ዶናልድ ትራምፕ ተከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የ16 የአሜሪካ ግዛቶች ጥምረት ዶናልድ ትራምፕ ላይ ክስ መሥርቷል። የክሱ ጭብጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያለ አግባብ በማወጅ ለግንብ አጥር ብር ለማግኘት ሞክረዋል የሚል ነው። ጥምረቱን የሚመራው የካሊፎርኒያ ግዛት ነው።
ክሱ የተከፈተበት ፍርድ ቤትም ኖርዘርን ዲስትሪክት ኦፍ ኮሎምቢያ ነው።
ትራምፕ የኮንግረሱ ፍቃድ ሳያሻቸው ገንዘብ ለማግኘት በማሰብ አገሪቱ በስደተኞች ቀውስ ውስጥ ስለምትገኝ ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጅ አውጃለሁ ብለው ይህንኑ ተግባራዊ አድርገዋል።
ዲሞክራቶች በበኩላቸው የትራምፕን 'ብልጣብልጥነት' በሚቻላቸው ሁሉ እንደሚመክቱ ዝተዋል።
የካሊፎርኒያ አቃቢ ሕግ ዣቪየር ባሴራ 'ትራምፕ ሥልጣናቸውን ያለአግባብ እየተጠቀሙበት ስለሆነ ፍርድ ቤት እንገትራቸዋለን' ብለዋል።
የፍርድ ቤት የመጀመርያ ተግባር የሚሆነው ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጁ ለጊዜው የፍርድ ሒደቱ እልባት እስኪያገኝ እንዲቆይ ማድረግ ነው።
ትራምፕ ይህን የአደጋ ጊዜ አዋጅ ያወጁት ኮንግረሱ ለአጥር የሚሆን ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆን ገንዘብ ሊፈቅድላቸው ባለመቻሉ ነው።
በሜክሲኮ አዋሳኝ ድንበር ላይ እንዲገነባ የተፈለገው ግዙፍ አጥር በድምሩ 23 ቢሊዮን ዶላር ያስወጣል። ኾኖም ትራምፕ ኮንግረሱ እንዲያጸድቅላቸው ጠይቀው የነበረው የገንዘብ መጠን ከ6 ቢሊዮን ያነሰ ነበር።
አሁን በዚህ የአደጋ ጊዜ አዋጅ ትራምፕ ቢያንስ ስምንት ቢሊዮን ዶላር ያለ ከልካይ ከአሜሪካ ካዝና ማውጣት ያስችላቸዋል።
አሜሪካ ከሜክሲኮ ጋር የምትጋራው የድንበር ርዝማኔ 3ሺህ 2 መቶ ኪሎ ሜትር ነው።
ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጅ ምንድነው?
ይህ አዋጅ ተግባራዊ የሚሆነው የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር አገሪቱ ቀውስ ውስጥ እንዳለች ባመነበት ጊዜ ነው። አወዛጋቢው ትራምፕ አገሬ የስደተኞች ቀውስ ውስጥ ገብታለች ብለው እየተከራከሩ ነው። የስደተኞች ጉዳይ ተንታኞች ግን ትራምፕ ቲያትር እየሠሩ ናቸው ሲሉ ይከሳሉ።
የአደጋ ጊዜ አዋጅ ርዕሰብሔሩ የተለመደውን የፖለቲካ አካሄድ ሳይከተሉ ያሻቸውን እንዲያደርጉ ዕድል ይሰጣል።