በጎንደር የተለያዩ ዞኖች በተከሰተ ግጭት 39ሺህ ሰዎች ተፈናቀሉ

የአማራ ክልል ኮሙኑኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰማኸኝ አስረስ
አጭር የምስል መግለጫ የአማራ ክልል ኮሙኑኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አሰማኸኝ አስረስ

ሰሞኑን በጎንደር እና ዙሪያው በተከሰቱ ግጭቶች በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን እና በሺዎች የሚቆጠሩ መፈናቀላቸውን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ።

የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው አቶ አሰማኸኝ አስረስ ዛሬ ከሰዓት ጋዜጠኞችን ሰብስበው ''ሰሞኑን በማዕከላዊ ጎንደር በምስራቅ ደንቢያ ወረዳ፣ ላይ አርማጨሆ እንዲሁም በጭልጋ አካባቢ ግጭቶች ተከስተው በሰዎች ሕይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል። ጎንደር አካባቢ በተፈጠረው ግጭት የተፈናቃዮች ቁጥር ወደ 39ሺህ ደርሷል'' ብለዋል።

አቶ አሰማኸኝ በባህር ዳር ከተማ በሰጡት መግለጫ፤ የዛሬ ሳምንት በዕለተ ዓርብ ጥር 24 በማዕከላዊ ጎንደር ሰፍሮ የነበረው የመከላከያ 24ኛ ክፍለ ጦር ቦታውን ለቅቆ 33ኛው ክፍለ ጦር እስኪረከብ ድረስ በተፈጠረው ክፍተት፤ ፅንፈኛ ያሏቸው ቡድኖች የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ላይ ተኩስ ከፍተው በሁለቱም ወገኖች መካከል የሰው ሕይወት መጥፋቱን ተናግረዋል። ከዚያ በኋላ ባሉት ቀናት የተለያዩ ቀበሌዎች የሰው ሕይወት መጥፋቱን እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶች በእሳት እንዲጋዩ መደረጋቸውን አብራርተዋል።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በተፈጠረ ግጭት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ

የማንነት ጥያቄዎች የጎሉበት የአማራ ክልል ከተሞች ሰልፍ

ጥር 27፣ 28 እና 29 በነባሩ ጭልጋ ወረዳ መቋሚያ ማርያም፣ ችሃ ማንጊያ፣ አማኑኤል ቀን ወጣ፣ ናራ እና አንከር አደዛ በተሰኙ ቀበሌዎች፤ ቤቶች መቃጠላቸውን እንዲሁም ጥር 29 እና 30 ደምቢያ ወረዳ ሰቀልተ ሰሃ መንጌ እና ድርማራ ቀበሌዎች ቤቶች መቃጠላቸውን እና በድርማራ ቀበሌ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉን ጨምረው ተናግረዋል።

እንደ አቶ አሰማኸን ገለፃ ትናንት ማታ በጎንደር በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ወጣቶች የከብት ማደለቢያ ላይ ቃጠሎ ደርሶ 40 የቀንድ ከብቶች ተቃጥለዋል። ቃጠሎው ከአለመረጋጋቱ ጋር መያያዝ አለመያያዙን ገና መጣራት እንዳለበትም ጨምረው አብራርተዋል። አቶ አሰማኸኝ በመቀጠል ያብራሩት፤ በምዕራብ ጎንደርም ግጭት እንደነበረና በዚህም ምክንያት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ነው።

ከዚህ በፊት የተፈጠረው ችግር መረጋጋት ቢያሳይም በቅርቡ ግን መተማ አካባቢ ችግር ተከስቶ የሰው ሕይወት ማለፉን አስረድተዋል።

''በምዕራብ ጎንደር ተከስቶ የነበረው ግጭት ወደ ሰላም እየመጣ ነው። ነገር ግን ጥር 30 በምዕራብ ጎንደር መተማ ወረዳ ግጭት ተከስቶ የአንድ ሰው ሕይወት አልፏል'' ብለዋል።

የጎንደር ሙስሊሞች እና የመስቀል በዓል

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ወልቃይትን አስመልክቶ ምላሽ ሰጡ

ለመሆኑ በግጭቱ የተፈናቀሉ ሰዎች ምን እየተደረገላቸው ነው ተብለው ተጠይቀው፤ መንግሥት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሆነ ገልፀው ማህበረሰቡ ዛሬም እርስ በእርሱ እየተደጋገፈ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በዛሬው ዕለት ከጎንደር አርማጨሆ የትራንስፖርት አገልግሎት ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም 2 ሰዎች በመታገታቸው ምክንያት ሌሎች ላይ የማሳደድ ተግባር በመፈፀሙ መቋረጡን ተናግረዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን የፖሊስ መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ኮማንደር እንየው ዘውዴ ደግሞ ለቢቢሲ ሲናገሩ ''አማራ እና ቅማንት ለረዥም ዓመታት አብረው የኖሩ እና ወደፊትም አብረው የሚኖሩ ሕዝቦች ናቸው። ነገር ግን በመካከላቸው ሌላ ኃይል ገብቶ ደም እያቃባ ይገኛል። እሱን ለመከላከል የክልሉ ኃይል እና ሃገር መከላከያ በመቀናጀት ሥራ እየተሠራ ነው''ብለዋል።

ኮማንደር እንየው ''ሌላ ኃይል'' ያሉት ቡድን የትኛው እንደሆነ እንዲነግሩን ላቀረብንላቸው ጥያቄ ''ይሄ ግልጽ ነው። ሁሉም ያውቀዋል። የአደባባይ ምስጢር ነው'' ከማለት ውጪ እሳቸው ''ኃይል'' አቶ አሰማኸኝ ደግሞ ''ጸንፈኛው ቡድን'' ያሉትን አካል በስም ከመጥቀስ ተቆጥበዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ