ትራምፕ አይኤስን ተቀላቅላ የነበረችውን አሜሪካዊት አላስገባም አሉ

ሆዳ ሙታናና ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ዶናልድ ትራምፕ አይኤስን ተቀላቅላ የነበረችውን አሜሪካዊት ተመልሳ ሀገሯን መርገጥ እንደማትችል ተናገሩ። በትዊተር ገፃቸው እንዳስነበቡት፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማይክል ፖምፒዮ፣ ሆዳ ሙታና የተባለችውን አሜሪካዊት ሀገሯ ተመልሳ እንዳትገባ ትእዛዝ አስተላልፈዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው የ24 አመቷ ወጣት አሜሪካዊት እንዳልሆነች እና አሜሪካም እንደማትገባ ቀድመው ተናግረው ነበር።

ቤተሰቦቿ እና ጠበቃዋ ግን ወጣቷ አሜሪካዊት እንደሆነች ይናገራሉ።

ሆዳ ሙታና ቤተሰቦቿን ወደ ቱርክ ሃገር ለከፍተኛ ትምህርት እንደምትሄድ ነግራ አይኤስን ልትቀላቀል ወደ ሶሪያ ያቀናችው በ20 አመቷ ነበር።

ሁኔታው ዜግነቷን ከተነጠቀችው የእንግሊዝ ተወላጇ ሸሚማ ቤገም ጋር ተመሳሳይነት አለው።

በቅርቡ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በመጨረሻው ከአይኤስ ጋር በተደረገው ውጊያ የተማረኩትን፣ እንግሊዝን እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት እንዲወስዷቸው እና ለፍርድ እንዲያቀርቧቸዉ ተናግረው ነበር።

የሆዳ ሙታና ቤተሰብ ጠበቃ፣ ሀሰን ሺብሊ፣ ትራምፕ የአውሮፓ ሀገራትን ዜጎቻቸውን መልሰው እንዲወስዱ ተናግረው "በአሜሪካ ዜጎች ላይ ግን ለመቀለድ እየሞከሩ ነው" ሲሉ ኮንነዋል።

አክለውም "የትራምፕ አስተዳደር ዜጎችን በተሳሳተ መንገድ ዜግነታቸውን ለመንጠቅ እየሞከረ ነው" በማለት ለኤቢሲ ኒውስ ተናግረዋል።

ሆዳ ሙታና ህጋዊ የሆነ የአሜሪካ ፓስፖርት ያላት ዜጋ ስትሆን የተወለደችው በኒው ጀርዚ እኤአ በ1994 ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP

ጠበቃዋ ወጣቷ ፍትሀዊ የሆነ የፍርድ ስርዓት እንደምትፈልግና እስርም ከተፈረደባት ለመቀበል ዝግጁ እንደሆነች ተናግረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፖፒዮ ግን "ወጣቷ ህጋዊ የሆነ ፓስፖርትም ሆነ ፓስፖርት የማግኘት መብትም የላትም" ብለዋል።

"ሆዳ ሙታና አሜሪካዊት አይደለችም፤ ወደ አሜሪካም አትገባም" በማለት ጨምረው አቋማቸዉን ገልፀዋል።

ሆዳ ሙታና የአሜሪካ ፓሰፖርት ወደ ቱርክ ከመሄዷ በፊት አመልክታ እንደተሰጣት ለኒው ዮርክ ታይምስ ተናግራለች። ሶሪያ ከደረሰችም በኋላ ከሌሎች ሶስት ሴቶች ጋር የአሜሪካን ጨምሮ ሌሎች የምዕራብ ሀገራትን ፓስፖርቶች ሲያቃጥሉ በትዊተር ገፅዋ ላይ ምስል ለቅቃ ነበር።

አስከትሎም የማህበራዊ ሚዲያ ገፆችዋ ላይ የእስላማዊ ታጣቂዎች አሜሪካውያንን እንዲገድሉ ገፋፍታለች። .

ተንታኞች እንደሚሉት የአሜሪካ መንግስት መልስ አባትዋ የየመን ዲፕሎማት መሆኑ ላይ አመዝኗል። በአሜሪካ ከውጪ ሀገር ዲፕሎማቶች የሚወለዱ ልጆች ወዲያው የአሜሪካ ዜግነት አይሰጣቸውም ምክንያቱ ደግሞ በአሜሪካ ህግ ስር ስላልሆኑ ነው።

ሆኖም ግን ጠበቃዋ ሁዳ ሙታና ስትወለድ አባትዋ የዲፕሎማትነት ሥራቸውን አቁመው እንደነበር ይናገራል።

የ18 ወር ወንድ ልጅ ያላት ሆዳ ሙታና አይኤስን መቀላቀልዋ እንደሚቆጫት እና በማህበራዊ ሚዲያ የእስላማዊ ቡድኑን እና አላማውን ለማስተዋወቅዋ ይቅርታ ጠይቃለች።

ሆዳ ከኤቢሲ ኒውስ ጋር ባደረገችው ቆይታ " ምኞቴ ይህን ድርጊቴን ሙሉ ለሙሉ መሰረዝ ብችል የሚል ነው። ይፀፅተኛል። አሜሪካ እንደ አደጋ እንደማታየኝ ተስፋ አደርጋለሁ። እኔ እንደማንኛውም ሰው አንዴ የተሳሳትኩ ነኝ። ዳግም እንደማልሳሳት ተስፋ አደርጋለሁ።"

ሆዳ ባሁኑ ወቅት በሰሜን ሶሪያ፣ በኩርዲሽ ሀይሎች ተማርካ በስራቸው በሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ትገኛለች።