በካናዳ 7 ሕፃናት በእሳት ቃጠሎ ምክንያት ሞቱ

7 ሕፃናት የሞቱበት ቤት

የፎቶው ባለመብት, Robert Short/CBC

ሰባት ታዳጊዎች በአንድ ቤት ውስጥ የእሳት እራት መሆናቸው ከካናዳዋ ሃሊፋክስ ተሰምቷል። እነዚህ ታዳጊዎች የአንድ ቤተሰብ አባላት ይሆናሉ ተብሎም ተገምቷል።

አንድ ወንድና ሴትም በእሳቱ ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በቤቱ ውስጥ የተነሳው እሳት የመጀመሪያውንና ሁለተኛውን ፎቅ ወዲያው እንደተቆጣጠረው ገልጿል።

ፖሊስ የሟቾቹን ማንነት እስካሁን ድረስ ባይገልፅም አንድ የዜና ተቋም ግን ሟቾቹ የሶሪያ ስደተኞች ናቸው ሲል ዘግቧል።

ቤተሰቡ ወደ ካናዳ ከመጣ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ገደማ ቢሆነውም ወደ ሐሊፋክስ ከተዘዋወሩ ግን ስድስት ወር እንደሆናቸው የአካባቢው ኢማም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እሳቱ ሕይወታቸውን ከነጠቃቸው ታዳጊዎች መካከል ትንሹ የአራት ወር ሕፃን ሲሆን ትልቁ ደግሞ የ15 ዓመት ጎረምሳ ነው።

በአካባቢው የሚገኝ ስደተኞቹን መልሶ በማቋቋም ላይ የተሰማራ አንድ ድርጅት በፌስ ቡክ ገፁ ላይ እንዳሰፈረው ቤተሰቦቹ የባርሆ ናቸው ብሏል።

የተጎዳው ግለሰብ ሕይወቱ በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝና በሆስፒታል የፅኑ ህሙማን ክፍል ክትትል እየተደረገለት እንደሆነ ተዘግቧል።

የእሳት አደጋ ሰራተኞች በስፍራው ደርሰው እሳቱን ለመቆጣጠር አንድ ሰዓት ያህል እንደፈጀባቸው ተገልጿል።

ባለ ሁለት ፎቅ ህንፃው ሙሉ በሙሉ የወደመ ሲሆን ለእሳቱ መንስዔ የሆነውን ነገር ለመለየት ጥናት እየተደረገ መሆኑም ተነግሯል።

የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር የከተማው ከንቲባ በደረሰው አደጋና ሕይወታቸውን ባጡት ታዳጊዎች የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልፀዋል።