ሦስት ጊዜ ከሞት ቅጣት ነፍሱ የተረፈችው ጎልማሳ

ካውላ ከእናቱ ጋር

ባይሶን ካውላ 'ሞት እምቢ' ነው። አንዳንዱ ትረፍ ሲለው የመታነቂያው ገመድ ይበጠስበታል። አንዳንዱ ትረፍ ሲለው የገዳዩ ሽጉጥ ጥይት ይነክሳል። እንደ ባይሶን ካውላ ዓይነቱ ደግሞ አንቆ ገዳዩ ደግሞት ከሞት ይተርፋል።

የነ ካውላ ገዳይ ሞት የተፈረደባቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር ይዞ አንድ በአንድ እያነቀ ከዚህ ምድር ያሰናብታል። ልክ ባይሶን ካውላ ጋ ሲደርስ ይደክመወና ያርፋል። 'በቃ ሌላ ጊዜ አንቃችኋለሁ፤ ሂዱ' ይላቸዋል።

ይህ የተከሰተው አንድ ጊዜ ቢሆን አይገርምም። ይህ የሆነው ሦስት ጊዜ ነው።

አሁን አገሩ ማላዊ አንቆ መግደልን በሕግ ከልክላለች።

ትረፊ ያላት ነፍስ

ባውሰን ካውሎን ለእስር የዳረጉት ቀናተኛ ጎረቤቶቹ ናቸው። ሰው ገድለኻል ተብሎ ተሰከሰሰ። የገደለ ይገደል ነበር፤ ያን ጊዜ። ዘመኑ 1992 ነው፤ እንደ ፈረንጆቹ ቀን አቆጣጠር።

ማላዊ ተወልዶ ያደገው ባይሶን ካውላ ደቡብ አፍሪካ ነዳጅ ማደያ ሠርቶ ያጠራቀማትን ጥሪት ይዞ ወደ አገሩ ተመለሰ። መሬት ገዝቶ አምስት ሰዎችን ቀጥሮ ፍራፍሬ፣ ስንዴና በቆሎ ማምረት ጀመረ።

"ከዚህ በኋላ ነበር ሕይወቴ ምስቅልቅል ውስጥ የገባችው"ይላል ካውላ። ከዚህ በኋላ የሆነውን አሳዛኝ ታሪክ እንዲህ ይተርክልናል።

የሞት ፍርድን እንደመጠበቅ የሚያስጨንቅ ምን ነገር አለ?

"ጎሬቤቶቼ አንዱ ሠራተኛዬ ላይ ጥቃት አደረሱበት። ያለ ረዳት መንቀሳቀስ ሁሉ አቅቶት ነበር። ሽንት ቤት እንኳ በኔ እርዳታ ነበር የሚንቀሳቀሰው። አንድ ቀን ታዲያ ከባድ ዝናብ ጥሎ ነበርና ጭቃ አዳልጦኝ ወደቅኩ። ስወድቅ ታዲያ እሱም እኔን ተደግፎ ነበረና አደገኛ አወዳደቅ ወደቀና ሆስፒታል ገባ። የቀን ነገር ኾኖ በዚያው ሕይወቱ አለፈች። እኔ ያኔ 40 ዓመቴ ነበር።

በጭራሽ ባላሰብኩት ሁኔታ ሰው በመግደል ተከሰስኩ።

እነዚሁ ክፉ ጎረቤቶቼ በሐሰት መሰከሩብኝና ፍርድ ቤት ጥፋተኛ አለኝ። ሰው ለገደለ ወዲያው ሞት ነበር ፍርዱ።

እናቴ ሉሲ ፍርድ ቤቱ ሞት እንደወሰነብኝ ስትሰማ ከሐዘኗ ብዛት እንባዋ ደረቀ።

በዚህ ወቅት ማላዊ በአምባገነኑ ሃስቲንግስ ባንዳ ሥር ነበረች። በቃ አቤት የማይባልበት ዘመን።

የሞት ቅጣቴ ተፈጻሚ እንዲሆን ወረፋ መጠበቅ ነበረብኝ። አንቆ መግደያ ማሽኑን የሚያንቀሳቅሰው አንድ ሰው ነበር።

ሞትን በወረፋ መጠበቅ እጅግ ከባድ ነገር ነው።

ከዕለታት አንድ ቀን ወረፋህ ደርሷል ተባልኩ። ወደ መታነቂያው ስሄድ የሞትኩ ያህል ደንዝዤ ነበር።

የሚገርመው በዚያ ዘመን ሁሉንም ፍርደኛ አንቆ የሚገድል ሰው ነበር። ደቡብ አፍሪካም ሌሎች አገሮችም እየሄደ እዚህ ማላዊም እየመጣ ይህንን ሥራ ለመንግሥት ይሠራል። በዚያ ዘመን እሱ ነበር የተዋጣለት አንቆ ገዳይ። ማላዊ የሚመጣው ታዲያ በሁለት በሦስት ወር አንድ ጊዜ ነበር።

ከ21 ፍርደኞች መካከል ስሜ እንዳለና በዚያ ቀን ልገደል እንደሆነ ተነገረኝ። ልክ ከቀኑ ሰባት ሰዓት የኔ ተራ እንደሆነና እንድዘጋጅ ተነገረኝ። በመኾኑም መጸለይም ተፈቀደልኝ።

7፡00 ሰዓት የተባልኩ እስከ ዘጠኝ ሰዓት አስጠበቁኝ። እውነት እውነት እላችኋለሁ ሞትን መጠበቅ ከባድ ነው። ልክ ዘጠኝ ሰዓት ሲል አናቂያችን [አንቆ ገዳያችን] ሥራ አቆመ። ሦስት የሞት ፍርደኞች ሌላ ቀን እንድንመለስ ተነገረን።

የመግደያ ማሽኑን እሱ ብቻ ነው ማንቀሳቀስ የሚችለው ይባል ነበር።

ያን ቀን "በቂ ሰው ገድያለሁ፤ ለዛሬ ይበቃል በሚቀጥለው ወር እንቀጥላለን" አለና ሄደ።

በሚቀጥሉት ጊዜያትም እንዲሁ ሆነ። የአጋጣሚ ወይም የዕድል ጉዳይ ኾኖ አንቆ ገዳያችን እየደከመው ወይም እየሰለችው በሚቀጥለው እመለሳለሁ እያለ የመሞቻችንን ቀን አራዘመው።

ይህ የሞት ቅጣት መዘግየት በብዙዎች እንደ ዕድለኛ ያስቆጥረኝ ይሆናል። ነገር ግን እጅግ የሚያሰቃይ ነገር ነው። በዚህም ምክንያት ሁለት ጊዜ ራሴን ለማጥፋት ሞክሬ ከሸፈብኝ።

ከሞት አፍ መልስ

እንዲህ እንዲህ እያለ በማላዊ የመንግሥት ለውጥ ተካሄደ። በዚያው የሞት ፍርደኞች ጉዳይ ቀስ በቀስ ተዘነጋ። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ግን የሞት ፍርድ ይሰጣል። ኾኖም ላለፉት 25 ዓመታት ተፈጻሚ ኾኖ አያውቅም። ፕሬዝዳንቱም በሞት ፍርደኛ ላይ አይፈርሙም። ዛሬም ድረስ የሞት ፍርደኞች አሉ፤ መንግሥት መጥቶ በገዳይ ማሽን እንዲያስቀምጣቸው የሚጠባበቁ። ኾኖም ግን ተፈጻሚ ኾኖ አያውቅም። የብዙ ሞት ፍርደኞች ውሳኔ ወደ ዕድሜ ልክ ይቀየራል።

ይኸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እኔም እስር ቤት ነበር የቆየሁት። እርግጥ ነው ከነበርኩበት ወደ ዞምባ ማእከላዊ እስር ቤት ተዘዋውሬያለሁ። እስር ቤት ውስጥ ትምህርት ላይ አተኩራለሁ። በእስር ቤት ውስጥ አስተማሪ ሆኜ አገለግላለሁ።

ሩብ ምዕተ ዓመት እስር ቤት ካሳለፍኩ በኋላ ድንገት በ2007 ዓ.ም አንድ አስገራሚ ነገር ተፈጠረ።

የእንጀራ ልጁን የገደለ አንድ አደገኛ እጽ ተጠቃሚ ወደ እስር ቤት መጣ። ነገር ግን ድርጊቱን የፈጸመው የአእምሮ በሽተኛ ስለነበረ እንደሆነ ተከራከረ። በዚህም የሞት ፍርደኛ መሆን እንደሌለበት ፍርድ ቤት በይግባኝ ተሟገተ። ፍርድ ቤቱ በሚገርም ሆኔታ ልክ ነህ አለው። በዚህ አጋጣሚ የሞት ፍርድ እንዲቀለበስ ሐሳብ ቀረበ።

ከ170 የሞት ፍርደኞች ውሰጥ 139ኞቻችን ጉዳያችን በድጋሚ እንዲታይ ተባለ። ፍርድ ቤት ትፈለጋለህ ስባል እንደተለመደው በአንድ ወንጀለኛ መስክር ሊሉኝ ነው ብዬ ነበር።

ዳኛው ያሉትን ነገር ማብላላት እንኳን አልቻልኩም። ነጻ ሰው ነህ ነው የሚሉኝ። እስር ቤቱን ለቀህ ውጣ ነው የሚሉኝ።

ሕጻን እያሉ የማውቃቸው 6ቱ ልጆቼ ከእስር ስወጣ ትልልቅ ልጆች ኾነው ነበር። ባለቤቴ ግን እኔ ሞትን በምጠባበቅበት ወቅት ሞታለች።

አሁን ነጻ ሰው ነኝ። ብቻዬን ነው የምኖረው።

እስር ቤት እየተመላለሰች ያን ሁሉ የእስር ዓመት ስትጠይቀኝ የነበረችው እናቴን እየተንከባከብኩ እኖራለሁ። 80 ዓመቷ ነው። እናቴ የመጀመርያ ልጇ ነኝ። በእኔ ምክንያት ተንከራትታለች። በዚያ ሁሉ የሞት ፍርደኝነት ዘመን መከራን ብቻዋን ተቋቁማለች። አሁን ወደ እርሻ እንድትሄድ አልፈልግም። ቤት ቁጭ አድርጌ እንከባከባታለሁ።

ቀጣዩ አላማዬ የሸክላ ቤት ለውዷ እናቴ መቀለስ ነው።