'የተሳመው ከንፈር' ጥቃት ደረሰበት

"የማያዳግም ፍቅር" ተብሎ የተሰየመው ሀውልት በቀለም 'ሚ ቱ' የሚል ተፅፎበት

የፎቶው ባለመብት, Sarasota Police Department

ነገሩ የሆነው የዛሬ 74 ዓመት ነው። አንድ መርከበኛ አንዲትን ኮረዳ ከመንገድ ዳር ሳብ አድርጎ ከንፈሯን ጎረሰው።

ይህ ሲሆን አልፍሬድ አይዠንስታድ የሚባል ዕድለኛ ፎቶ አንሺ ድንገት በቦታው ነበር። ቀጭ፣ ቀጭ፣ ቀጭ አደረገው፤ ካሜራውን።

ያ ፎቶ ሳር ቅጠሉን አነጋገረ። ዓለም ይህንን 'ድንገቴ መሳሳም' ወደደው። ሀውልትም ሠራለት። ስሙንም "የማያዳግም ፍቅር" ሲል ጠራው።

ትናንት ታዲያ በዚያ ፎቶ ላይ የልጅቱን ከንፈር ሲስም የሚየታው የያኔው ጎረምሳ 95 ዓመት 'ሞልቷቸው' ሞቱ።

ዓለም አዘነ። ስለዚያ ቅጽበታዊ ስሞሽም ይበልጥ መነጋገር ያዘ።

ለካንስ አንዳንዶች ያን ሀውልት ሲያዩ ደማቸው ይፈላ ኖሯል። ለካንስ መሳሳሙንም እንደ ጾታዊ ጥቃት ነበር የሚመለከቱት። ሌሊቱን አድብተው ጥቃት አደረሱበት። ሀውልቱ ላይ።

ምነው ቢባሉ ያ 'መርከበኛ የልጅቱን ከንፈር የሳመው አስፈቅዶ ስለመሆኑ ምንም መረጃ የለም' አሉ።

ነሐሴ 14፤ 1945፤ ኒውዮርክ

የ2ኛው የዓለም ጦርነት በአሜሪካ ድል አድራጊነት መጠናቀቁ በተበሰረበት ወቅት ነበር እነዚህ ሁለት ተአምረኛ ከንፈሮች የተገናኙት።

እርግጥ ነው አይተዋወቁም። ተያይተውም ተደባብሰውም አያውቁም፣ ከዚያ በፊት። ያን ዕለት ግን ድንገት ተገናኙ። ያገናኛቸው ደግሞ የጃፓን በጦርነቱ እጅ መስጠት ነው።

የአቶ ጆርጅ ማንዶሳ እና የወይዘሪት ዚመር ፈሬድማን ከንፈሮች ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይኸው እስከዛሬ ዓለምን ጉድ አሰኝተዋል።።

ይህን ቅጽበታዊ ክስተት በፎቶ ካሜራ የቀለበው ዕድለኛ ሰው አልፍሬድ አይዠንስታድ ነው። እሱም "አረ እኔ ድንገት ነው፣ አስቤበትም አይደለም ያነሳኋቸው" ብሏል።

ፎቶው እጅግ ዝነኛና ዓለምን በአውደ ርዕይ ያዳረሰ ሲሆን ላለፉት 74 ዓመታት ዝናውን የነጠቀው የለም።

ይህ ሁሉ የሆነው ነሐሴ 14፣ 1945 ዓ.ም ነበር።

ታዲያ የትናንቱ ልብ የሚሰብረው ዜና በዚያ ፎቶ ላይ ይታይ የነበረው ያ የያኔው መርከበኛ በተወለደ በ95 ዓመቱ ከዚህ ዓለም መለየቱ ነበር።

ጥቃት አድራሾቹ ምን አሉ?

በፍሎሪዳ ሳራሶታ የሚገኘው ይህ ሀውልት "አንኮንዲሽናል ሰሬንደር" የሚል ስም አለው። "ለማይናወጽ ፍቅር እጅ መስጠት" እንበለው? ወይስ "የማያዳግም ፍቅር"?

ይህን ሀውልት ያልታወቁ ሰዎች ሌሊቱን በቀለም አበለሻሽተውታል።

በሀውልቱ ላይ በጎረምሳው መርከበኛ እየተሳመች ያለችው ወይዘሪት ዚመር እግሮቿ ላይ "ሚቱ"(Me too) የሚል ጽሑፍ በቀይ ቀለም ተጽፎባት ታይቷል። ይህም ምናልባት ድርጊቱ በ'አክራሪ ጾተኞች' የተፈጸመ እንደሆነ ጥርጣሬን አሳድሯል።

ፖሊስ የደረሰውን ጥፋት በገንዘብ አንድ ሺህ ዶላር ተምኖታል።

ለብዙዎች የነዚህ ጥንዶች 'ድንገቴ ስሞሽ' በወቅቱ የነበረውን መጠን ያለፈ ደስታና ፈንጠዚያ የሚወክል ነው።

ነገር ግን ክስተቱ በ'ጽንፈኛ ጾታ' ተሟጋቾች ዘንድ የተወደደ አይመስልም። የወቅቱን ፈንጠዚያ ከማሳየቱ ይልቅ ጾታዊ ጥቃትን ነው የሚዘክረው ብለው የሚሟገቱ አልጠፉም።

ይህን እንዲሉ ያስቻላቸው መርከበኛው መንዶሳ የወይዘሪት ፍሬድማንን ስምምነት ሳያገኝ ነው ከንፈሩን ከንፈሯ ላይ ያሳለፈው በሚል ነው።

እርግጥ ነው ከዓመታት በፊት (በ92 ዓመታቸው) የያኔዋ ኮረዳ ወይዘሪት ዚመር ፍሬድማን በሰጠችው (በሰጡት) ቃል "በ1945 ያ መርከበኛ የሳመኝ እኮ በፍቃዴ ሳይሆን እንዲያው ድንገት ደርሶ ጎተት አድርጎ ነበር ከንፈሬን የጎረሰው" ሲሉ የወቅቱን ሁኔታ አስታውሰው ነበር።

ነገር ግን ይህን ቃል ሰጥተው በ2016 ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ ልጃቸው ለኒውዮርክ ታይምስ እንደተናገረው እናቱ የያን ጊዜውን ድንገቴ ስሞሽ ያን ያህልም በአሉታዊ መንፈስ እንደማያዩት ተናግሯል።

የሳሮሳታ ፍሎሪዳ ፖሊስ በሀውልቱ ላይ የደረሰውን ድርጊት በማኅበራዊ ሚዲያ ካሰራጨ ወዲህ በ'ጽንፈኛ ጾተኞች' ላይ ሰፊ ውግዘት መዝነብ ጀምሯል።

"ጸታዊ ጥቃት በጥቅሉ የሚወገዝ ነው። ነገር ግን ይህ ፎቶ ያንን አያሳይም። በጭራሽ ከጥቃት ጋር የሚተሳሰር አይደለም። በእርግጠኝነት የምነግራችሁ ኮረዳዋን የሳሟትና ትናንት የሞቱት ሰው በዚያ ወቅት ድርጊቱን ሲፈጽሙ ጥቃት እየፈጸሙ አልነበረም።" ብላለች አንዲት አስተያየት ሰጪ።

ሌሎች ደግሞ ይህን የአክራሪ ጾተኞችን ድርጊት ጸያፍና መጠን ያለፈ ብለውታል።

"ይህን ያደረጉ ሰዎች ያሳዝናሉ። መርከበኛው በ95 ዓመታቸው ባረፉበት ማግስት ይህ መሆን አልነበረበትም" ብለዋል ሌላ አስተያየት ሰጪ።

ሌሎች በአንጻሩ ሀውልቱ የሴቶችን ጥቃት የሚያንጸባርቅ በመሆኑ የሳራሶታ ከተማ ሀውልቱን እንዲያፈርሰው ጠይቀዋል። ሀውልቱም ስሙ "የማያዳግም ፍቅር" ሳይሆን "የማያዳግም ጥቃት" ነው መባል ያለበት ብለዋል።