"ሲጀመርም መጠለያው መንግሥትና ህዝብ ሳይግባቡ የተሰራ ነው" የላሊበላ ከተማ ከንቲባ

የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት

የፎቶው ባለመብት, J. Countess

ለላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት የተሰራው የአደጋ መከላከያ መጠለያ ራሱ ለቅርሱ አደጋ ሆኗል በማለት የከተማዋ ነዋሪዎች በተለያየ ጊዜ ቅሬታቸውን ለመንግሥት አቅርበዋል። በጥቅምት ወር 2011 ዓ.ምም ከከተማዋ የተወጣጣ ኮሚቴ ም/ጠ/ሚ/ር ደመቀ መኮንን ድረስ በመሄድ ይህንኑ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

በወቅቱ ም/ጠቅላይ ሚንስትሩ ጥቅምት ወር ሳያልቅ የገቢ ማሰባሰቢያ መድረክ ተዘጋጅቶ መጠለያውን ለማንሳትና ጥገናውን ለማከናወን የሚጠበቀውን 300 ሚሊዮን ብር እንደሚሰበሰብ ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል።

በሳምንታት ልዩነት ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ በስፍራው በመገኘት መንግሥት ቅርሱን እንደሚጠግን ለነዋሪዎቹ ቃል ገብተው ነበር። ይህን ተከትሎ ጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ አወሮፓ ባመሩበት ወቅት ቅርሱ የሚጠገንበትን ድጋፍ ጠይቀው ከፈረንሳይ መንግሥት አዎንታዊ ምላሽ አግኝተዋል።

ይሁንና የተሰራው ጊዜያዊ መጠለያ አንደኛ ምሰሶው የተተከለው የቅርሱ አለት ላይ በመሆኑ በነፋስ ሃይል በሚወዛወዝበት ጊዜ ቅርሱ እንዲሰነጠቅ እያደረገው ነው፣ ሁለተኛ መጠለያው ለአመታት የቆየ በመሆኑ ቅርሱ ዝናብና ጸሐይ ስለማያገኝ የቅርሱ ጣሪያ ወደ አፈርነት እየተቀየረ ነው፤ በአጠቃላይ ደግሞ የመጠለያው የአገልግሎት ዘመን ስላለቀ በቅርሱ ላይ ወድቆ አብያተ ክርስቲያናቱን ያወድማል የሚል ስጋት እንዳላቸው ነዋሪዎቹ በተደጋጋሚ ያነሳሉ።

የላሊበላ ከተማ ከንቲባ ሙሉጌታ ወልደሚካኤል እንደሚሉት ደግሞ "መጠለያው ሲደረግ በሃላፊነት ስሜት ፣ በግልጸኝነት እና ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ የተሰራ ባለመሆኑ በዘላቂነት ቅርሶቹን መታደግ አልተቻለም"።

የባህልና ቱሪዝም ሚንስትሯ ዶር ሂሩት ካሳው ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ "የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት መንግሥት አስፈላጊውን ጥገና ለማድረግ እየሰራ ነው" ብለዋል።

ላሊበላ ከ900 አመት በፊት በኢትዮጵያውያን ተሰርቶ አሁን ግን የአውሮፓውያንን እርዳታ እየሻተ ነው። ከ10 አመት በፊት አሁን ያሉት መጠለያዎች በጣሊያን ኩባንያ የተሰሩ ናቸው። እነዚህ መጠለያዎች የአገልግሎት ዘመናቸው ስላለፈ መነሳት የነበረባቸው ከአመታት በፊት ነው።

የፎቶው ባለመብት, J. Countess

መጠለያውን ለማንሳትና ጥገናውን ለማከናወን 300 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ የሃገር ውስጥ ባለሙያዎች አረጋግጠዋል። 'ኢትዮጵያ ግን ለላሊበላ የሚሆን 300 ሚሊዮን ብር የለኝም አለች'። እናም አሁንም የተማጽኖ እጆቿን ወደ አውሮፓ ዘርግታለች።

ፈረንሳዮቹ ቃል ከገቡበት ጊዜ ጀምረው በትኩረት እየሰሩ ነው ያሉት ዶ/ር ሂሩት "ፈረንሳዮቹ በግላቸው የ10 አመት ጥናት ስለነበራቸው ለኛ አቅርበውልን ከሃገር ውስጥ ሙያተኞች ጥናት ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ቀጣይ ስራዎችን እየሰራን ነው" ብለዋል።

ሁሉንም ስራ ባስቀመጡት እቅድ መሰረት እየሰሩ አንደሆነ የገለጹት ሚንስትሯ "የሚሰራው ስራ ቅርሱን መጠገንና መጠለያውን ማንሳት ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ መልክዓ ምድራዊ (landscape) ስራ ይሰራል" ብለዋል። ቅርሱ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ተፈሰሶችን መሰራት እና የአረንጓዴ አካባቢዎችን ከማልማት ባሻገር አጠቃላይ የቅርሱን ታሪክ የሚያትቱ መጽሃፋት የሚቀመጡበት ቤተ መጽሐፍ ግንባታን ያካተተ ስራ ይሰራል ነው ያሉት።

የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሃይለማርያም ታደሰ በስራው ደስተኛ መሆናቸውንና ከፈረንሳዮቹ ጋርም ውይይት አድርገው መስማማታቸውን ገልፀዋል። ነገር ግን የእሳቸውም የሌላውም ነዋሪ ፍላጎት መጠለያው ተነስቶ ማየት ነው።

ዶር ሂሩት እንደሚሉት ደግሞ "መጠለያው በመኖሩ ቅርሱ ለብዙ ጊዜ ዝናብና ጸሃይ ስላላየ መጠለያው ቶሎ ቢነሳ ጉዳት ሊኖር ስለሚችል ጥገናው እየተካሄደ ነው መጠለያው የሚነሳው" ብለዋል። ከንቲባው ሙሉጌታ በአሁኑ ወቅት ለቅርሱ የተሰጠው ትኩረት የሚያስደስት መሆኑን ተነግረዋል።

ነገር ግን "በባለሞያዎች የተሰጠው መጠለያውን የማንሳት ጊዜ መራዘምና ህዝቡ ደግሞ አሁኑኑ እንዲነሳ ያለውን ፍላጎት ማጣጣም አለመቻሉ ግን ችግር ሆኖብናል" ብለዋል።

መጠለያውን ማንሳት ብቻ በቂ መፍትሄ አይደለም የሚሉት ሚኒስትሯ ቅርሱ በዘላቂነት የሚጠገንበትን መንገድ እየተፈለገ እንደሆነና በተደጋጋሚ በሚነካካበት ወቅት ችግሩ እየተባባሰ በመሄዱ የሁለቱ ሃገራት ሞያተኞች በጥምረት ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ነው።

መጠለያውን የፈረንጆቹ 2019 ከማለቁ በፊት ለማንሳት እቅድ መያዙን የገለጹት ሚንስትሯ በቀጣዮቹ ሳምንታትም የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ስራውን በይፋ የሚያስጀምሩ መሆኑንም ተናግረዋል።