ኢትዮጵያ፡ ዲዛይን ዊክ አዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

በዲዛይን ዊክ አዲስ አበባ የፈጠራ ሥራዎች ይተዋወቃሉ Image copyright Gallery 26/ Design Week Addis Ababa
አጭር የምስል መግለጫ በዲዛይን ዊክ አዲስ አበባ የፈጠራ ሥራዎች ይተዋወቃሉ

ፓሪስ ዲዛይን ዊክ፣ ኒው ዮርክ ዲዛይን ዊክ፣ ኢስታንቡል ዲዛይን ዊክ፣ ዱባይ ዲዛይን ዊክ. . . በዓለም እውቅናን ካተረፉ የዲዛይን መሰናዶዎች መካካል ይጠቀሳሉ።

ቢያንስ ለአንድ ሳምንት በሚካሄዱት የዲዛይን መሰናዶዎች ሥነ ህንጻ፣ ሥነ ጥበብ፣ ቴክኖሎጂና ፋሽንን ጨምሮ በርካታ ዘርፎች ይዳሰሳሉ። የፈጠራ ባለሙያዎች ሥራዎቻቸውን ያሳያሉ፤ ግብይት፣ ውይይትና የልምድ ልውውጥም ይደረጋል።

እነዚህ ዓለም አቀፍ የዲዛይን መድረኮች ከሚሰናዱባቸው ሀገሮች ባለፈ ከሌሎች ሀገራትም ታዳሚዎችን ይስባሉ።

የሀብ ኦፍ አፍሪካ ፋሽን ሳምንት ፎቶዎች

የ2010 የጥበብ ክራሞት

አዲስ አበባ የዲዛይን ሳምንት የማስተናገድ ሀሳብን ከወረሰች አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል። ዲዛይን ዊክ አዲስ አበባ የሚል መጠሪያም ተሰጥቶታል።

Image copyright Gallery 26/ Design Week Addis Ababa
አጭር የምስል መግለጫ የአራተኛው ዲዛይን ዊክ አዲስ አበባ ታዳሚዎች

የዲዛይን ሳምንቱ በፈጠራ ዘርፍ ያለውን እንቅስቃሴ ለማስተዋወቅና ለማጠናከር እንደተወጠነ የዲዛይን ዊክ አዲስ አበባ መስራችና ዳይሬክተር መታሰቢያ ዮሴፍ ትናገራለች።

በዲዛይን ዊክ አዲስ አበባ ከተካተቱ ዘርፎች ውስጥ የሥነ ህንጻና የከተማ ዲዛይን፣ ፋሽንና ጨርቃ ጨርቅ፣ ቴክኖሎጂ፣ ግራፊክ ዲዛይን፣ የምግብ አዘገጃጀት ይገኙበታል።

ለፈጠራ ሥራዎች መድረክ መስጠት

በተለያየ ዘርፍ ያሉ የፈጠራ ሥራዎች ተመልካች ጋር የሚደርሱበት በቂ መድረክ አለ? የሚለው አጠያያቂ ነው። አብዛኞቹ ፈጠራዎች ከሙያ ዘርፉ ውጪ ላሉ ሰዎች የሚደርሱበት መድረክ ሲያገኙ አይስተዋልም።

Image copyright Gallery 26/ Design Week Addis Ababa
አጭር የምስል መግለጫ መታሰቢያ ዮሴፍ

በዲዛይን ሳምንት ውስጥ የተካተቱት የፈጠራ ዘርፎች በቂ መድረክ ማግኘት ያልቻሉ መሆናቸውን መታሰቢያ ታስረዳለች። ዲዛይን ዊክ አዲስ አበባ ክፍተቱን በመጠኑም ቢሆን ለመድፈን እንደሚሞክር መስራቿ ታክላለች።

"ሁሉም ሥራቸውን በተወሰነ መንገድ ሲያቀርቡ ነበር። በዲዛይን ዊክ አዲስ አበባ ግን ሰፊ መድረከ ተሰጥቷቸዋል።"

ረሃብ የቀሰቀሰው ፈጠራ

የአገልግል ምግብ አምሮዎታል?

ለምሳሌ አንድ ምግብ አብሳይ ቅመማ ቅመም አዋህዶ፣ ልዩ ጣዕም በመፍጠር አዲስ ምግብ ይሠራል። የምግብ አቀራረቡም ፈጠራ ይታከልበታል። ይህን ጥበብ እንደ ዲዛይን ዊክ አዲስ አበባ ባሉ መሰናዶዎች ማሳየት ይችላል።

የቴክኖሎጂ ውጤቶች፣ የሥነ ህንጻና የከተማ ዲዛይን እንዲሁም የሥነ ጥበብ ሥራዎችም ለእያታ ይበቃሉ።

Image copyright Gallery 26/ Design Week Addis Ababa
አጭር የምስል መግለጫ ዲዛይን ዊክ አዲስ አበባ የተለያዩ ሀገሮች ተሞክሮን የተመረኮዘ ነው

ከ18 ዓመት እስከ 60 ዓመት

ዲዛይን ዊክ አዲስ አበባ ባለፉት አራት ዓመታት የተለያየ ሙያ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደረጃ ያላቸውን ሰዎች ማሰባሰብ መቻሉን መታሰቢያ ትገልጻለች።

"ከ18 እስከ 60 ዓመት ሰው እናገኛለን። የተመልካቾች አይነት እየሰፋ፤ ቁጥሩም እየጨመረም ነው።"

የተለያየ ዘርፍ የፈጠራ ውጤቶች አንድ ላይ መገኘታቸው ተመልካቾችን እንደሳበ ታምናለች።

እንደ ፋሽንና ግራፊክስ ዲዛይን ያሉት ዘርፎች የተሻለ ተደራሽነት አላቸው። የቤት ውስጥ መገልገያዎች ሥራ እንዲሁም የቤት ውስጥ ዲዛይን ደግሞ ብዙም እውቅና ያልተቸራቸው ናቸው። የዲዛይን ሳምንት በሁለቱ መካከል ድልድይ ዘርግቷል።

አራተኛው ዲዛይን ዊክ አዲስ አበባ የተጀመረው ሰኞ የካቲት 4/ 2011 ዓ. ም ሀያት ሪጀንሲ ውስጥ ነበር። 'ያኔ ኮሌክሽን' የተባለ ተቋም የኢትዮጵያና የኤርትራን ባህል የተመረኮዙ የጌጣ ጌጥ ምርቶች አስተዋውቋል።

አንድ ፈረንሳዊ ዲዛይነር ላሊበላ ላይ የሠራውን ፕሮጀክት አቅርቧል። 'ሼፒንግ አዲስ ስሩ ኢኖቬሽን' በሚል ርዕስ የከተማ እቅድ ላይ ያተኮረ ወርክሾፕም ተካሂዷል።

እስከ የካቲት 10/ 2011 ዓ. ም ድረስ ዐውደ ርዕይ፣ የሙዚቃና የምግብ መሰናዶ፣ ባዛርና ወርክሾፖች ይካሄዳሉ።

Image copyright Gallery 26/ Design Week Addis Ababa
አጭር የምስል መግለጫ የሥነ ህንጻና የከተማ ዲዛይን ከፈጠራዎቹ መካከል ይገኙበታል

"ቀላል ባይሆንም አስፈላጊ ስለሆነ እናደርገዋለን"

መሰል መሰናዶዎች ብዙም ባልተለመዱበት ሀገር የዲዛይን ሳምንትን በገንዘብ የሚደግፉ ሰዎች ወይም ድርጅቶች ማግኘት ከባድ መሆኑን መታሰቢያ ትናገራለች።

ከተለያዩ ሀገሮች የዲዛይን ሳምንት የተወረሰው የአዲስ አበባው የዲዛይን ሳምንት፤ ፈጠራን በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት መስራቿ ገልጻ፤ "ቀላል ባይሆንም አስፈላጊ ስለሆነ እናደርገዋለን" ትላለች።

ብዙዎች ሀሳቡን ባለመገንዘብ ለመደገፍ ቢያቅማሙም፤ ግንዛቤው ሲያድግ ሂደቱ ቀላል እንደሚሆን ተስፋ ታደርጋለች።

ኢትዮጵያ ውስጥ የተመረቱና ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠሩ ሥራዎችን በማስተዋወቅ እንደምትገፋ መታሰቢያ ትገልጻለች።

በዲዛይን ዊክ አዲስ አበባ ላይ ሥራቸውን ማሳየት የሚፈልጉ ሰዎች፤ ሥራዎቻቸውን ከስድስት ወር በፊት ካስረከቡ በኋላ በኮሚቴ ተገምግሞ ለእይታ የሚበቁት ይመረጣሉ።