ናንሲ ፒሎሲን ሊገድል የነበረው አሜሪካዊ ወታደር

የአሜሪካ ፖሊስ ባልደረባ የሆነው ግለሰብ የሽብር ጥቃት ለማድረስ አቅዶ ያዘጋጃቸው የጦር መሳሪያዎች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካ ድንበር ጠባቂ አባል የሆነው ግለሰብ የሽብር ጥቃት ለማድረስ በማሰብ ተብሎ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ተሰማ።

ይህ የፖሊስ ባልደረባ ክሪስቶፈር ፖል ሐሶን የሚባል ሲሆን መኖሪያ ቤቱ ሲበረበር የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች ስብስብ ተገኝቷል።

ይህ የነጭ የበላይነትን አቀንቃኝ እንደሆነ የሚናገረው የፖሊስ ባልደረባ ጥቃቱን የሚፈፅምባቸውን ታዋቂ ዲሞክራት ፖለቲከኞችን ጨምሮ ሌሎች ግለሰቦችን ለይቶ የጨረሰ መሆኑን አቃቢ ሕግ ተናግሯል።

ግለሰቡ ይህንን ሐሳብ ያገኘው ከኖርዌጂያዊው የጭምላ ግድያ ፈፃሚ አንደርስ ብሬቪክ እንደሆነ ገልጿል።

"ግለሰቡ ንፁሐን ዜጎችን በዚህ ሀገር ከዚህ በፊት እምብዛም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ለመግደል አስቦ ነበር" ያሉት ደግሞ የሕግ ባለሙያው ሮበርት ሁር ናቸው።

አቃቤ ሕግ እንደሚለው ከሆነ በ2017 ጽፎ ባልላከው የኢሜል መልእክት ላይ " በምድር ላይ ያለን የመጨረሻውን ግለሰብ ሳይቀር የምገልበትን መንገድ እያለምኩ ነው። መቅሰፍት የሚያስከትል ነገር በጣም ጥሩ ሳይሆን አይቀርም፤ ነገር ግን እንደ ስፔን ጉንፋን፣ አንትራክስ እና ቦቱሊዝምን እንዴት ማግኘት እችላለሁ? እስካሁን እርግጠኛ ባልሆንም አንድ ነገር እንደማገኝ ግን እርግጠኛ ነኝ። " ሲል አስፍሯል።

የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ግለሰቡ 49 ዓመቱ መሆኑን ጠቅሰው በድንበር ጠባቂ ፖሊስ ውስጥ የሌተናል ማዕረግ ያለው መሆኑን ዘግበዋል።

የድንበር ጠባቂው ቢሮም የሥራ ባልደረባቸው በቁጥጥር ሥር መዋሉን አረጋግጠው ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

15 የጦር መሳሪያዎች፣ 1ሺህ ቦንቦች ከተለያዩ ሕገወጥ ዕጾች ጋር በግለሰቡ መኖሪያ ምድር ቤት ውስጥ ተገኝቷል።

ሊገድላቸው በዕቅድ ውስጥ ከያዛቸው ግለሰቦች መካከል የዲሞክራቲክ ፖርቲ አባሏ ናንሲ ፒሎሲ፣ ቻክ ሹመር እና የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ባልደረቦች ይገኙበታል።