ለ60 ዓመታት የዘለቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድና የቦይንግ ግንኙነት

ተወልደ ገ/ማርያም

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደ አውሮፓውያኑ በ1945 ሥራ የጀመረው በአሜሪካ ሠራሽ አውሮፕላኖች ነበር። በጊዜው አየር መንገዱን ከከፈቱት ዐፄ ኃይለሥላሴ ጋር በተደረገ ስምምነት አየር መንገዱ ያቋቋመው ዛሬ ላይ ገበያ ላይ የሌለው የአሜሪካኑ TWA (Trans World Aviation) ነበር።

ከ15 ዓመታት በላይ ስለ አቬየሽን ኢንዱስትሪ የዘገበው የሪፖርተር ጋዜጠኛ ቃለየሱስ በቀለ ኢትዮጵያ አየር መንገድና ቦይንግ ከ60 ዓመት በላይ የዘለቀ የንግድ ግንኙነት እንዳላቸው ይናገራል።

"ለምሳሌ እንደ አውሮፓውያኑ በ1960ዎቹ D720 የመጀመሪያው ጀት ኤንጅን ያለው አውሮፕላንን መጀመሪያ ወደ አፍሪካ ያመጣው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነው።ከዚያም ቦይን 707፣ 727፣737፣ 757፣ 767ን አስመጥቷል።" ሲል ኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ 747 ውጭ ሁሉንም የቦይንግ አውሮፕላኖች እንደተጠቀመ ይገናገራል።

የጦር ኃይሎችን አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ ለመንደርደሪያ በቂ ስላልነበር የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ መገንባትም ከቦይንግ ጋር የሚያስተሳስረው የታሪክ ቅንጣት እንዳለው ይጠቅሳል።

ስለ አደጋው እስካሁን የምናውቀው

ቃለ እየሱስ እንደሚለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦይንግ 767 ፣ ድሪም ላይነር 787 አውሮፕላኖችን ወደ አፍሪካ በማምጣት የመጀመሪያው ነው። ወደ አፍሪካም ብቻ ሳይሆን ከሁለቱ የጃፓን አየር መንገዶች ቀጥሎ ከአሜሪካ አየር መንገዶች በፊት ቦይንግ 787ን ዓለም ላይ የተጠቀመው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደሆነም ያስረዳል።

ለምሳሌ እንደ ቦይንግ 707 እና 727 ያሉ የኩባንያው ሥሪት አሮጌ አውሮፕላኖች አሁን ከገበያ መውጣታቸውን በመጥቀስ ቃለየሱስ አውሮፕላን አምራቾች በየጊዜው የሚሻሻሉ አውሮፕላኖችን ከብዙ ጥናትና ምርምር በኋላ እንደሚያወጡ ይናገራል።

አውሮፕላኖቹ ሲሻሻሉ ደግሞ በዋናነት የነዳጅ አጠቃቀምና የመንገደኛ ምቾት ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮች ናቸው። "የአንድ አየር መንገድ ትልቁ ወጪ ማለትም ከ40 በመቶ በላይ ነዳጅ ስለሆነ አዳዲስ አውሮፕላኖች በተለይ ነዳጅ የሚቆጥብ እንዲሆኑ ይፈለጋል።"

ከትናንት ወዲያ የተከሰከሰው ቦይንግ 737-8 ማክስ በዚህ ረገድ ከ10-12 ከመቶ ነዳጅ ቆጣቢ እንደሆነ ይነገርለታል። ይህ አውሮፕላን ሥሪት በቦይንግ ታሪክ ብዙ ገበያን ያገኘና በ737 ሞዴሎች ዝርዝር ውስጥ የመጨረሻውና እጅግ ዘመናዊው ነው።

የንግድ አውሮፕላን ኾኖ ወደ ገበያ የገባውም እንደ ፈረንጆቹ በ2016 ነበር።

በእነዚህ ሁለት የአገልግሎት ዓመታት ውስጥ ታዲያ አውሮፕላኑ ሁለት ጊዜ አደጋ አጋጥሞታል። ከአምስት ወራት በፊት በኢንዶኔዥያ ጃካርታ ያጋጠመው አደጋ የመጀመርያው ሲሆን የእሑዱ ሁለተኛው መሆኑ ነው።

አውሮፕላኖቹ በተነሱ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ መከስከሳቸው ሁለቱን አደጋ እንደሚያመሳስለው ይገልፃል።

የአደጋው መንስኤ ምርመራ ተደርጎ በሲቪል አቬሽን ባለሥልጣን እስኪገለፅ እንዲህ ነው፣ እንዲያ ነው ብሎ መገመትን ዓለም አቀፉ የሲቪል አቬሽን ድርጅት ስለሚከለክል የመቆጠብ ነገር ቢኖርም "በኢንዶኔዥያውና በአሁኑ የኢትዮጵያ አደጋ ከበረራ መቆጣጠሪያ ጋር የተያያዘ ችግር ያለ ይመስላል" ሲል ቃለየሱስ የሩቅ ግምቱን ያስቀምጣል።

ዓለም ዓቀፍ የአቬሽን ኤክስፐርቶችም በስፋት እየገለጹ ያሉት የአውሮፕላኑ የበረራ መቆጣጠሪያ ስሪቱ አንዳች ችግር ሳይኖረው አይቀርምና እሱ ላይ ትኩረት ተደርጎ ምርመራ መደረግ አለበት እያሉ እንደሆነ በመጥቀስ ግምቱን ያጠናክራል።

በአሁኑ ሰዓት በርካታ ግዙፍ አየር መንገዶችም ይህንኑ ሥሪት ለጊዜው ከአገልግሎት ውጭ ለማድረግ መወሰናቸውም የሚነግረን ይህንኑ ነው።

ቻይና በቦይንግ 737 ማክስ 8 የሚደረጉ በረራዎችን አገደች

"አዲስ አውሮፕላን አዲስ እንደተወለደ ልጅ ነው"

ቃለየሱስ እንደሚለው አዲስ አውሮፕላን ሲመረት ብዙ ጊዜ ከችግር ጋር ነው የሚመጣው። እርግጥ ነው አዲስ ቴክኖሎጂ ስለሆነ ብዙ ሙከራ አድርገው ነው የሚያወጡት። ብዙ ፍተሻም ይደረግባቸዋል።

"ይሄን ሁሉ ፍተሻ አልፎ ሲወጣ ግን አውሮፕላን ላይ አንድ ችግር አይጠፋም" የሚለው ቃለየሱስ ድሪምላይነር 787 ከባትሪ ጋር የተያያዘ ችግር እንደነበረበት በዚህም ዓለም ላይ ያለ ድሪምላይነር 787 ሁሉ ለወራት እንዳይበር ተደርጎ እንደነበር ያስታውሳል።

የዚህ ዓይነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድሪምላይነር አውሮፕላን 2013 ላይ በለንደኑ ሄዝሮው አውሮፕላን ማረፊያ በቆመበት እሳት ተነስቶ እንደነበርም፣ ጃፓን አየር መንገድም በዚሁ አውሮፕላን ተመሳሳይ ችግር ገጥሞት እንደነበር ቃለየሱስ ያስታውሳል።

"የባትሪው ችግር ከተፈታ በኋላ ዛሬ ግን ድሪምላይነር 787 በጣም ጥሩ አውሮፕላን ነው።"

"የአቬሽን ኢንዱስትሪ ኤክስፐርቶች አዲስ የተሠራ አውሮፕላንን አዲስ ከተወለደና ጥርስ ሲያወጣ ከሚያስቀምጠውና ጉንፋን ቶሎ ቶሎ ከሚይዘው ህፃን ጋር ያመሳስሉታል" ሲል ነገሩን በቀላሉ ለማስረዳት ይሞክራል።

አዲስ አውሮፕላን ሲመጣ አስፈላጊውን ስልጠና በሙሉ አብራሪዎች እንዲወስዱ ማድረግ ወጪው ቀላል ስላልሆነ አየር መንገዶች በዚህ ጉዳይ ላይ ደከም ሊሉ እንደሚችሉ ይነገራል ።እዚህ ጉዳይ ላይ ቃለየሱስን አስተያየቱን ጠይቀነው ነበር።

"ኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦይንግ ብቻ ሳይሆን አሁን የኤርባስም ባለቤት ሆኗል። አዲስ አውሮፕላን ሲወጣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፓይለቶች አምራቹ ጋር ሄደው ስልጠና ይወስዳሉ። ይህን ኤርባስ ሄጄ ተመልክቻለሁ" የሚል መልስ የሰጠው ቃለየሱስ ይህ ተለመደ አሰራር እንደሆነ ያስረግጣል።

በአዲስ አበባ ህዝባዊ ውይይት የታሰሩ ተለቀቁ

ከአውሮፕላን የመረጃ ሳጥን ምን ዓይነት መረጃ ይገኛል?

የአውሮፕላን የመረጃ ሳጥን ሁለት ክፍሎች ያሉት ሲሆን አንደኛው አውሮፕላኑ ጋቢና ውስጥ አብራሪዎቹ ከአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ጋር ያደረጉትን ንግግር ሲቀዳ ሌላኛው ደግሞ አውሮፕላኑ በምን ያህል ፍጥነት፣ አንግልና ከፍታ ሲበር እንደነበር የሚሉና ተያያዥ የበረራ መረጃዎችን የሚመዘግብ ነው።

ጥቁሩ ሰንዱቅ የመጀመሪያው ፓይለቶቹ አውሮፕላኑ ውስጥ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ የተነጋገሩትን የግል ወሬ ሳይቀር ይቀዳል ማለት ነው" ሲል ያስረዳል ቃለየሱስ።

ለመሆኑ ይህን የመረጃ ሳጥን የመመርመር ሥልጣን ያለው ማን ነው?

ጥቁሩ የመረጃ ሰንዱቅ እጅግ ረቂቅ በመሆኑ ምርመራ የሚደረገው ወደ ውጭ ተልኮ ነው። የምርመራ ውጤቱ ከውስብስብ የአቪየሽን ፖለቲካ ነጻ ለማድረግም ከፍተኛ ጥንቃቄን ይፈልጋል። ይህም የሚሆነው አውሮፕላን አምራቾችን ጨምሮ አየር መንገዶች በውጤቱ ላይ እጃቸው ረዥም ስለሚሆን ነው።

በዓለም አቀፉ የሲቪል አቬሽን ድርጅት አሠራር መሠረት የአደጋውን ምርመራ የመምራትና ምርመራ የማድረግ ሥልጣን አደጋው የደረሰበት አገር ሲቪል አቬሽን ባለሥልጣን ይሆናል።

ቤሩት ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን አደጋ ሲደርስበት የምርመራውን ሂደት የመራው የሊባኖስ ሲቪል አቬሽን ባለሥልጣን እንደነበርና ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሊባኖስ አቪየሽን ከኢትዯጵያ በርካታ መረጃዎችን ቢወስድም በምላሹ ለኢትዯጵያ መረጃዎችን በመስጠት ረገድ በሚፈለገው ደረጃ ተባባሪ እንዳልነበር ያወሳል።