አይ ኤስን ተቀላቅላ የነበረችው እንግሊዛዊ ታዳጊ ዜግነቷን ልትነጠቅ ነው

የፎቶው ባለመብት, PA
በ15 ዓመቷ እስላማዊ ቡድኑን በሶሪያ የተቀላቀለችው ሸሚማ ቤገም የእንግሊዝ ዜግነቷን ልታጣ እንደምትችል ተገለፀ።
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ምንጮች እንዳስታወቁት የ19 ዓመቷ ወጣት የሌላ ሀገር ዜግነት ሊኖራት ስለሚችል የእንግሊዝ ዜግነቷን ልታጣ ትችላለች።
የቤተሰቧ ጠበቃ የሆኑት ታስኒም አኩንጄ በውሳኔው ማዘናቸውን ገልፀው "ያሉትን ህጋዊ መንገዶች ሁሉ እንጠቀማለን" ብለዋል።
ቤገም ለንደንን ለቅቃ የሄደችው በ2015 ሲሆን አሁን ግን መመለስ እንደምትፈልግ መዘገቡ ይታወሳል።
ባለፈው ሳምንት የአይ ኤስ እስላማዊ ቡድን ጠንካራ ግዛት ከነበረው ባጉዝ፣ መጥታ በሶሪያውያ የመጠለያ ጣቢያ ውስጥ የተገኘች ሲሆን በሳምንቱ መጨረሻ ላይም ወንድ ልጅ ተገላግላለች።
በእንግሊዝ የዜግነት ሕግ መሰረት አንድ እንግሊዛዊ ዜግነት ያለው ግለሰብ ዜግነቱን ሊያጣባቸው ከሚችልባቸው ምክንያቶች መካከል የሀገር ውስጥ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ "ለሕብረተሰቡ መልካም ጥቅም ሲባል" ብሎ ሲያምንና በሂደቱ ዜጋው ዜግነት አልባ የማይሆን ከሆነ ነው።
የሀገር ውስጥ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ እንደተናገሩት "ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሀገር ውስጥ ጉዳዮች መስሪያ ቤቱ በግልፅ እንዳስቀመጠው ለሀገሪቱ ዜጎችና እዚህ ለሚኖሩ ግለሰቦች ደህንነት ቅድሚያ ይሰጣል።"
አክለውም በግለሰቦች ጉዳይ አስተያየት እንደማይሰጡ ገልፀው "ያሉት መረጃዎች በሙሉ ከግምት ውስጥ ገብተውና አፅንኦት ተሰጥቶት የሚሰራ" ነው ብለውታል የአንድን ግለሰብ ዜግነት ስረዛ።
በሀገሪቱ የሽብርተኛ ህግ ላይ የሰሩ ግለሰቦች እንደሚሉት ከሆነ የቤገም እናት የባንግላዲሽ ዜግነት ካላት ልጅቷም በባንግላዲሽ ህግ መሰረት ዜግነት ይኖራታል።
የቤገም ቤተሰቦች የባንግላዲሽ ዝርያ ያላቸው ሲሆን ቤገምን ቢቢሲ ስለ ጉዳዩ በጠየቃት ወቅት ግን አንድም ጊዜ ወደ ባንግላዲሽ ሄዳ እንደማታውቅና ፓስፖርትም እንደሌላት ገልፃለች።
ከቤገም የተወለደው ልጅም በህጉ መሰረተ ዜግነቷ ከመፋቁ በፊት ስለተወለደ እንግሊዛዊ ዜግነት ይኖረዋል።