ኢትዮጵያ፡ በፍቅረኞች ቀን የፍቅር ስጦታ ለሴት ተማሪዎች

ቢጫ ንቅናቄን የሚወክል አበባ Image copyright Martha Tadesse
አጭር የምስል መግለጫ ቢጫ ንቅናቄን የሚወክል አበባ

ከስምንት ዓመት በፊት ነበር። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ፤ የጾታ እኩልነት ጥያቄ ያነገቡ ተማሪዎች 'የሎ ሙቭመንት' (ቢጫ ንቅናቄ) የተሰኘ ቡድን የመሰረቱት። ተማሪዎቹ ጾታን መሰረት ያደረገ አድልዎን ለመታገል በተለያየ መንገድ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውንም ገፉበት።

የሳዑዲ ሴቶች መሪ ጨበጡ

ሴቶች የተቆጣጠሩት የስፔን ካቢኔ

ሩት ይትባረክ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲውን የሎ ሙቭመንት ወደ መቐለ ዩኒቨረስቲ የወሰደችው የተቋሙ ተማሪ ሳለች ነበር።

Image copyright Martha Tadesse
አጭር የምስል መግለጫ ወጣቶች አበባ በመሸጥ ላይ

ከየሎ ሙቭመንት ተግባሮች አንዱ የሆነውን የፍቅረኞች ቀን የአበባ ሽያጭ በማስተባበር ላይ ሳለች አነጋግረናታል።

እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ዘንድሮም አበባ በመሸጥና ለሰዎች የአበባና የቸኮሌት ስጦታ በማድረስ ገንዘብ እያሰባሰቡ ነው። ገንዘቡ ችግረኛ ለሆኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሴት ተማሪዎች ተሰጥቶ የንጽህና መጠበቂያ ሞዴስና ሌሎችም አስፈላጊ ነገሮች ለመግዛት ይውላል።

ለአካል ጉዳተኛ ሴት ተማሪዎች የገንዘብ ድጎማም ያደርጋሉ።

በፍቀረቀን የፍቅር ስጦታ ለሴት ተማሪዎች

የፍቅረኞች ቀን የሚከበርበት ወቅት አበባ በብዛት የሚመረትበት ነውና አበባ እንደልብ ይገኛል። ዘንድሮ አራት አበባ አምራች ፋብሪካዎች ወደ 15 ሺህ የሚጠጉ አበቦች እንደለገሷቸው ሩት ትናገራለች።

"ፍቅር ደግነት ከሆነና ሰዎች በዚህ ቀን አበባ መግዛታቸው ካልቀረ ለምን ለጥሩ ነገር አይውልም? ስንል የጀመርነው ንቅናቄ ነው" ትላለች።

ወቅቱ ተማሪዎች እረፍት የሚያደርጉበት በመሆኑም ብዙ በጎ ፍቃደኛ ተማሪዎች ለማግኘትም ያመቻል።

ታሪክ እየቀየሩ ያሉት ሴቶች

የሴቶች ብቻ መጓጓዣዎች ትንኮሳን ይቀንሳሉ?

አንድ ሰው የየሎ ሙቭመንት አባላትን "ለእከሌ አበባ ስጡልኝ" ብሎ መላክ ይችላል።

ሩት ባነጋገርናት የፍቅረኞች ቀን ብቻ ለአምስት ሰዎች አበባ ማድረሷን ነግራናለች። በሰዎች መኖሪያ ቤት፣ በመሥሪያ ቤትና ለወለደች ሴት።

አበባዎቹ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ በአሜሪካ ኤምባሲ እና እፎይ ሬስቶራንትን ጨምሮ በለያዩ አካባቢዎች ይሸጣሉ።

አንዲት ተማሪን ለአንድ ዓመት ስፖንሰር የሚያደርግ ትልቅ የአበባ እስር 2,000 ብር፣ አንድ አበባ ደግሞ 30 ብር ይሸጣል።

Image copyright Martha Tadesse
አጭር የምስል መግለጫ ወጣቶች አበባ በመሸጥ ላይ

ከገንዘብ ልገሳ ባለፈ

የዘንድሮው የአበባ ሽያጭ ያስገኘው ገቢ ገና ባይሰላም አምና 216 ሺህ ብር ተሰብስቦ 186 ሴት ተማሪዎች መረዳታቸውን ሩት ትናገራለች።

የሎ ሙቭመንት ለፍቅረኞች ቀን አበባ ሸጦ ገንዘብ ከማሰባሰብ በተጨማሪ፤ የጷግሜ ንቅናቄን ጨምሮ በማኅበራዊ ሚዲያ ንቅናቄዎችና 'ቴብል ደይ' በተባለው ሳምንታዊ የውይይት መድረክም ይታወቃል።

መድረኩ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ አስተማሪዎች በጾታ እኩልነት ላይ ውይይት የሚያደርጉበት ነው።

"በትንንሽና ቀጣይነት ባላቸው ድምጾች እናምናለን" የምትለው ሩት፤ ዘለቄታዊ ለውጥ የእንቅስቃሴዎቹ ድምር ውጤት መሆኑን ታስረዳች።

ችግረኛ ሴት ተማሪዎች የንጽህና መጠበቂያ ሞዴስ እንዲያገኙ ከማድረግ በተጨማሪ ስለ ወር አበባ ያለውን የተዛባ አመለካከት መቅረፍም ግባቸው ነው።

ሩት እንደምትለው፤ "የወር አበባ እንደ ቆሻሻ መታየቱ እንዲቀር እንፈልጋለን። በአንድ ወቅት በሰራነው ስሌት አንዲት ሴት በወር አበባ ምክንያት በወር ሦስት ቀን ከትምህርት ቤት ከቀረች በአንድ የትምህርት ክፍለ ዘመን 18 ቀን ትቀራለች ማለት ነው። ይህም ብቃት እያላትም ከእኩዮቿ ጋር እኩል እንዳትፎካከር ያደርጋታል"

የተዛባውን አመለካከት ለማቅናት መሰል እንቅስቃሴዎች አጋዥ ናቸው።

Image copyright Martha Tadesse
አጭር የምስል መግለጫ አበባ ለመሸጥ ሲያዘጋጁ

አበባ በአማካይ ከሚሸጥበት ገንዘብ ጨምረው ከየሎ ሙቭመንት አባላት አበባ የሚገዙ ሰዎች ቁጥር ከዓመት ወደ ዓመት እየጨመረ መምጣቱ፤ ሰዎች አላማቸውን ተረድተው እየደገፉ ስለመሆኑ ማሳያ እንደሆነ ታምናለች።