይገባል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ገንዘብ እስካሁን የት እንዳለ የሚጠቁም መረጃ አልተገኘም ተብሏል።

"አቶ ጌታቸው አሰፋን በተመለከተ ከክልሉ ጋር እየሰራን ነው" ዐቃቤ ሕግ

ሠላም የራቃት ድሬዳዋ

ካናዳ

• የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ በቻይና ሀገራቸውን ወክለው የሄዱትን አምባሳደር ከሁዋዌ ጋር በተያያዘ በሰጡት አስተያየት ምክንያት አባረሩ።

አምባሳደሩ የተባረሩት አሜሪካ በዋስ የተለቀቁት የሁዋዌ የፋይናንስ ኃላፊ ሜንግ ተላልፋ ትሰጠኝ ማለቷ ተገቢነት የለውም ማለታቸውን ተከትሎ እንደሆነ ተገልጿል።

አሜሪካ

• አሜሪካ በዲፕሎማቶቿ እና በተቃዋሚ መሪው ጁአን ጉአኢዶ ላይ ለሚደርሱ ማናቸውም አይነት ማስፈራሪያዎች ''የማያዳግም እርምጃ እወስዳለው'' ስትል የቬንዙዌላ መንግሥትን አስጠነቀቀች።

ተቃዋሚው ሁዋን ጉአኢዶ የቬንዙዌላ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት አድርገው እራሳቸውን መሾማቸውን ተከትሎ አሜሪካ እና ካናዳን ጨምሮ ከ20 ሃገራት በላይ እውቅናን አስገኝቶላቸዋል።

• በአሜሪካ የምትገኝ አንዲት ፕሮፌሰር ለተማሪዎቿ ቻይንኛ ቋንቋ እንዳትናገሩ ብላ መልእክት ማስተላለፏ ከስራዋ እንድትባረር መንስኤ ሆኗል።

ሜጋን ኒሊ የተባለችው መምህር ከቻይና የመጡ ተማሪዎች እንግሊዝኛ የማይናገሩ ከሆነ ያላሰቡት ቅጣት እንደሚጠብቃቸው አስጠንቅቃ ነበር ተብሏል።

ፔሩ

• በደቡብ ምሥራቅ ፔሩ ያጋጠመ የመሬት መንሸራተት ባደረሰው አደጋ የሠርግ ድግስ ላይ የታደሙ ቢያንስ 15 ሰዎችን መግደሉን ባለስልጣናት አስታወቁ።

በሆቴሉ አቅራቢያ የደረሰው የመሬት መንሸራተት የሠርግ ሥነ ሥርዓቱ ታዳሚዎች በፌሽታ ላይ የነበሩ ሰዎችን ያስተናግድ የነበረውን ሆቴል ግድግዳዎችና ጣራ እንዲደረመስ በማድረጉ ነው አደጋው የተከሰተው።