ሴት ተመራቂዎች ለምን ሥራ አያገኙም?

የመመረቂያ ባርኔጣ

የፎቶው ባለመብት, Christopher Furlong

መርየም አሊ ተወልዳ ያደረችው ጎንደር፣ ደባርቅ ውስጥ ነው። የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች የሥነ ዜጋ ትምህርት ውጤቷ ከፍተኛ ስለነበረ ዩኒቨርስቲ ገብታም ያጠናችው ሥነ ዜጋ እና ሥነ ምግባር ትምህርት ነው።

በ2009 ዓ. ም. ስትመረቅ አላማዋ በሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች ላይ አተኩሮ በሚሠራ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ መሥራት ነበር። ሆኖም ከተመረቀችበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ሥራ ማግኘት አልቻለችም።

"አሁን የሚያስፈልገኝን ነገር ሁሉ የሚሰጡኝ ቤተሰቦቼ ናቸው። ቤት ውስጥ እንጀራ እጋግራለሁ፤ ልብስ አጥባለሁ።"

እንደ መርየም ሁሉ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋሞች ከተመረቁ በኋላ ሥራ ለማግኘት የሚቸገሩ ሴቶች በርካታ ናቸው።

ለዓመታት ሴቶች እኩል የትምህርት እድል ማግኘት ሳይችሉ ቆይተዋል። አሁን ግን ችግሩ ትምህርት አለማግኘት ብቻ ሳይሆን ቢማሩም ከተመረቁ በኋላ ሥራ ለመያዝ መቸገርን ያካትታል።

መርየም እንደምትለው ሴት ተመራቂዎች ሥራ የማግኘት እድላቸውን ከሚያጠቡባቸው ምክንያቶች መካከል በቂ የሥራ እድል አለማግኘት፣ የሥራ ቦታ ርቀትና የቤተሰብ ጫና ይጠቀሳሉ።

ሴቶች ከሚኖሩበት አካባቢ በራቀ ቦታ ሥራ ሲያገኙ "አንቺ ሴት ስለሆንሽ አትሄጂም" ይባላሉ ትላለች።

የሥራ እድል በብዛት እንደማይገኝ የምትገልጸው መርየም፤ "ቢገኝም ለአንድ ሥራ ብዙ ሰው ስለሚወዳደር አስቸጋሪ ነው" ትላለች። አንዳንድ ተመራቂዎች ቢያንስ እንኳን በሰው በሰው ሥራ የሚያገኙበት እድል እንዳላቸው ታክላለች።

መርየም እንደምትለው ብዙ ጊዜ የሥራ ማስታወቂያ ሲመጣ አዳዲስ ተመራቂዎችን ታሳቢ አድርጎ አይደለም። የዲፕሎማ ምሩቅ የሆኑ ግለሰቦች በርቀት ትምህርት ዲግሪ ከያዙ በኋላ ባላቸው የሥራ ልምድ በቀላሉ ሥራ ሲያገኙም አይታለች።

እሷ ተመርቃ ሥራ ሳታገኝ ከሷ በኋላ ዩኒቨርስቲ የገቡ ተማሪዎች ተመርቀው ሲወጡ ስታይ ሥራ ያለማግኘቷ ጉዳይ የበለጠ እንደሚያስጨንቃት ትናገራለች።

ከሷ ጋር የተመረቁ ጓደኞቿ በተማሩበት ዘርፍ ሥራ እስከሚያገኙ ድረስ ሌሎች አማራጮች እየሞከሩ ቢሆንም እሷ ግን በሀይማኖት ምክንያት ልትሠራቸው የማትፈቅዳቸው ሥራዎች አሉ።

"አማራጭ ስለሌለ ጓደኞቼ ሆቴል ላይ ይቀጠራሉ። እኔ ግን ሙስሊም ስለሆንኩ ሆቴል ተቀጥሬ አልሠራም።"

ከጓደኞቿ መካከል የቀን ሥራ የሚሠሩ፣ የጀበና ቡና የሚሸጡም ይገኙበታል።

የያለምዘርፍ አሰፋ ተሞክሮም ከመርየም የተለየ አይደለም።

ያለምዘርፍ ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የተመረቀችው አምና ነበር። በራስ አለመተማመን፣ ከመረጃ መራቅና ቶሎ ተስፋ መቁረጥ የሴት ተመራቂዎች ፈተናዎች ናቸው ትላለች።

ቤተሰብ ልጆቹን እንደምንም ብሎ ካስተማረ በኋላ ሥራ ይይዛሉ ብሎ ቢጠብቅም እውነታው ከዛ የራቀ ነው ስትል ትገልጻለች። ተመርቆ ሥራ አለማግኘት ከባድ የሥነ ልቦና ጫና እንደሚያሳድር ትናገራለች።

"ማህበረሰቡ በበጎ አይመለከትሽም። ቤተሰብም ይሰለቻል። እንደተመረቅን ሰሞን ያለው ደማቅ አቀባበልም ይጠፋል።"

ያለምዘውድ እንደምትለው ከተማ አካባቢ የሚኖሩ ሴቶች ገጠር ከሚኖሩ ሴቶች በተሻለ ሥራ የማግኘት እድል አላቸው።

"ከተማ አካባቢ አንድ ሰው የሚፈልገውን ሥራ ቶሎ እንደማያገኝ ይረዳሉ። ገጠር ግን ተመርቀሽ ስራ ሳታገኚ ስትቀሪ 'ውጤቷ ዝቅ ስላለ ነው' ወይም 'ስለማታውቅ ነው' ብለው ያስባሉ።"

ተመርቆ ሥራ ማጣት ተመራቂዎችን ብቻ ያስጨነቀ ጉዳይ አይደለም። የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎችንም ተስፋ ያስቆረጠ ይመስላል።

"ተማሪዎች ተመርቀው ሥራ ሲያጡ ስታይ፣ በተለይ ደግሞ አንቺ እያጠናሽ ባለሽው የትምህርት ዘርፍ ተመርቀው ከወጡት መካከል ሥራ ያልያዙት ቁጥር ሲበዛ ለመማር አያበረታታም። ስትማሪ ጊዜ እያጠፋሽ መስሎ ይሰማሻል" ስትል የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ የሆነችው ሄራን መብራቱ ትናገራለች።

"ወንድ ተማሪዎች 'እንደምንም ተፍ ተፍ ብዬ ሥራ አገኛለው' ይላሉ፤ በተቃራኒው ሥራ ማጣትን ማሰብ ሴት ተማሪዎች ላይ ትልቅ ጫና ያሳድርባቸዋል፤ ወደ ኋላም ይጎትታቸዋል" ትላለች።

ተመራቂዎች ሥራ ለማፈላለግ ከሚጠቀሙበት መንገድ አንዱ የተለያዩ የሥራ ማስታወቂያዎች የሚወጡባቸው ጋዜጣዎችና ድረ ገጾችን መመልከት ነው።

በርካቶች ሥራ ከሚያፈላልጉባቸው ድረ ገጾች አንዱ የሆነው ኢትዮ ጆብስ ሥራ አስኪያጅ ህሊና ለገሰ፣ ለሥራ ቅጥር ምልመላ ሲያደርጉ ጾታን ከግምት ውስጥ እንደማያስገቡ ትናገራለች። ሆኖም ብዙ ሴት ተመራቂዎች ለሥራ ሲያመለክቱ አይስተዋልም።

"ማንኛውም የሥራ ማስታወቂያ ሲወጣ ወደ 70 በመቶ የሚሆኑት አመልካቾች ወንዶች ናቸው። ሴት ተመራቂዎች መረጃ እያገኙም ወይም ሥራ የት እንዳለ አያውቁም ማለት ነው" ትላለች።

ህሊና እንደምትለው ሥራ ሊገኝባቸው የሚችሉ አማራጮችን ጠንቅቆ አለማወቅ እንዲሁም በቃለ መጠይቅ ወቅት ድፍረት በማጣት ተገቢ መልስ አለመስጠት ለሴት ተመራቂዎች ፈተና ሆነዋል።

ተማሪዎች ሥራ ላላገኝ እችላለሁ ብለው መስጋታቸው ክህሎታቸውን የሚያሳደጉ ስልጠናዎች ከመውሰድ እንደሚያግዳቸውም ህሊና ትናገራለች።

በሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚንስቴር ዳይሬክተር ወ/ሮ ኤልሳቤጥ ገሰሰ እንደሚሉት ሴት ተማሪዎች ከመመረቃቸው በፊት ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ የተለያዩ ስልጠናዎች እንዲወስዱ ይደጋል።

ዩኒቨርስቲ ሳሉ ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ ሴቶች እዛው ዩኒቨርስቲ እያስተማሩ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንዲማሩ መደረጉ ሌላው ድጋፍ ነው ይላሉ።

በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሥራ ማስታወቂያ ወጥቶ ውድድር ሲደረግ ለሴቶች የሦስት ነጥብ አብላጫ ይሰጣል።

በሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚንስቴር የተሳትፎና ንቅናቄ ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ታደሰ በበኩላቸው ሴት ተመራቂዎች ሥራ ለማግኘት ከሚቸገሩባቸው ምክንያቶች ዋነኛው ህብረተሰቡ ለሴቶች ያለው የተዛባ አመለካከት ነው ይላሉ።

ሌላው ምክንያት ሴቶች ከተወሰነ ደረጃ በላይ በትምህርት አለመግፋታቸው ነው። አቶ ስለሺ እንደሚሉት በሥራው ዓለም የሚታዩ ሴቶች ቁጥር ዝቅ ያለበት ምክንያት በትምህርት የሚገፉበት እድል አለመኖሩ ነው።