"ከመቶ ምናምን ፓርቲ ሴት የምናገኘው አንድ ወይም ቢበዛ ሁለት ሊሆን ይችላል" ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ

ብርቱካን ሚደቅሳ

በመላው ዓለም ማርች 8 የሴቶች ቀን ሆኖ ይከበራል። ቀኑን በማስመልከት የቀድሞዋ የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ አመራርና በቅርቡ የአትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሀላፊ ሆነው የተመረጡት ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ከቢቢሲ ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል።

ቢቢሲ፡ ከዚህ ቀደም የነበረውን የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ከአሁኑ ጋር እንዴት ያነጻጽሩታል?

ወ/ሪት ብርቱካን፡ ከዚህ በፊት በነበረው ሁኔታ ሴት ሆነህ በፖለቲካ ውስጥ ስትሠራ በጣም በብቸኝነት ነበር። እሱ ብዙ ችግሮች ነበሩት። ማንኛዉም ህብረተሰብ ውስጥ አንዱ የፍትህና የእኩልነት ጥያቄ ይህ ነው። የሴቶች አማራጮች ተብለው የሚቀርቡት ሃሳቦች ከምንም በላይ አስፈላጊ ናቸው። ካሏቸው ማህበራዊ ሃላፊነቶች የተነሳ ሴቶች ሲጎዱ አጠቃላይ ማህበረሰቡ እንደሚጎዳ ግልጽ ነው። እናም ተሳትፎው በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነበር ማለት ትችላለህ። አሁን ግን የተሻለ ሁኔታ አይተናል። ግን የተሻለ ነገር ያየነው በመንግሥት ሃላፊነት ነው። የፖለቲካ ፓርቲዎችን አደረጃጀትና የፖለቲካ አመራር ስታየው አሁንም ብዙ ልዩነት አላይም። የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆኜ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የውይይት መድረክ እመራለሁ። ከመቶ ምናምን ፓርቲ ሴት የምናገኘው አንድ ወይም ቢበዛ ሁለት ሊሆን ይችላል። ከፓርቲዎች አኳያ ስታየው "ሴቶችን እንዴት ወደ ፖለቲካ ማምጣት አለብን? ተቸገርን" ይላሉ። ነገር ግን የችግሮቹን መነሻዎች በደንብ ተመልክቶ ሥራዬ ብሎ የፖሊሲ አቅጣጫ አስቀምጦ እስከተሠራ ድረስ የማይቻል ሁኔታ ነው ተብሎ መተው የለበትም። እኛም እንደ ምርጫ ቦርድ የምናደርጋቸው ድጋፍና እገዛዎች ያንን ለማምጣት እንዲሆኑ እናረጋግጣለን። ይህንን የሚከታተል ራሱን የቻለ ክፍል አለ። እሱን እንከታተላለን።

ወ/ሪት ብርቱካን በወዳጆቻቸው አንደበት

ቢቢሲ፡ ለውጡ ያለው ከላይ ለው ክፍል እን ታችባለው የህብረተሰብ ክፍል አልተደገፈም ይባላልርሰዎ አስተያየት ምንድን ነው?

እኔ እንግዲህ ሃሳቦችንና አስተያየቶቼን በተመለከተ ካለኝ ሃላፊነት ብቻ መወሰን እፈልጋለሁ። የፓርቲዎችን እንቅስቃሴና ራሱን የምርጫ ቦርድ አደረጃጀት በተመለከተ (ቀጥታ ስለሚመለከተኝ ማለት ነው) ወደታች ስትሄድ በጣም ውስንነት እንዳለው ወደ ላይም ያንን አረጋገጠናል ለማለት ያስቸግራል። በተለይ ከመንግሥት መሥርያ ቤቶች አንጻር ስናይው ልዩነቱ የሰማይና የመሬት ነው። እናም ከዛ አኳያ ስናየው፣ አዎ ልክ ነው ብዬ እስማማለሁ።

"ሃገሬን ሳላስብ የዋልኩበት፤ ያደርኩበት ቀን የለም" ብርቱካን ሚደቅሳ

የቦርዱ ማሻሻያና የብርቱካን ሹመት ምንና ምን ናቸው?

ቢቢሲ፡ ምን መደረግ አለበት?

ወ/ሪት ብርቱካን፡ ምን መደርግ አለበት? የሚል ጥያቄ ባብዛኛው በጣም ደስ አይለኝም። ለምን መሰለህ ደስ የማይለኝ? እንዲህ መደረግ አለበት ብለህ ወይም እንደዚህ መደረግ አለበት እያልክ ስትወስን ያንን ለማድረግ የሚያስችል ሃላፊነትና አቅም ሲኖርህ ትንሽ ትረጉም ይኖረዋል። እንዲያው ባጠቃላይ ግን እንደዚህ መደረግ አለበት ሲባል ዝም ብሎ ማውራት ይመስለኛል። ግን ትንሽ ልሞክር።

የፖለቲካ ተሳተፎውን በተመለከተ፣ እኔ በምመራው ተቋም ሃሳቦችን እንዴት እንተግብራቸው በማለት የተለያዩ ክርክሮች አሉ። ክርክሮቹ በተለያዩ ሀገራት የራሳቸውን ጥሩ ዉጤት ያመጡ ናቸው። ሁልግዜ እንደገና ማሰብን ይጠይቃል። መፈክር ነገር ሰርተህ ወይም ሰርኩላር አስተላልፈህ የምትተወው ጉዳይ አይደለም።

በጣም የተላመድነው ነገር ስለሆነ፣ እያንዳንዱን ነገር ጊዜ ሰጥቶ ማሰብና እያንዳንዱ የምትወስናቸው የፖሊሲ ውሳኔዎች ላይ ያንን ማካተትህን ማረጋገጥ ይኖርብሃል። ለእንደዚህ አይነት ሥራዎች አይኑ ሊጋረድበት የሚችለው ወንድ ብቻ አይደለም። ሴቶች ሆነንም እንደሱ ልንሆን እንችላለን። ምክንያቱም የነበረው ሁኔታ ከባድ ነበር። በደንብ ካላሰብከው እንደ ወራጅ ውሃ ይዞህ ይሄዳል።

በተለይ የጾታ ጉዳይ ሲሆን ልዩነቱ ይሰፋል። ስለዚህ እያንዳንዱን ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይጠይቃል። ልታሳካቸውና ልትለካቸው የምትችላቸውን ነገሮች ማድረግ ይኖርብሃል። ለምሳሌ በመንግሥት አመራር ደረጃ የታየው ነገር እንደዛ ይመስለኛል። መሥራት የሚችሉትን አቀዱ አደረጉት። ሴቶች እንዲሳተፉ ብዙ ተነጋግረናል ግን አይፈጸሙም።

እኔ የፓርቲ አመራር ሆኜ ሠርቻለሁ። በርግጥ የተቃዋሚ ፓርቲ ላይ አሁን ሳይሆን በፊት ወጣቱ ላይም ችግር ነበር። ባጠቃላይ የፖለቲካ ሂደቱ ራስህን ለስቃይ የምትመለምልበት ነው። ሃሳብ አለኝ ስትል፣ ገና ግማሹን ውሳኔህን ሰጥተህ አደባባይ መጥተህ ልትናገር ስትል፣ "የመታሰር እድሌ ወደ 80 በመቶ ነው፤ ስለዚህ ስታሰር የትኛዉን መጽሃፍ አነባለሁ?" አይነት እቅድ ነው ያለው።

በእንደሱ አይነት ሁኔታ ደግሞ ሀገሪቱ ላይ ያሉት መልካም ነገሮች ይመጣሉ ብለህ አታስብም። በእርግጥ ያንን መስዋትነት የሚከፍሉ ሰዎች ይኖራሉ። ግን ገምቺ ብትለኝ፣ በህብረተሰቡ የፖለቲካ ተሳትፎ ውስጥ በጣም ያልተማከለ ተሳትፎ ነው የሚኖረው። በዚህ ምክንያት ብዙ የሕዝብ ተሳትፎ አታገኝም። የወጣቶች ተሳተፎ ስትል አታገኝም። የሴቶችንም እንደዛው። ያው ባለህ ነው የምትሄደው ማለት ነው። እንደዛ ሆኖም ግን የሃላፊነት ቦታ ላይ በነበርንበት ጊዜ የፖሊሲ ውሳኔና እቅድ ኖሮን ማድረግ የምንችላቸውን ነገሮች በትክክል አድርገናል ብዬ አላስብም።

ተያያዥ ርዕሶች