ናይጄሪያ፡ ሙሐመዱ ቡኻሪ ምርጫ የሚያጭበረብሩን አልታገስም አሉ

የናይጄሪያ ርዕሰብሄ ር ሙሃመዱ ቡሃሪ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የናይጄሪያው ፕሬዝዳንት ሙሀመድ ቡኻሪ ፖሊስና ወታደሩን ምርጫ የሚያጭበረብሩ ግለሰቦች ላይ "የማያዳግም እርምጃ " እንዲወስዱ ማዘዛቸውን ተናገሩ፤ ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት በመጨረሻ ሰዓት ላይ ምርጫው መራዘሙ ከተገለፀ በኋላ ነው።

ይህንን የርዕሰ ብሔሩን ሐሳብ የተቹ አካላት ንግግሩን "ማን አለብኝነት እንዲሰፍን መንገድ የሚጠርግ" ሲሉ አጣጥለውታል።

ቡኻሪ የምርጫ ኮሚሽኑንም ለምን ምርጫው እንዲራዘም እንዳደረገ ማጣራት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

የምርጫ አስፈፃሚ አካላት ግን ለምርጫው መራዘም ያቀረቡት ሰበብ "ለምርጫ የሚሆኑ ግብአቶች አልተሟላም" የሚል ነበር።

ርዕሰ ብሔሩ ይህንን ንግግር ያደረጉት ፓርቲያቸው ኦል ፕሮግረሲቭ ኮንግረስ ፓርቲን (ኤፒሲ) አስቸኳይ ስብሰባ እንቀመጥ ብለው አቡጃ ውስጥ በሰበሰቡበት ወቅት ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

"ማንም የምርጫ ኮሮጆን የሚገለብጥ ወይንም ምርጫውን ለመረበሽ አደገኛ ቦዘኔዎችን የሚያሰማራ ያ ወንጀል የሕይወቱን ፍጻሜ ታቀርበዋለች" ሲሉ በጠንካራ ቃላት አስጠንቅቀዋል።

አክለውም ማንም ምርጫውን ለማደናቀፍ የሚሞክር አካል "በሕይወቱ ፈርዶ" ነው ሲሉም አስተያየታቸውን አጠናቅቀዋል።

የናይጄሪያ ዋናው ተቀናቃኝ ፓርቲ ግን "ማን አለብኝነት እንዲሰፍን የተደረገ ጥሪ ነው" ሲል የርዕሰ ብሔሩን ሐሳብ ኮንኖታል።

"ይህ ከአንድ ሀገር መሪ የማይጠበቅ፣ በይፋ ግደሉ የሚል አዋጅ ነው" ብለዋል የተፎካካሪ ፓርቲው ቃል አቀባይ ኮላ ኦሎግቦንዲያን።

በናይጄሪያ የሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊና የሕዝብ እንደራሴዎች ምርጫ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው ባለፈው ቅዳሜ ሲሆን ምርጫው ሊካሄድ አምስት ሰዓታት ብቻ ሲቀረው መተላለፉ ተገልጿል።

ለዚህም እንደ ምክንያት የቀረበው የናይጄሪያ አንዳንድ አካባቢዎች የምርጫ ወረቀቶች ማጓጓዝ ስላልተቻለ የሚል ነበር።

ምረጫው የፊታችን ቅዳሜ ይካሄዳል ተብሎ ዳግም ቀጠሮ ተይዞለታል። ነገር ግን የምርጫ ታዛቢዎች በዚህም ላይ ጥርጣሬ አላቸው።

የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎች ቡድንን የሚመሩት የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ መሆናቸው ይታወቃል።