ሳዑዲ ልዕልቷን የአሜሪካ አምባሳደር አደረገች

ልዕልት ሪማ ቢንት ባንዳር አል-ሳዑድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ልዕልት ሪማ ቢንት ባንዳር አል-ሳዑድ

ሳዑዲ አረቢያ፤ ልዕልት ሪማ ቢንት ባንዳር አል-ሳዑድን በአሜሪካ የሳዑዲ አምባሳደር አድርጋ ሾመች። ልዕልቷ መሰል ሥልጣን የተሰጣት የመጀመሪያ ሴት ናት።

ልዕልቷ ከልጅነት ህይወቷ ከፊሉን ያሳለፈችው በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ሲሆን፤ ለአምባሳደርነት መመረጧ ይፋ የሆነው ቅዳሜ እለት ነበር።

የጋዜጠኛው ጀማል ኻሾግጂን ግድያ ተከትሎ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሳዑዲ ላይ ጣቱን በቀሰረበት ወቅት በአምባሳደርነት መሾም የልዕልቲቷን የሥራ ኃላፊነት ከባድ ያደርገዋል እየተባለ ነው።

ሳዑዲ በኻሾግጂ ግድያ ዙሪያ እርስ በእርስ የሚጣረስ መረጃ ስታወጣ መቆየቷ ይታወሳል።

ሳዑዲ፤ በኻሾግጂ ግድያ አልጋ ወራሽ ልዑል መሀመድ ቢን ሳልማን እጃቸው የለበትም ብትልም የአሜሪካ የስለላ ተቋም ነገሩ አልተዋጠለትም።

የአሜሪካ ሕግ አውጪዎች ኋይት ሀውስ ነገሩን እንዲያጣራ ጫና ለማሳደር ሞክረዋል።

የኮንግረሱ አባላት የኒውክሌርና የየመን ጦርነት ገዳይን ጨምሮ በአሜሪካና በሳዑዲ መካካል ያለውን ግንኙነት መርምረዋል።

ልዕልቷ ሥልጣኑን የምትረከበው ከልዑል አልጋ ወራሹ ታናሽ ወንድም ልዑል ካሊድ ቢን ሳልማን ነው።

የልዕልቷ አባት ባንዳር ቢን ሱልጣን አል-ሳዑድ እንደ አውሮፓውያኑ ከ1983 እስከ 2005 ድረስ በአሜሪካ የሳዑዲ አምባሳድር ነበሩ።

በአባቷ ስልጣን ምክንያት አሜሪካ ያደገችው ልዕልቷ፤ ከዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ በሙዝየም ጥናት የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች።

ልዕልት ሪማ ቢንት ባንዳር አል-ሳዑድን በ2005 ከአሜሪካ ወደ ሪያድ ተመልሳ በመንግሥትና በግል ተቋሞች ውስጥም አገልግላለች።

በበርካታ የቢዝነስ ተቋሞችን በሀላፊነት የምትሠራው ልዕልቷ፤ ለሴቶች እኩልነት በመከራከር ትታወቃለች። ሳዑዲ ሴቶችን በመጨቆን ከሚተቹ ሀገሮች አንዷ መሆኗ ይታወቃል።

ልዕልቲቷ በቅርቡ የሳዑዲ የስፖርት ባለሥልጣን ነበረች። ሥራዋ በዋነኛነት ሴቶች በስፖርት ዘርፍ ያላቸውን እንቅስቃሴ ለማሳደግ ያለመ ነው። ልዕልቷ ስለ ጡት ካንሰር ግንዛቤ ለመፍጠር ንቅናቄ በማድረግም ትታወቃለች።