አር ኬሊ ሴቶችን አስክሮ በመድፈር ውንጀላ ቀረበበት

አር ኬሊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካዊው ድምፃዊ አር ኬሊ ለብዙዎቻችን ጆሮም ሆነ ዐይን እንግዳ አይደለም። ይህ የ52 ዓመቱ ድምፃዊ በድንቅ የሙዚቃ ችሎታውና ሙዚቃው የምናውቀው ያህልም በጾታዊ ትንኮሳም ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ነው።

ከዚህ በፊት አንዲት የ20 ዓመት ወጣት በግድ መጠጥ እንድትጠጣ አድርጎ ሩካቤ ሥጋ በመፈፀም አባላዘር በሽታ እንዳስያዛት በመናገር ክስ መሥርታ ነበር።

አር ኬሊ የ27 ዓመት ወጣት ሳለ ነበር የ15 ዓመቷን ማሪስ አሊያህን በድብቅ ያገባው። ይህም የፍርድ ቤትና የመገናኛ ብዙኃን እሰጣገባ ውስጥ ከትቶት ብዙ ተባብሎበታል።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ነበር የተለያዩ ሴቶች ችሎት ፊትም ሆነ መገናኛ ብዙኃን ጋር እየቀረቡ፣ ተደፍረናል፤ ተተንኩሰናል፤ እሱ ያላደረገን ነገር የለም በማለት አቤቱታቸውን ማሰማት የጀመሩት።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዛሬም ሁለት ሴቶች እኛም በአር ኬሊ ጥቃት ደርሶብናል ሲሉ ድምፃቸውን አሰምተዋል።

እነዚህ ሴቶች ሮሼል ዋሺንግተን እና ላትሬሳ ስካፍ ይባላሉ። በ1990ዎቹ በባልቲሞር በነበረ የሙዚቃ ድግስ ላይ ተገኝተው አር ኬሊን ሲታደሙ የኬሊ ጠባቂዎቹ ዐይን ውስጥ ይገባሉ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በወቅቱ አፍላ ጎረምሳ የነበሩትን እነዚህን ሴቶች የኬሊ አጃቢዎች ከሙዚቃ ድግሱ መካከል አውጥተው ከወሰዷቸው በኋላ መጠጥና አደንዛዣ ዕፅ እንደተሰጣቸው ገልፀዋል።። ይህ የሆነው በ1995 ወይንም በ1996 እንደሆነ ያስታውሳሉ።

የዛሬዎቹ ከሳሾች በወቅቱ ስለነበረው ሲያስታውሱ ኮኬይን፣ ማሪዋና እና መጠጥ ቀርቦላቸው በድምፃዊው መኝታ ክፍል እንዲቆዩ ተደረገ።

በመኝታ ክፍሉ እያሉ 'ድምፃዊው እየመጣ እንደሆነ' ተነግሯቸው ልብሳቸውን አውልቀው እንዲጠብቁት ታዘዙ። ድምፃዊው ሲመጣ የመራቢያ አካሉ ለወሲብ ዝግጁ ኾኖ ይታይ ነበር ብለዋል። ከዚያም ለ'ሦስትዮሽ-ወሲብ' ጋበዛቸው።

ወይዘሪት ዋሺንግተን አሻፈረኝ በማለት ወደመታጠቢያ ክፍል ስታመራ ወይዘሪት ስካፍ ግን አብራው ተኛች።

የወቅቱን ሁኔታ ስታስረዳም "በመጠጣቴና አደንዛዥ ዕፅ በመውሰዴ የምደራደርበት አቅም አልነበረኝም" ብላለች።

አሁን ጉዳዩን ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ ለማድረግ የፈለገችው ሌሎች እንደ እርሷ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች በደላቸውን ማሰማት በመጀመራቸው ነው።

የእነዚህን ሁለት ሴቶች ጉዳይ እንዲህ ዓይነት ጥፋቶች የፍትህ ፀሐይ እንዲሞቃቸውና ተገቢውን ፍትህ እንዲያገኙ በማድረግ የሚታወቁት ስመጥር ጠበቃ ግሎሪያ አልሬድ ይዘውታል።

አር ኬሊ ሙሉ ስሙ ሮበርት ሲልቨስተር ኬሊ ሲሆን ላለፉት 20 ዓመታት በወሲባዊ ጥቃትና ትንኮሳ የመገናኛ ብዙኃን የወሬ ማሟሻ ሆኖ ኖሯል።

በቅርቡም በአሜሪካ አንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ በእርሱ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ላይ በሠራው ዘጋቢ ፊልም ያደረሰውን አካላዊ እና የስሜት ስብራት በጥልቀት አሳይቷል። ድምፃዊው በዕድሜ ለጋ ከሆኑ ሴቶች ጋር ይቃበጥ እንደነበር የሚገልፁ የተለያዩ ክሶችም ቀርበውበታል።

የአር ኬሊ ጠበቆች ግን እንደተለመደው አጣጥለውታል።

ድምፃዊው ራሱ የስምንት ዓመት ልጅ እያለ በዕድሜ የምትበልጠው ሴት በተደጋጋሚ ወሲባዊ ግንኙነት እንደፈፀመችበትና እንዳይናገር ታስፈራራው እንደነበር የሕይወት ታሪኩን ባስነበበት መጽሐፍ ላይ አስፍሯል።