ደቡብ አፍሪካዊው ኮማኪ ትሬቨር ኖዋ እየተወገዘ ነው

ትሬቨር ኖዋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የተወዳጁ "ዘ-ዴይሊ ሾው" አሰናጅና እውቁ ደቡብ አፍሪካዊ ኮማኪ ትሬቨር ኖዋ በማኅበራዊ የትስስር መድረክ ሚሊዯኖች ውግዘት እያዘነቡበት ነው።

ውግዘቱ በፓኪስታንና ሕንድ የሰሞኑ የካሽሚር ፍጥጫ ላይ የሰነዘረውን ቀልድ ተከትሎ የመጣ ነው።

ይህንኑ የማሕበራዊ ትስስር መድረኩን የውግዘት ዘመቻ ተከትሎ ትሬቨር በይፋ አድናቂዎቹን ይቅርታ ጠይቋል።

"ሕንድና ፓኪስታን ወደ ጦርነት ከገቡ በጣም አዝናኙ ጦርነት ይሆናል። በታሪክም ረጅሙ ጦርነት እንደሚሆን እገምታለሁ" በሚል ውጥረቱን ከቦሊውድ ፊልሞች ጋር በማስተሳሰር ነበር ቀልድ ለመፍጠር የሞከረው።

አድናቂዎቹ ትሬቨር ኖዋን "ዘረኛ" እና "ጨካኝ" ሲሉ ነው የተቹት።

ኖዋ ለአድናቂዎቹ በጻፈው የትዊተር የይቅርታ ደብዳቤ "እኔ ቀልድን የምጠቀመው ሕመምንና ስቃይንም ለማስታገስም ጭምር ነው። ሕንድና ፓኪስታን ላይ የኮመኩት ነገር ከጦርነቱም በላይ ትኩረት መሳቡ ግን ገርሞኛል፤ ለማንኛውም ካስከፋኋችሁ ይቅርታ" ብሏል።

የሰሞኑን የሕንድና ፖኪስታን የካሽሚር ግጭት ተከትሎ ሁለቱ የኒኩሌየር ታጣቂ ሃገራት ወደ ሙሉ ጦርነት እንዳያመሩ ስጋት አለ።

ፓኪስታን የሕንድን የጦር ሄሊኮፕተር መትታ ከጣለች በኋላ ውጥረቱን ለማርገብ በሚል የማረከችውን አብራሪ ለሕንድ አሳልፋ መስጠቷ ይታወሳል።