ከቴፒ ግጭት ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪዎች እየታሰሩ ነው

ቴፒ

ማሻና አንድራቻ 12፣ ቴፒና የኪ ላይ ደግሞ 17 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተሰማ። እነዚህ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉት በአካባቢው ለተፈጠረው አለመረጋጋት የተለያየ አስተዋፅኦ አድርገዋል በሚል መሆኑን የዞኑ የኮሙኑኬሽን ባለሙያ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ካለፈው ዓመት ነሐሴ 7 ጀምሮ በሸካ ዞን ውስጥ የሚገኙት ወረዳዎች ማሻ፣ አንድራቻ፣ ቴፒና የኪ ችግር ውስጥ መሆናቸውን የአካባቢው አስተዳደሮችም ሆኑ ነዋሪዎች የሚናገሩት ነው።

በዚህም የተነሳ ከፌደራልና ከክልል መንግሥት የተውጣጡ አካላት ከዞን አስተዳደር ጋር በመሆን ኮማንድ ፖስት ተቋቋሙ አካባቢውን ለማረጋጋት እየሠሩ እንደሆነ የዞኑ ኮሙኑኬሽን ባለሞያ አቶ አስማማው ኃይሉ ይናገራሉ።

በነበረው ብሔር ተኮር ግጭትና አለመረጋጋት 'ከስድስት ሺህ በላይ የተፈናቀሉ ሰዎች በቴፒ ከተማ አዳራሽ ይገኛሉ' የሚሉት ደግሞ በአካባቢው ሰላም ለማምጣት ታስቦ የተቋቋመው ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ መንገሻ አዲስ ናቸው።

የእነዚህን ተፈናቃዮች ጉዳይና ሌሎች የሕግ ጥሰቶችን ለከፍተኛ የመንግሥት አካላት እንዲሁም ለፌደራልና ለክልል መንግሥታት ቢሮዎች አቤት በማለታችን ማዘዣ ወጥቶብን እየታደንን ነው ይላሉ አቶ መንገሻ።

"የዞኑን ሸፍጥ የሚያጋልጡ ሰዎች ፍትኃዊ ባልሆነ መልኩ እየታሰሩ ነው" በማለትም ደረሰ ያለውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ነዋሪነታቸው አዲስ አበባ የሆነውና የአካባቢው ተወላጅ የሆኑት አቶ ስንታየሁ ወዳጆ ለስራ ጠዋት ከሚኖሩበት አካባቢ ወጥተው በሞተራቸው ሲንቀሳቀሱ የአዲስ አበባ ፖሊስ ከሸካ ዞን ከመጡና ማዘዣ ከያዙ የፖሊስ አባላት ጋር በመሆን በቁጥጥር ስር እንዳዋሏቸውም ባለቤታቸው ከድጃ ሰይድ ነግረውናል።

ባለቤታቸው እንደሚናገሩት አቶ ስንታየሁ ኑሯቸውን በአዲስ አበባ ካደረጉ ስምንት ዓመት ተቆጥሯል። ነገር ግን በሸካ ዞን አንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩትን የሕግ ጥሰቶች ለተለያዩ የፌደራል መንግሥት ቢሮዎች አቤቱታ በማስገባት የክልሉን ሰዎች ይረዱ እንደነበር አልሸሸጉም።

"ለቀይ መስቀል ስለተፈናቀሉ ሰዎች ጉዳይ መረጃ በመስጠት፣ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለሚመለከታቸው አካላት በማድረስ የአካባቢውን ተወላጆች ይረዳ ነበር" ሲሉም ተናግረዋል።

አቶ ስንታየሁ የታሰሩት ወንጀሉ ተፈፀመ ከተባለበት ሥፍራ ከ90 ኪሎ ሜትር በላይ ርቆ ነው የሚሉት ወ/ሮ ከድጃ የታሰሩበት ስፍራ ከአዲስ አበባ ደግሞ 900 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ እንደሚገኝና ቤተሰብም ሊጠይቃቸው የሚችልበት ሁኔታ እንደሌለ ባለቤታቸው ለቢቢሲ አስረድተዋል።

አቶ መንገሻ አዲስ እንደነገሩን ከሆነ የሰላም ኮሚቴው ፀሐፊ የሆኑት አቶ ሸዋ ቱቻም ለተለያዩ የመንግሥት አካላት የቴፒን ጉዳይና ያለውን ኢፍትሀዊነት ስለሚያሰሙ በዞኑና በወረዳው የሚፈጠረውን ኢ- ፍትሃዊነት ስለሚቃወሙ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

የሸካ ዞን ኮሙኑኬሽን የሆኑት አቶ አስማማው ኃይሉ እነዚህ ግለሰቦች በዞኑ ውስጥ ችግር በመፍጠር የተያዙ መሆኑን ጠቅሰው የተያዙት መረጃ ተሰባስቦባቸው ጥፋት መሥራታቸው ተረጋግጦ ነው ይላሉ።

በዞኑ የተነሳው የመዋቅር ጥያቄ መሆኑን ያሰታወሱት አቶ አስማማው "የመዋቅር ጥያቄ የሚፈታው የመንግሥትን መዋቀር ተከትሎ ነው" በማለት፣ ንብረት እየወደመ፤ ብሔር ተኮር ጥቃት እያደረሱ፤ የሰው ሕይወት እየጠፋ የመዋቅር ጥያቄ የለም የሚለው የኮማንድ ፖስቱ ግምገማ እንደሆነ አብራርተዋል።

"እነዚህ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉት ማስረጃ ተገኝቶባቸው፤ ምስክር ተቆጥሮባቸው ነው" የሚሉት አቶ አስማማው እስካሁን ድረስ 29 ሰዎች በሕግ ጥላ ሥር ሆነው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በቴፒ ከተማ ጥር 22/2011 ዓ.ም በተነሳ ግጭት ሰባት ሰዎች መሞታቸውን የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ የሽዋስ አለሙ ለቢቢሲ መግለፃቸው ይታወሳል።

በወቅቱ በግጭቱ 100 የሚጠጉ ቤቶች ሲቃጠሉ፤ 1500 ሰዎችም ከቀያቸው ተፈናቅለው ነበር። በአጠቃላይ በዞኑ ለሚገኙ ተፈናቃዮቹ እየተደረገ ስላለው ድጋፍ ለማወቅ ያደረግነው ጥረት በጉዳዮ ላይ ምላሽ የሚሰጠን አካል ባለማግኘታችን አልተሳካም።