"ታከለ ኡማ አዲስ አበባን መምራት የለባቸውም"

እስክንድር ነጋ Image copyright YONAS TADESSE

በተደጋጋሚ ለእስር የተዳረገውና በሽብር ተከሶ ከሰባት አመታት እስር ቆይታ በኋላ ባለፈው አመት የተፈታው እስክንድር ነጋ የተለያዩ አስተያየቶች ብዙዎችን እያነጋገሩ እያወዛገቡም ይገኛሉ።

ከነዚህም ውስጥ በቅርቡ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ለአዲስ አበባ ህዝብ ጥቅም የቆሙ አይደሉም፤ "በምርጫ እንቀጣቸዋለን" የሚለው አስተያየቱ የሚጠቀስ ሲሆን ይህም ብዙዎችን እያወዛገበ ይገኛል።

እነ እስክንድር ነጋ ተለቀቁ

"በሰላማዊ ትግል እስከመጨረሻው በፅናት እንታገላለን" እስክንድር ነጋ

"አዲስ አበባን መምራት የለባቸውም" የሚል ጠንካራ አቋም ያለው እስክንድር ለዚህ የሚያስቀምጠው "አቶ ታከለ ኡማ አብዛኛውን የአዲስ አበባን ህዝብ አመለካከት አይጋሩም፤ የአዲስ አበባን ህዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ፤ ለአዲስ አበባ ህዝብ መብት ለመከራከር አይችሉም።" የሚል ምክንያት ነው።

በተለይም በህገመንግሥቱ የሰፈረውና ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም አላት የሚለው አቋማቸው የብዙኃኑን አዲስ አበቤ አመለካከት እንደማይወክል የሚናገረው እስክንድር ከንቲባው ለለውጡ ያደረጉት አስተዋፅኦ ግን መታወስ እንዳለበት ያስገነዝባል።

"እኔ ታከለ ኡማን እንደ ሰው አከብራቸዋለሁ፤ በለውጡ ሂደትም አስተዋፅኦ አበርክተዋል፤ ለሱም ዋጋ እሰጣለሁ። ለዚህም ካደረጉት አስተዋፅኦ አንፃር በፌደራል የሚኒስትርነት ቦታ ወይም በኦሮሚያ ክልል መሾም ነበረባቸው።" ይላል

"አዲስ አበባን እንዲመሩ መሾም አልነበረባቸውም" ብሎ አጥብቆ የሚከራከረው እስክንድር ሹመቱ በአጠቃላይ ሲታይም በሽግግሩ ላይ ያለውን ክፍተት የሚያሳይ ነው ብሎ ያምናል። "የብዙኃኑን አመለካከት እንደማይወክሉ እየታወቀ፤ እንዴት ከተማዋን እንዲመሩ ተመረጡ? ሲልም ይጠይቃል።

ከተማ ይፍሩ፡ ያልተነገረላቸው የአፍሪካ አንድነት ባለራዕይ

ሃገሪቱ ላይ በተፈጠረው ለውጥ ደስተኛ መሆኑን የሚናገረው እስክንድር ለውጡ ለአመታት ሲጠበቅ የነበረ እንደሆነ ገልጿል።

ለአመታት ተለያይቷቸው የነበረው ቤተሰቡን ማየት መቻሉ እንደ ግል ስኬት የሚቆጥረው እስክንድር "ቢቻል ሃገሪቷ ተረጋግታ ወደ አገር ቤት ቢመለሱ ደስ ይለኝ ነበር። ነገር ግን ባለፈው አንድ አመት ውስጥ ሃገሪቷ ስላልተረጋጋች ቤተሰቡ ወደ ሃገር ውስጥ መመለስ አልቻለም። ስለዚህ አሁንም እንደተለያየን ነው" ብሏል።

ነገር ግን በሃገር ደረጃ " የዲሞክራሲያዊ ሽግግሩ መድረስ የሚገባው ቦታ ላይ ደርሷል ወይ?" የሚለውን ዋና ጥያቄ ሲመዝነው ለውጡ ባለፈው አንድ ዓመት እንደተፈለገው ሄዷል ብሎ እንደማያምን ይናገራል።

"ከዚህም አልፈን መሄድ ነበረብን ብዬ አምናለሁ" ይላል። እንደ ምሳሌም የሚያነሳው አቶ ጌታቸው አሰፋ የእስር ትዕዛዝ ቢወጣባቸውም አለመታሰራቸው ያለውን ክፍተት የሚያሳይ ነው ብሏል።

እስክንድር በተለይም ቄሮን በተመለከተ በሰጠው አስተያየት ብዙ ነቀፌታዎች የተሰነዘሩበት ሲሆን " እንዲፈታ ላደረገው ትግል ውለታ ቢስ ሆኗል" የሚል አስተያየትም አይሎ ወጥቷል።

የሃሳብ ልዩነትን በፀጋ እንደሚቀበል የሚናገረው እስክንድር "የተለያዩ ሃሳቦች እንዲንሸራሸሩ ነው የታገልነው" ይላል። ነገር ግን ከቄሮ ጋር ተያይዞ በሰጠው አስተያየት ከሃሳብ ልዩነት አልፎ እንገድልሃለን የሚሉ ማስፈራሪያዎችንና ዛቻዎችን እንዳስተናገደ ይናገራል።

"በአጠቃላይ ይሄ እንደ ሃገር መወገዝ አለበት፤ እንደተባለው ውለታ ቢስ ብሆንም እንኳ እኔ በሃሳብ እንጂ በዛቻ ልሸነፍ አይገባም" ይላል።

ይሄ ኃይልን እንደ መሳሪያነት መጠቀም መፈለግን ሙጥኝ የማለት ባህል እንዳለም አመላካች ነው ይላል።

እስክንድር ብዙ ጊዜ "አክራሪው ቄሮ" እያለ አስተያየት ቢሰጥም ቄሮን ለሁለት ይከፍለዋል።

"ጤናማው ቄሮ እንዲሁም አክራሪው ቄሮ አለ። አክራሪው ቄሮ ለአገር አደጋ ነው ብያለሁ። አሁንም የማምንበት ጉዳይ ነው። በአጠቃላይ ቄሮ ለአገር፣ለዴሞክራሲው አደጋ ነው አላልኩም። አክራሪው ቄሮ አደጋ የሆነው በያዘው ፖለቲካዊ አመለካከት ወይም አቋም ሳይሆን ኃይልን ለመጠቀም በመፈለጉ ነው። ለዚህ ደግሞ አባ ቶርቤ በሚል ተደራጅተው የነበሩ ወጣቶች ማስረጃ ናቸው።" ይላል

እሱ እንደሚለው ይህ ሃይልን የመጠቀም አካሄድ ደግሞ ቄሮ በተለይ አምባገነናዊውን ስርአት ለመጣል ያደረገውን እንቅስቃሴ አፍራሽ ነው።

ስለዚህም "ከለውጡ በኋላ ሁለት ቄሮ አለ ፅንፈኛውን መታገል አለብን" ይላል።

በተደጋጋሚ ለእስር የተዳረገው እስክንድር በአሁኑ ወቅት የኢትዮጲስ ጋዜጣ ባለቤት ነው። ቀደም ሲልም የሰርካለም ማተሚያ ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ የነበረ ሲሆን በስሩም አስኳል፣ ሳተናውና ሚኒልክ የተባሉ ጋዜጦችንም ያሳትም ነበር።

የ1997ዓ.ም ምርጫ ቀውስን ተከትሎ ጋዜጦቹ የተዘጉ ሲሆን ከዚያም በሽብር ለእስር የበቃው እስክንድር ከአንድ አመት በፊት ከበርካታ የፖለቲካ እስረኞች ጋር በይቅርታ እንደተፈታ የሚታወስ ነው።